ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች 1 ተማሪ ብቻ የወደቀበት ትምህርት ቤት
ዓርብ፣ መስከረም 10 2017ከተቀረው የሀገሪቱ ክፍል በተለየ ትግራይ ክልል ውስጥ የ 2016 ዓመተ ምህረቱን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወሰዱት ተማሪዎች ቀደምሲል በነበረው የፈተና አሰጣጥ ስርዓት ስለተፈተኑ ጠቅላላው ውጤት እንደ ሌሎቹ 600 ሳይሆን 700 ነጥብ ነበር። ይህንንም ፈተና ተማሪ ዮናስ ንጉሰ 675 ነጥብ በማግኘት፣ ተማሪ ሄለን በርኸ ደግሞ 662 ነጥብ በማግኘት ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግበዋል። ተማሪ ሄለን በቅድሚያ ለምን ትግራይ የሚገኙ ተማሪዎች ከ700 አጠቃላይ ነጥብ እንደተፈተኑ ታብራራለች፤ « እኔ 10ኛ ክፍልም ማትሪክ ወስጃለሁ። ከኛ በኋላ ያሉት ከ 9ኛ እስከ 12ኛ ተምረው ነው የሚፈተኑት። እኛ ግን 12ኛ ክፍል ላይ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍልን ብቻ ነው መፈተን የነበረብን። 2013 ላይ መፈተን ነበረብን። ትምህርት ተቋርጦ ስለነበር ለዛ ነው በድሮው አፈታተን አሁን የተፈተነው።»
ይህንኑ ፈተና 675 ነጥብ በማምጣት ቀዳሚውን ውጤት ያስመዘገበው የ20 ዓመት ወጣት ዮናስ እንደነገረን የስኬቱ ሚስጥር በተማሪዎች መካከል የሚደረግ ፉክክር ነው።
« በቃላሚኖ ትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪ ጎበዝ ነው። ስለዚህ ፉክክር አለ። ፉክክር ደግሞ በርትተን እንድናጠና ይረዳል። መምህራንም ይረዱናል። ለፈተና አንድ ወር ያህል ሲቀረንም በቀን እስከ 9 ሰዓት ድረስ እያጠናሁ እዘጋጅ ነበር።»
ተማሪ ሄለንም ብትሆን ለዚህ ውጤቷ ተግታ ማጥናት ነበረባት። « ለፈተናው በጣም ነው የተዘጋጀሁት። እንደሚታወቀው ትግራይ ውስጥ በጣም ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍነው። ከዛ በኋላ ወደ ትምህርት ለመመለስ ከብዶኝ ነበር። ሁለት ሶስት ዓመታት ከእድሜ ተቀንሷል። ያንን ለማካካስ ቀን እና ሌሊት ነበር የማጠናው። እግዚያብሔር ይመስገን የልፋቴን ሰጥቶኛል። »
ለሶስት ዓመታት ያህል ያለ ትምህርት
በአሁኑ ሰዓት መቀሌ ከተማ የምትገኘው ሄለን ተወልዳ ያደገችው ማይጨው ከተማ ነው። ለሶስት ዓመታት ያህል «ስለ ትምህርት የማስብበት ጊዜ እንኳን አልነበረኝም» ስትል የጦርነቱን ጊዜ መለስ ብላ ታስታውሳለች « ያለንበት ቦታ ጦርነት ሲነሳ ጦርነት ወደሌለቤት ቦታ እንሄዳለን። ቤተሰቦች ይሰቃያሉ።ያንን ማየት ለእኔ ከባድ ነበር። እህል አልነበረም። ቢኖርም ወፍጮቤት ስላልነበር ቆሎ ብቻ ነበር የምንበላው እና ከባድ ጊዜ ነበር»
