ቃለ ምልልስ ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ዴታ ከበደ ደሲሳ ጋር
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 2016ዛሬ ከሰዓት ዘርዘር ብሎ የወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ መካከል ከሰሞኑ የተፈረመው የመግባቢ ሰነድ “በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ መስኮች ሰፋ ያለውን የትብብር አድማሶችን ያካተተ” ነው ይላል፡፡ሶማሌ ላንድ በእንግሊዝ ቅኝ ተገዝታ እአአ ጁን 26 ቀን 1960 ነጻነቷን ማሀግኘታን በታሪካዊ ዳራነት ያጣቀሰው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር መግለጫ፤ ሶማሌላንድ ሶማሊያ ከጣሊያን ቅን ግዛት ከተላቀቀች በኋላ ዳግም ሶማሊያን ብትቀላቀልም ከ1991 እ.አ.አ ጀምሮ ለ30 ዓመታት እራሷን እንደ አገር በመሰየም ዴሞክራሲን በመለማመድ ላይ ትገኛለች ብሏል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በሐርጌሳ ቆንስላ ጽ/ቤት ከፍተው እንደሚንቀሳቀሱም በማንሳት የወደብ አገልግሎትን ጨምሮ ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ስምምነት ስምምነት ስለመፈረሟም አመልክቷል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት ይፈቀድ የነበረ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ እንደነበርም በማስታወስ፤ ኢትዮጵያ አሁን የፈረመችው የወታደራዊ ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሰጥቶ መቀበልና በኪራይ መልክ በመሆኑ ስምምነቶቹ በመርህ ደረጃ አይለያዩም ብሏል።
የስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች
በተያዘው ዓመት መንግስት ይህንኑን ፍላጎቱን ቤፋ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ማቅረቡ ተነስቶ፤ ከሶማሌ ላንድ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ለወራት “በብስለትና በስክነት” ምክክር እና ድርድር ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል። የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ ለኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ ነው ተብሏልም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በምላሹ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል። ከዚያም ባሻገር በሂደት ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም እንደሚወስድም በስምምነቱ ስለመካተቱ ተነግሯል፡፡
ስምምነቱን የተከተሉት ውዝግቦች
ይሁንና ይህ ስምምነት ከተለያዩ ወገኖት የሚወዛግቡ አስተያየቶችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ በዚሁ ላይ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ጉዳዩ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት ሰፊ ጥናት የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡ አቶ ከበደ “እንደ አገር አገራዊ ትቅምን አስቀድሞ ከማሰብ ይልቅ የተገኘውን ድል የአንድ ወገን ስኬት አድርጎ ማሰብ” በዜጎች መካከል ለተነሳው ውዝግብ ምክኒያት መሆኑንም በማስረዳት ጉዳዩ “ቢያንስ በኢትዮጵያውያን መካከል ልዩነት መፍጠር ያልነበረበት” ብለውታል፡፡
አቶ ከበደ “እንደ መንግስት ኢትዮጵያን የባህር በር እንደሚያስፈልጋት በአደባባይ ስንናገር ቆይተናል፡፡ ከዚያም አልፎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተጻፈው የመጀመሪያው የመደመር መጽሃፍ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተጽእፎ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ አስቀድሞ ጉዳዩ ታስቦበት የተቀመጠ መሆኑን ያስረዳል” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በጉዳዩ ዙሪያ ክፍተቶች እንኳ ቢኖሩ በጥናት መተባበር እንጂ ሂደቱን መቃወማቸው ያልተገባ ነው በማለትም የተቹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ተገኝቷል ያሉት ስኬት ላይ ውሃ መቸለስ ያልተገባ ሲሉም ወርፈዋል፡፡ ጉዳዩን “አብዛኛው ቅን ኢትዮጵያውያን የደገፉት” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ትናንት ለተሰየመዉ ለሐገሪቱ ጥምር ምክር ቤት (ፓርላማ) ባደረጉት ንግግር «ሉዓላዊነታችን ሲደፈር ዝምብለን አንቀመጥም» በማለት ኢትዮጵያን በሐገራቸው ሉዓላዊነት ጣልቃ መግባት ከሰዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ አካላትም ሂደቱን የተቃወሙ አሉ፡፡
በዚህ ላይ የመንግስታቸውን ምላሽ የተጠየቁት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ “ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከበረው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም ለማስከበር በምትንቀሳቀስበት ወቅት የጣሰችው መርህ የለም ነው ያሉት፡፡ “ሶማሌ ላንድ የራሷ መሪ፣ የራሷ መንግስት እና ዜጎች ያላት ለዜጎቻም የራሷን ፓስፖርት የምታድል ናት” ብለው ራስገዝ የሆነችው ሶማሌ ላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከበርካታ አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሰረተች ብለው ገልጸውአታል፡፡ ሶማሌ ላንድ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ቻይና፣ ታይዋን፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ እና እንግልዝን ከመሳሰሉ አገራት ጋር ጉዳይ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤቶችን ከፍታ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት መመስረቷን አንስተውም፤ ኢትዮጵያ ጋር ሲሆን ለምን ጥያቄ አስነሳ የሚለውን ጥያቄ አስገንዝቦ ማንሳት የተገባ ነው ብለዋል፡፡ መሰል ስምምነት አዲስ ነገር አለመሆኑንም በማንሳት ሞቃዲሾ ካለው የሶማሊያ መንግስት ጋርም ኢትዮጵያ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ስራ የነበራትና ያንኑን የማስቀተል ፍላጎት መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡ የሶማሊ መንግስት ተቃውሞን “ግር የሚያሰኝ” ያሉት አቶ ከበደ “ምናልባትም ቀጠናዊ ጉዳዩን ሊያወሳስብ የሚችል” በማለት ገልጸውታል፡፡
የኢትዮጵያ ቀጣይ የቤት ስራ
ኢትዮጵያ የሶማሌን ሉዓላዊነትን የመጋፋት ፍላጎት የላትም ያሉት አቶ ከበደ ቀጣይ የመንግስትታቸው ትኩረት የተፈጠሩትን የዲፕሎማሲ ክፍተቶች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ገፍቶ መፍታት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ከሰሞኑ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መሆኑንም ያስረዱት አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ በቀጣይ “ምናልባትም በቅርቡ የስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች በውይይት ዳብሮ እንደሚፈረም” አክለው ገልጸዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ወደቡን የምታገኘው በሊዝ መልክ ነው የሚሆነው፡፡ ግን ኢትዮጵያ የወደቡን ማልማትና ቁጥጥር በራሷ የምተከውን ነው የሚሆነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ወደብና የጦር መንደር ትገነባለች ተብሎ ነው የሚታሰበው፡ሶማሌ ላንድም በሰጥቶ መቀበል መርህ ከኢትዮጵያ ልማት ድርጅቶች ጥቅሟን የምታረጋግጥበት የሉዙን ዋጋ ታገኛለች ተብሎ ነው የሚጠበቀው” ሲሉም ስለስምምነቱ ግብ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ መሰል የወደብ እና የባህር በር አማራጮችን መፈለጓን ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በምትከውናቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች ትቀጥላለችም ነው የተባለው፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ባለፈዉ ሰኞ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ገቢራዊ ከሆነ ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚገኘዉን የበርበራን ወደብ እንደምትጠቀም ይታመናል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚዘብሔር