ኮሮና የቻይና አፍሪቃ ግንኙነትን ቀያይሯል
ቅዳሜ፣ ሰኔ 6 2012ባለፉት ስድስት ወራት የአፍሪቃ እና ቻይና ግንኙነት ፈተና የበዛበት ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን ቻይናዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ድጋፋቸውን ለአፍሪቃ ለማሳየት ፈጣን ቢኾኑም፤ የወረርሽኙ መከሰት የቻይና እና የአፍሪቃ ግንኙነት አንዳንድ ቦታ ላይ እየሠራ እንዳልኾነ ዐሳይቷል።
ቻይና ለአፍሪቃ ትሰጥ የነበረው ግዙፍ ብድር ከእንግዲህ እንደበፊቱ ላይኖር ይችል ይኾናል። ቻይና ውስጥ የሥራ አጥነት ከምንጊዜውም በላይ ከፍ ማለቱ ብሎም የግዙፍ ኩባንያዎች ክስረት ስጋት መጨመሩ ምጣኔ-ሐብቷ እንዲዋዥቅ አድርጓል። ተንታኞች የቻይና ምጣኔ-ሐብት መንገታገቱ የሚቀጥል ነው ባይ ናቸው። እናም አፍሪቃውያን መሪዎች ከፊታቸው የተደቀነው ብርቱ ቀውስን ለማርገብ ይረዳቸው ዘንድ ጥልቅ ወደኾነው የቻይና ኪስ ከእንግዲህ ማማተራቸው ፍሬ አልባ ሊኾን ይችላል ይኾናል። በቻይና እና የአፍሪቃ ሃገራት ነዋሪዎች ዘንድ በኮሮና ወቅት የተከሰተው አለመግባባት እና የዘረኝነት ድርጊትም ሌላኛው ተግዳሮት ነው።
እንዲያም ኾኖ ግን ቻይና በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ዘመን ከአፍሪቃ ልታተርፍ የምትችለው ነገር መኖሩ አይቀርም። የኮሮና ተሐዋሲ ከራሷ ከቻይና ተቀስቅሶ በመላው ዓለም የተዛመተ ቢኾንም የተሐዋሲውን ሥርጭት የተቆጣጠረችው ቻይና አፍሪቃ ውስጥ በርካታ ዜጎቿ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሠማርተው ይገኛሉ። የቻይና አፍሪቃ ፕሮጀክት ድረ ገጽ እና ፖድካስት ሥራ አስኪያጅ ኤሪክ ኦላንደር ቻይና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተፎካካሪዎች ጋር ስትነጻጸር ብዙ ዜጎቿ አፍሪቃ ውስጥ መገኘታቸው የሚያስገኝላትን ጥቅም እንዲህ ይገልጣሉ።
«ቻይና እንበልና ከአውሮጳ እና አሜሪካ ጋር ስትወዳደር የተለየ ቦታ ነው ያላት። ከቻይና ውጪም በርካታ ዜጎቿ ይገኛሉ። ቻይና አፍሪቃ ውስጥ በደንብ የተደላደሉ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት አሏት። እነሱ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።»
ቻይና ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለአፍሪቃ የሰጠችው ርዳታ እና ድጋፍ 280 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል። አብዛኛው ድጋፍ የተገኘው ታዲያ ከግለሰቦች እና ከንግዱ ማኅበረሰብ ነው።
አፍሪቃ ውስጥ የሚኖሩ ቻይናውያን ቊጥራቸው ወደ አንድ ሚሊዮን ይጠጋል። ምናልባት በአኅጉሪቱ አፍሪቃውያን ካልኾኑ ዜጎች በብዛት ቻይናውያን አንደኛ ናቸው። የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭትን ለመቀልበስ ቻይናውያኑ የሚያደርጉት ተሳትፎ ጎላ ብሎ ታይቷል።
በአንጻሩ በዚሁ ወረርሽኝ ወቅት ቻይና ውስጥ የታየው አፍሪቃውያንን የማግለል ድርጊት ሌላ ቊጣን አፍሪቃ ውስጥ ቀስቅሶም ነበር። ቻይናውያን እና አፍሪቃውያን ነዋሪዎች ባለመግባባትም አላስፈላጊ የኾኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። ሚያዝያ ወር ላይ በወደብ ከተማዋ ጉዋንጁ ውስጥ አፍሪቃውያን ላይ ቻይናውያን ነዋሪዎች የዘረኝነት እና የማግለል ድርጊት መፈጸማቸው ቊጣን አጭሮ ነበር። በርካታ አፍሪቃውያን አምባሳደሮች የዘረኝነት ድርጊቱን በወቅቱ በጽኑእ አውግዘዋል። የቻይና መንግሥትም አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል።