ዮናስም ለሶስት ዓመታት ያህል ከማደሪያ ትምህርት ቤቱ ርቆ ሽሬ የሚገኙ ቤተሰቦቹ ጋር ሄዶ ነው የጦርነቱን ወቅት ያሳለፈው። በዚህም ወቅት በመጠኑም ቢሆን ራሱን ከትምህርት ሳያገል ቆይቷል። «መፅሀፍት አነብ ነበር። ሌላው ደግሞ የጎረቤት ልጆችን መሠረታዊ የሆኑ የሂሳብ እና እንግሊዘኛ ትምህርቶችን አስጠና ነበር።»
ኢትዮጵያ ውስጥ በ 2016 ዓ ም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎቻቸውን ያስፈተኑ 1363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪያቸው ለከፍተኛ ተቋም ትምህርት የሚያስፈልገውን ነጥብ አላገኘም።
ዮናስ እና 21 ዓመቷ ሄለን የተማሩበት የቃላሚኖ ልዩ ትምህርት ቤት ግን ካስፈተናቸው የሁለት ዙር በጠቅላላው 284 ተማሪዎች የወደቀው አንድ ተማሪ ብቻ ነው። ይህም ምክንያት እንዲጣራ ጠይቀናል» ብለውናል የትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መምህር ታጋይ ዘበነ ሀብቴ « ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከእነዚህ ሁሉ ተማሪዎች አንድ ተማሪ ወድቋል። ምክንያቱን ለማወቅ ጠይቀናል። በትምህርት ቤቱ እንደዚህ አይነት ነገር ታይቶ አይታወቅም። መልስ እየጠበቅን ነው። »
የቃላሚኖ ትምህርት ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መምህር ታጋይ አክለው እንደገለፁልንም ፈተናውን ከ 700 ነጥብ ከወሰዱት 284 ተማሪዎች መካከል 92ቱ ከ 600 ነጥብ በላይ ማግኘት ችለዋል። ከዚህም ሌላ ትምህርት ቤቱ ባለፈው ዓመት መስከረም አካባቢ 106 ተማሪዎችን ያስፈተነ ሲሆን ሁሉም 106 ተማሪዎች ፈተናውን አልፈዋል።
ትምህርት ቤቱ ስኬታማ ተማሪዎችን ለማፍራት የቻለው እንዴት ይሆን?
« ይህ ትምህርት ቤት የትግራይ ልማት ማህበር የሚያስተዳድረው ትምህርት ቤት ነው። አስተማሪዎቹ እነዚህን ተማሪዎች ብቁ ለማድረግ ቀንና ሌሊት ይሰሩ ነበር እንጂ የተለየ «ሪሶርስ» ኖሮት አይደለም። ተማሪዎች እዚህ ትምህርት ቤት ለመግባት ክልል ላይ በሚሰጠው ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማምጣት አለባቸው፣ ሁለተኛ ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን መግቢያ ፈተና ማለፍ አለባቸው። ሶስተኛ የናቹራል ሳይንስ ተማሪ መሆን አለባቸው። ከጦርነቱ በፊት ደግሞ እድሜያቸው 15 እና ከዚያ በታች መሆን ነበረባቸው »
