እየተባባሰ የመጣው የመንገድ ላይ ጥቃት
ሰኞ፣ ጥር 27 2016ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የደቡባዊ ኢትዮጵያ ከተሞች የተዘረጉ ጎዳናዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታጣቂዎች እንደልብ የሚንቀሳቀሱባቸው መስመሮች እየሆኑ መምጣታቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ለወትሮው አንጻራዊ ደህንነት ይስተዋልባቸው የነበሩት ከአዲስ አበባ ሀዋሳ ፣ ወልቂጤና ቡታጅራ መንገዶች አሁን አሽከርካሪዎች በሥጋት ፤ መንገደኞች በጸሎት የሚጓዙባቸው መስመሮች ሆነዋል ነው የሚባለው ፡፡
የውብዓለም እምባ
የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ውብዓለም አማረ ነዋሪነታቸው አርባምንጭ ከተማ እንደሆነ ይናገራሉ ፡፡ በጭነት መኪና አሽርካሪነት የተሰማሩት ባለቤታቸው ጥር 13 ቀን 2016 ዓም ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ በመጓዝ ላይ ሳሉ በስልክ መገናኘታቸውን ወይዘሮ ውብዓለም ያስታውሳሉ ፡፡
«እየደረስኩ ነው ሲለኝ ከአራት ልጆቼ ጋር የጠበኩት ባለቤቴ ግን በታጣቂዎች መገደሉን ፖሊስ ደውሎ ነገረኝ» ያሉት ወይዘሮዋ «ባለቤቴ በጥይት ተመቶ አርሲ ነገሌ ሆስፒታል መግባቱን ፖሊስ ደውሎ ነገረኝ፡፡ የተባልኩት ሆስፒታል ስደርስ ሆዱ ተመትቶ አንጅቱ ወጥቷል፡፡» «ባለቤቴ መጥታለች እሷ ናት» «ካላቸው በኋላ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል» በማለት በለቅሶ በታጀበ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
የተሽከርካሪዎች የጅምላ ቃጠሎ
በምሥራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ ነዋሪ የሆነው ክፍሌ ባልቻ እንደ ወይዘሮ ውብዓለም አማረ ባለቤት ታጣቂዎቹ አልተኮሱበትም፡፡ ነገር ግን «ቤተሰቤን አስተዳድርበት ነበር» ያለውን ሚኒ ባስ ተሽከርካሪ እንዳቃጠሉበት ነው ክፍሌ ለዶቼ ቬለ የተናገረው ፡፡ « ታጣቂዎቹ የመጡብኝ ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ በመጓዝ ላይ እንዳለሁ ነበር» የሚለው ክፍሌ «ኦሮሚያ ክልል ተሬ ወረዳ ልንደርስ ጥቂት እንደቀረን ነው ታጣቂዎቹ ያገኙን፡፡ በምልክት እንድቆም ሲነግሩኝ ተሽከርካሪውን ከዳር አቆምኩ ፡፡ ምክንያቱም ከፊት ሌሎች ታጣቂዎች ስላሉ የማምለጥ ዕድል አልነበረኝም ፡፡ ሊያመልጡ ሞክረው የተገደሉም አሉ ፡፡ በመጨረሻም ተሳፋሪውን አስወርደው የእኔን ጨምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ማቃጠል ጀመሩ» ብሏል ፡፡
የሥጋት ጉዞዎች
በታጣቂዎቹ ጥቃት ባለቤታቸውን ያጡት ወይዘሮ ውብዓለምም ሆኑ ተሽከርካሪው የተቃጠለበት ክፍሌ «ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት ምን እያሰበ ነው?» ሲሉም ይጠይቃሉ ፡፡ ዶቼ ቬለ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ስለተባለው የታጣቂዎች ጥቃት የኦሮሚያንም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ የሥራ ሃላፊዎችን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ነገር ግን መንግሥት በአካባቢው መሰል ጥቃቶችን እየፈጸመ የሚገኘው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን እንደሆነ ደጋግሞ ገልጿል፡፡ ቡድኑ በዚህ ድርጊት እጄ የለበትም በማለት በፋንታው የመንግሥት የጸጥታ አካላትን ይወነጅላል ፡፡
በሰላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና
አቶ አንዱዓለም ግርማ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም እና የአካባቢ አስተዳደር መምህር ናቸው ፡፡ ዶቼ ቬለ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የታጣቂዎች ጥቃት በተመለከተ ያነጋገራቸው አቶ አንዱዓለም «የታጣቂዎቹ ጥቃት የችግሩን ክብደት ያህል ትኩረት ያገኘ አይመስለኝም» ይላሉ፡፡ የነፍስ ግድያዎችና የንብረት ውድመቱ እየተካሄደባቸው የሚገኙት ከአዲስ አበባ ብዙም ባራቁ ሥፍራዎች ላይ ነው የሚሉት አቶ አንዱዓለም «ነገሩ የክብደቱን ያህል ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም ህዝቡ ያለበትን ስጋትና ችግር እያስተጋቡ አይደለም» ብለዋል ፡፡
ከዚህ ሥጋት ለመውጣት መፍትሄው ምንድን ነው? በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት አቶ አንዱዓለም « መፍትሄው አንደኛ ሕግን ማስከበር ሁለት ጥያቄ አለን ከሚሉ ታጣቂዎች ጋር ሰላማዊ ድርድር ማድረግ ነው» ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ድርሻውን መውሰድ ያለበት መንግሥት ሊሆን እንደሚገባ የጠቀሱት አቶ አንዱዓለም «ምክንያቱም መንግሥት የሚያስፈልግበት የመጀመሪያው ዓላማ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ለመጠበቅ ነው፡፡ መንግሥት በብቸኝነት «የሞኖፖሊ ፓወር» የተሰጠው ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ዋስትና እንዲሆን ነው፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በመንግሥት በኩል የሚታየው የቁርጠኝነት ችግር መቀረፍ ያለበት ይመስለኛል» ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