በሌላ ጎኑ ቻይና ውስጥ የተፈጸመውን ድርጊት ተከትሎ ቻይናውያን ዜጎች አፍሪቃ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የጥቃት ሰለባዎች ኾነዋል። ሦስት ቻይናውያን ዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ ውስጥ በተቆጡ ሰዎች በደቦ ተገድለዋል። ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንደኛዋ የአንድ ፋብሪካ ባለንብረት ባለቤት ነበረች። ገዳዮቹ አስክሬኗን አውጥተው ከማቃጠላቸው በፊት ሲጎትቱትም ነበር። ግድያው የተፈጸመው የሉሳካ ከንቲባ የፋብሪካው ባለቤት የኮቪድ-19 ስጋት ቢኖርም ሠራተኞቹን ወደቤታቸው ከመላክ ይልቅ ፋብሪካው ውስጥ እንዲቆዩ አስገድደዋል በሚል ባለንብረቱን የሚወቅስ የቪዲዮ መልእክት ፌስቡክ ላይ ካወጡ በኋላ ነበር።
ምንም እንኳን ታዲያ ቻይና ውስጥም ኾነ በአፍሪቃ በአንዳንድ ነዋሪዎች አስደንጋጭ እና አስነዋሪ ድርጊቶች ቢፈጸሙም በኮሮና ወረርሺኝ ትንቅንቊ ግን ቻይና እና አፍሪቃ አኹንም እንደተሳሰሩ ነው። የቻይና መንግሥት ቀጥተኛ ተሳትፎው ቀዝቀዝ ቢልም ቻይናውያን ባለሐብቶች እና ግለሰቦች ለኮቪድ-19 ድጋፍ እያደረጉ ነው።
የቻይና መንግሥት አፍሪቃ ውስጥ መጠነ ሰፊ የሚባል መዋዕለ ንዋይ እና ገንዘብ ቀደም ሲል አፍስሷል። ብዙዎች እንደሚገምቱት አፍሪቃውያን ከውጭ ብድራቸው 20 ከመቶ የሚኾነው ከቻይና የተገኘ ነው። የቻይና ምጣኔ-ሐብት በዋዠቀበት በአኹኑ ወቅት ታዲያ የግል ባለሐብቶች ተሳትፎ መበራከቱ ምናልባትም ቻይና አፍሪቃ ላይ የሚኖራት የወደፊት አቅጣጫ ማመላከቻ ሊኾንም ይችላል። መቀመጫውን ቻይና ቤጂንግ ውስጥ ያደረገው የልማት ተቋም አባሏ ሃናህ ራይደር የሚሰማቸው ያ ነው።
«እኔ የሚሰማኝ በእውነቱ በብርቱ የሚገፋ ኃይል ይኖራል፤ ማለት በተለይ ብድር ሳይኾን መዋዕለ ንዋዩ ላይ። አዲስ ፋብሪካዎችን መገንባት ወይንም ሌሎች ፋብሪካዎችን ወደ ማስፋፋቱም ያዘንብላሉ። ምክንያቱም በዋናነት ቻይና ውስጥ የሚኖረው እድገት ለረዥም ጊዜ ጋሬጣ ይደቀንበታል።»
የቻይና መዋዕለ-ንዋይ አፍሳሾች በዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮጳ የበለጠ ገደብ ስለሚገጥማቸው ሌሎች ቦታዎች ላይ ማተኮራቸው ይበልጥ መጨመሩ የማይቀር ነው። የዛሬ 2 ዓመት ግድም ለአብነት ያኽል ቻይና በዩናይትድ ስቴትስ ገበያ ላይ ብዙ ጥያቄ ሲነሳባት ፊቷን ያዞረችው አፍሪቃ ውስጥ ጀማሪ የስነ ቴክኒክ ፈጣሪዎች ላይ መዋዕለ ንዋዩዋን ማፍሰሱ ላይ ነበር።
በዚህም አለ በዚያ ታዲያ የቻይና እና የአፍሪቃ ትብብር አለመመጣጠኑ የገዘፈ ነው። የንግድ ግንኙነቱ ላይ የታየው ድክመትም ቀላል የሚባል አይደለም። ጉዋንጁ ውስጥ የተከሰተው የዘረኝነት ድርጊት ግንኙነቱ ላይ የፈጠረው አንድምታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አፍሪቃውያን ባለሀብቶች ቻይናውያን ፍልሰተኞች አፍሪቃ ውስጥ እንዳላቸው የምጣኔ ሐብት አቅም እና ብርታት አይስተዋልባቸውም።
«ማየት የምንሻው በቻይናም ኾነ በአፍሪቃ በኩል በፖለቲካ ግንኙነቱ ብቻ ሳይኾን በምጣኔ ሐብቱም ረገድ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ለውጥ እንዲኖር ነው።»
ያም ቢኾን አንዳች ችግር አለ ይላሉ ሃናህ ራይደር። አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት የቻይና መዋዕለ ንዋይን የሚስብ አቅጣጫ አላዳበሩም። የአፍሪቃ ሃገራት ቻይና ውስጥ ያላቸው የሀገር ጎብኚዎች ዘመቻ አንዱ ጥሩ አብነት ሊኾን ይችላል። ዘመቻዎቹ ለአውሮጳውያን ካዘጋጁት እምብዛም የሚለዩ አይደሉም። ይኼ አፍሪቃውያኑ ወደ ውጪ በሚልኳቸው ምርቶች ላይም የሚስተዋል ነው። ስለዚህ እነዚያ ዘርፎች ላይ ለውጥ ያስፈልጋል።
«ከቻይና ጋር ላለን ግንኙነት የምር የኾነ ስልት መንደፍ ያሻል። ቻይና ያላት የተለየ ገበያ ነው። እዚያ ያለውም የልማት አጋር ለየት ያለ ነው። አሳታፊ የኾነ ስልት መንደፍ ያሻል። ከዚያ ግንኙነት ነጥለን ማጉላት የምንፈልገው ምን እንደኾነም ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል።»
ይኽ የኮሮና ወረርሽኝ በአፍሪቃ መቼ እንደሚያበቃ ዐይታወቅም። ቻይና በእርግጥ ወረርሽኙን ድል የነሳችው ይመስላል። የማይታወቀው በቻይና እና አፍሪቃ መካከል ቀድሞ የነበረው ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ተመጣጣኝ በኾነ መልኩ የሚታደስ የመኾኑ ጉዳይ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ቺፖንዳ ቺምቤሉ