ተማሪ ዮናስ እና ሄለን ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አለማለፋቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያሳስባቸዋል። እንደ ተማሪ ደግሞ ለዚህ ምክንያት ይሆናሉ የሚሉትን አካፍለውናል። «ያለፈው የትምህርት ስርዓት የፈጠረው ነው ብዬ አስባለሁ፤ ከዚህ በፊት በሌላ ሰው ላይ ጥገኛ ሆኖ የመጣ ተማሪ ይኖራል። ይህ አሰራር ስለተቀየረ ሊሆን ይችላል። አቅም ኖሯቸው ስለማይረጋጉ ሊሆንም ይችላል» ትላለች ሄለን። ዮናስ ደግሞ « ተማሪዎች የሚወድቁት ስለማያጠኑ ይመስለኛል። ሌላው ደግሞ በትምህርት ላይ ተስፋ መቁረጥ ይመስለኛል»
የሚከብድ ትምህርት ላይ አተኩሮ መስራት
ሄለን የፊዚክስ ትምህርት ይከብዳት የነበረ ትምህርት እንደነበር ነግራናለች። ይሁንና ባደረገችው ጥረት ከመቶ መቶ ውጤት ማምጣት ችላለች። ታድያ ሌሎች ተማሪዎችም ስኬታማ እንዲሆኑ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?« ያለፉትን አመታት የማትሪክ ፈተናዎች እሰራ ነበር። አብረውኝ ዶርም ካሉ ተማሪዎች ጋር አብረን እናነብ ነበር። እና የቡድን ስራ አስፈላጊ ነው። ሌላው ደግሞ የሚከብዳቸውን ትምህርት ባይተውት እና ቢያጠኑ ጥሩ ነው።ከዛ ደግሞ እችላለሁ ብሎ ራስን ማሳመን ነው»
ተማሪ ሄለን ብትችል አዲስ አበባ በህክምናው ዘርፍ በተለይም በነርቭ ህክምናው ዘርፍ ተሰማርታ መማር እና መስራት ትፈልጋለች። «ብዙ ሰው የነርቭ ህክምና ስለማያጠና እዛ ገብቼ ያለውን እጥረት እቀርፋለሁ ብዬ እገምታለሁ። አዲስ አበባ ደግሞ ሰፊ ከተማ ስለሆነ ለውጭ የትምህርት እድልም ይመቻል። ኤምባሲዎች እዛ አሉ።» ዮናስ ደግሞ የኮምፒውተር ሳይንስ ማጥናት ይፈልጋል። መቀሌ ዮንቨርስቲ ቀዳሚ ምርጫው ነው።
በአሁኑ ሰዓት ለዮንቨርስቲዎች እያመለከቱ እና ለመግቢያ ፈተና እየተዘጋጁ የሚገኙት ሄለን እና ዮናስ ውጤታቸውን ካወቁ በኋላ በዕለት ከዕለት ህይወታቸው ላይም ስለተቀየረው ነገር ገልፀውልናል። «ሽልማቾች አግኝቻለሁ። ሌላ ደግሞ የስልክ ጥሪዎች በዝቶብኛል። ብዙ ሰዎች አውቀውኛል። ቃለ መጠይቆች አሉኝ። እሱን ማኔጅ ማድረግ ይከብዳል።»
ሄለንስ?« ትንሽ የራሴን ህይወት ለመኖር ከብዶኛል። ሁሉም ነገር ግልፅ ስለሆነ ሰው በመንገድ ሲያገኘን ይጠይቀኛል። በርግጥ ደስ ይላል ለእኔ ሞራል ነው። ግን ቃለ መጠይቅ እናደርጋለን እና ለራሴ ትንሽ ጊዜ አጥቻለሁ።»
ማን አርዓያ ሆናቸው?
ሁለቱም ተማሪዎች የበኩር ልጆች ሲሆኑ አርዓያ ሆኖኛል የሚሉት አባታቸውን ነው። « አባቴ ለትምህርት ያለው ፍላጎት አግዞኛል። የፈለኩትን ነገር ይገዛልኝ ነበር። ሶስተኛ ክፍል እያለሁ ኮምፒውተር ገዝቶልኛል። እና ለኮምፒውተር ያለኝ ፍላጎት እንዲጨምር አግዞኛል።»
« ቤት ውስጥ አርዓያ የሆነኝ አባቴ ነው። አባቴ በጣም ጠንካራ ተማሪ ነበር። እናት እና አባቱ ገበሬዎች ነበሩ። ቢሆንም በራሱ ጥረት ነው የተማረው። እኛንም ለማሳደግ ብዙ ነገሮች እየከፈለ ነው። እሱ ያጋጠመው ነገሮች እኛ እንዲያጋጥመን አይፈልግም። እና አባቴ አርዓያዬ ነው»ትላለች ሄለን።
ልደት አበበ
ፀሀይ ጫኔ