1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሞዴልነት ወደ ጫማ አምራችነት የገባችው ምስጋና

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥቅምት 22 2017

ምስጋና ገ/እግዚአብሔር የሞዴሊንግ ሥራዋን የጀመረችው በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ሳለች ነበር። « ሞዴል መሆን የምፈልገውን ስራ ከመስራት አልከለከለኝም» ትላለች። አሁን ላይ ከራሷ አልፋ ከ30 በላይ ለሚሆኑ ተቀጣሪ ሰራተኞች እንደተረፈችም በኩራት ትናገራለች። ምኞቷ ስለነበረውና እውን ስላደረገችው ስራ ጠይቀናታል።

https://p.dw.com/p/4mOv4
ምስጋና ገ/እግዚአብሔር ጫና ስትሰራ
ምስጋና ገ/እግዚአብሔር ምስል Privat

«ሴቶች ከወንዶች ጠባቂ መሆን የለባቸውም»

«ለምናደርጋቸው ነገሮች ፅናት ይኑረን » ትላለች የዛሬዋ እንግዳችን መስጋና ገ/እግዚአብሔር ። መስጋና ወደ ሞዴሊንግ ስራ የገባችው በ19 ዓመቷ ገና ተማሪ ሳለች ነው።  በወቅቱ ምንም አይነት የሞዴልነት የስራ ልምድ ባይኖራትም አንድ የወጣ ማስታወቂያ አይታ ለመወዳደር መድፈሯ ለዛሬው ስኬቷ ረድቷታል።«አስታውሳለሁ። በፖስታ ቤት ነበር የተወሰኑ ፎቶዎች አድርጌ የላኩት። ከዛ ወዲያው ከ 25 ሰዎች መካከል ተካተሻል ብለው ነገሩኝ። የመጀመሪያውን ፋሽን ሾው ሳሳይ ምንም እውቀቱ አልነበረኝም። ብሔራዊ ቲያትር  የተካሄደ ትልቅ ዝግጅት ነበር። በእድሜም ትንሿ ነበርኩ። ግን ሚስ ቲን-ኤንጀር ተብዬ ሁለተኛ ወጣሁኝ። ከዛ ውድድር በኋላ ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ገብቼ ሞዴሊንግ ተማርኩኝ። »
እሷም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትላልቅ የሞዴሊንግ ስራዎችን ለማግኘት በቅታ ነበር።  ይህንንም ስራ ለአራት ዓመት ያህል ገፋችበት። «መጀመሪያ ላይ ሚስ ዩንቨርስ ላይ ነበር የተወዳደርኩት 2ኛ ወጥቼያለሁ። ትልቅ ውድድር ነበር። ሌላ ደግሞ ሀገር ውስጥ ትላላቅ ዝግጅቶች ላይ ሰርቻለሁ። ሂልተን፣ ሸራተን፣ የታላቁ ሩጫ ላይ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰርቻለሁ።» 

«ሞዴል መሆን የምፈልገውን ስራ ከመስራት አላገደኝም»

የሞዴሊንግ ስራ ግን መስጋና ሁሌም ለመስራት ያለመችው ስራ አልነበረም።  ህልሟ ጫማ ማምረት ነበር። ይህንንም እውን ለማድረግ ከዜሮ መጀመር ነበረባት።  ለፋሽን እና ዲዛይን ያላት ፍላጎት ስራዋን ጎን ለጎን ለማስኬድ በወቅቱ ረድቷታል። «ሁለቱ ስራዎች የተለያዩ ስራዎች ናቸው። ሞዴል የሆነ ሰው ያኛውን ስራ መስራት አይችልም ተብሎ ነው የሚታሰበው። እኔ ደግሞ ሞዴሊንጉን እየሰራሁ ይኼኛውንም እሰራ ነው። ያው አንድ ጫማም ሆነ ሁለት እቤት በእጅ እሰራ ነበር። ከዛ ግን ወንድሜንም ፣ እህቴንም እዚህ ስራ ላይ አካተትኳቸው። »
ምስጋና ዛሬ ከራሷ ፣ ከወንድምና እህቷ አልፋ 30 ለሚሆኑ ተቀጣሪ ሰራተኞች እንደተረፈች ነግራናለች። ከ10 ዓመት በፊት የመጀመሪያዎቹን ጫማዎች በእጇ መስራት ስትጀምር ከእህቷ ጋር ሁለት ሰዎች ብቻ መቀመጥ የሚችሉበት ተለጣፊ ሱቅ ውስጥ ሆና እንደነበር እያስታወሰች። « ሰው ለመቅጠር አቅም ያዳበርኩት ከብዙ ዓመት ልፋት በኋላ ነው። እንደዚህ አይነት ስራ ላይ ሴቶች ተሰጥዎ አላቸው፤ ከወንዶች ፅናት አላቸው ብዬም በራሴ አምናለሁ። እና ከፍ ያለ የጉልበት ስራ የሚጠይቀውን ነገር ወንዶች እየመጡ ያግዙናል። በተረፈ ግን አብዛኞቹ ሰራተኞቼ ሴቶች ናቸው።  ማስጋና ጫማ አሁን ላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉት። አዲስ አበባ መሀል ከተማ ላይ ነው የሚሰራው። መንግሥት ለአነስተኛ እና ጥቃቅን ብሎ የሰራቸው ፎቆች አሉ። እዛ ውስጥ ነው እየሰራን የምንገኘው። »

ምስጋና ገ/እግዚአብሔር
ምስጋና ገ/እግዚአብሔር ምስል Privat

ምስጋና ለምን የስራ ልምድ የሌላቸውን ሴቶች ትቀጥራለች?

