ኦላፍ ሾልስ መተማመኛ ድምፅ አጡ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2017የጀርመን ፓርላማ ቡንደስ ታግ ዛሬ በመራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ላይ የመተማመኛ ድምፅ ሲጠይቅ ነዉ የዋለዉ። ሾልዝ የመተማመኛ ድምፅን አተዋል። በመራሄ መንግሥቱ ላይ የመተማመኛ ድምፅ ለመካሄድ የተወሰነዉ በቅርቡ ጥምረቱ የፈረሰበት የጀርመን መንግሥትን ለመተካት ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነዉ። ምርጫዉ ከመካሄዱ በፊት ግን በመራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ላይ የመተማመኛ ድምፅ እንዲካሄድ ተጠይቆ ነበር። መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የመተማመኛ ድምፅ ማጣታቸዉ የተሰማዉ ዛሬ ምሽት ላይ ነዉ።
የጀርመን ፓራላማ በቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ላይ ያለውን እምነት ባካሄደዉ ድምፅ አሰጣጥ ማንሳቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል። ለመራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በመተማመኛ ድምፅ የሰጡ 207 የፓርላማ አባላት ሲሆኑ 394 የፓርላማ አባላት ደግሞ ሾልዝን ተቃዉመዋል። 116 የፓራላማ አባላት ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። እንደታሰበው ሁሉ የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ቢያንስ የ367 ድምፅ ማጣታቸዉ ይፋ ሆንዋል። ዛሬ በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ የተካሄደዉን የመተማመኛ ድምፅ አሰጣጥና ዉጤቱን ተከትሎ፤ የሶሻል ዲሞክራቶቹ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለጀርመን ፌደራል መንግሥት ምርጫ ጥርግያ መንገዱን መክፈታቸዉ ይፋ ሆንዋል።
የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ እስከያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን 2024 ዓመት መጨረሻ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ለማስቻል በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥባቸዉ እንደሚሰሩ ቀደም ብለዉ አስታዉቀዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አባሉ፤ የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ፤ ከጀርመን ከቴሌቪዥን ጣብያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ «የፓርላማ አባላቱ አዲስ ለሚካሂዱት ምርጫዎች የጊዜ ሰሌዳ ላይ መስማማት ይኖርባቸዋል፤ ቀኑ ሲወሰን፤ በቀጣይ የሚደረጉ እቅዶች ላይ ለመስራት እችላለሁ» ሲሉ ተናግረዉም ነበር። በአፋጣኝ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አዲስ ሕጋዊ መንግሥት እንደሚያስፈልግም ሾልዝ ገልፀዉ ነበር።
በጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች፤ አረንጓዴዎች እና ሊበራል ፓርቲዎች የተጣመሩበት የሦስትዮሹ መንግሥት ከፈረሰ በኋላ፣ ቻንስለር ሾልዝ የተለያዩ ትችቶች ሲቀርቡባቸዉ ነበር። ይህን ተከትሎ ተቃዋሚዎቹ እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስቲያን ኅብረት ፓርቲዎች ህዝብ የሚሰጣቸው ድጋፍ ጨምሯል።
መደበኛው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ በመጪው ዓመት መስከረም ነበር የሚካሄደው። ሆኖም ሾልዝ የጥምሩ መንግሥት አካል ከሆነው የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪና የፋይናንስ ሚኒስትራቸው ክርስቲያን ሊንድነር ጋር ለወራት ሲያሟግታቸው በቆየው በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም የሀገሪቱ በጀት ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ሾልዝ ያባረሯቸው ሊንድነር ከጥምሩ መንግሥት ሲወጡ መንግሥቱ ፈርሶ ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ እንዲጠራ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