ምስጋና ለምን ሴቶች ላይ አተኩራ እንደምትሰራም ገልፃልናለች።  አባት እና እናቷ በልጅነቷ ነው የተለያዩት ። « እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ። ታላቅ ወንድም እና ታላቅ እህት አሉኝ። እናት እና አባቴ ሲለያዩ ያልተረጋጋ ህይወት ነው የነበረኝ። እናቴ ስራም ሆነ መተዳደሪያ አልነበራትም። ሁል ጊዜ ያ ያሳስበኝ ነበር። እሷ በጣም ስትቸገር እኔና እህቴ ወደ አባቴ እንሄዳለን። እና ኑሮ ጫን ሲልባት ወደ ክፍለ ሀገር አባቴ ጋር እየሄድን እየተመላለስን ነው ያደግነው። እና እሱም ነው እንድጠነክር ያደረገኝ። ምንም ቢሆን እንደ እናቴ መሆን የለብኝም ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። የገንዘብ ተፅምኖ ምን ማለት እንደሆነ ገና ከልጅነት ገብቶኝ ነው ያደኩት » ስለሆነም ሴት ልጅ የራሷ የሆነ የገቢ ምንጭ ሊኖራት ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አላት። ይህንንም ለማበረታታት ምስጋና ችሎታ ያላቸውን ሴቶች  ብቻ ሳይሆን ልምዱ የሌላቸውንም አሰልጥና እንደምታሰራ ትናገራለች። «የግድ ሙያተኛ የሆኑትን ብቻ አይደለም ወደ እኛ ድርጅት የማስገባው። ምንም የማይችሉ ልጆች ብዬ እለጥፋለሁ። እነሱን እያሰለጠንኩ የማብቃት ስራ ነው። የእኔን ተሞክሮ እነግራቸዋለሁ። እና ብዙ ልጆች አሉ የእኔን ፈለግ የተከተሉ። »
ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ችግርም በስራው እንድገፋ እንዳበረታታት የምትናገረው ምስጋና «ራሴን ለውጬ ቤተሰቤን ማገዝ አለብኝ የሚለው ሀሳብ ሁሌም በአዕምሮዋ ነበር። ይህም በሂደቷ የሚገጥሟትን ፈተናዎች ለመቋቋም ረድቷታል። « እንዴት ይህንን ስራ ትሰሪያለሽ?  ፅድት ብለሽ የሞዴሊንግ ስራ ይሻልሻል የሚሉ ብዙ ልክ ያልሆኑ አስተያየቶች ነበር። ብዙ ሰዎች እየቀለድሽ ነው ይሉኝ ነበር። የምሰራበት ቦታ መጥተው የሚያዩም ነበሩ። ያን የመሰለ መልክ እና ቁመና ይዘሽ እንዴት እዚህ ተቀብረሽ ትሰሪያለሽ ይሉኝ ነበር። እና ብዙ ሰው አስተያየቱ ልክ አልነበረም። »

ምስጋና ጫማ
«ጫማዎችን የምንሰራው አሮጌ ተብለው በሚጣሉ የመኪና ጎማዎች እና ቆዳ ነው ግብዓታችን። »ትላለች መስራቿ ምስጋናምስል Privat

ምስጋና ጫማ

«ምስጋና ጫማ » ወደፊት ትልቅ ድርጅት ሆኖ ማየት እና ብዙ ሴቶችን ብቁ ማድረግ የ 33 ዓመቷ ወጣት ምኞት ነው።  ስኬታማም ለመሆን ወደ ጫማ ስራው ከገባች በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ሙያዊ ድጋፍ ለማግኘት አጫጭር የትምህርት ኮርሶች እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ወስዳለች።  «ምስጋና ጫማ»  የምርቷ መለያ ነው። « ጫማዎችን የምንሰራው አሮጌ ተብለው በሚጣሉ የመኪና ጎማ ነው። መርካቶ ይሸጣል። በእጅ የሚሰሩ ነገሮች እና ቆዳ ነው ግብዓታችን። ማስትሹም የሀገር ውስጥ ነው። በተቻለ መጠን ሀገር በቀል ነገር ነው የምንጠቀመው። ዲዛይኑ ላይ የእጅ ስራ ነገሮች እንጠቀማለን። »
ምስጋና ከራሷ ተሞክሮ ተነስታ ሌሎች ወጣቶችን መምከር የምትፈልገው በሚሰሩት ነገር ላይ ፅናት እንዲኖራቸው ነው። « እዚህ ብዙ ነገር አያለሁ። ምንም ሳይኖር ስራ ማማረጥ፣ ስራ የመናቅ፤ ፅናት አለመኖር ነገር አያለሁ። እና ለወጣቶች የማስተላልፈው ነገር  ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ገና ከጅማሬው ተስፋ የምንቆርጥ ከሆነ ግን ውጤቱን ማየት በጣም ከባድ ነው።  በተለይ ደግሞ ሴቶች ከወንዶች ጠባቂ መሆን የለባቸውም። »

ልደት አበበ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር