ወቅታዊዉ ሁኔታ በምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2010በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከሰሞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ እንደነበር ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ከክልሉ ነዋሪዎች አንዱ ይናገራሉ። የተቃዉሞ ሰልፎቹ ተካሄደባቸዋል ያሏቸውን ስፍራዎችም ይዘረዝራሉ።
«ተቃዉሞ ,,, ተደረገ፣ ኤረር ተደረገ፣ ሺኒሌ ተደረገ፤ መልካጀልዱም ሰምቻለሁ ገና አረጋግጣለሁ፤ አዲጋላ ተደረገ፤ ግን አጠቃላይ ኢሳዎች የሚኖሩበት ቦታ ተቃውሞው አለ ማለቴ ነው።»
በተለይ ካለፈው ዓርብ አንስቶ ከድሬደዋ ብዙም በማትርቀው ሽንሌ ዞን የተቃውሞው እንቅስቃሴ መቀጠሉንም አስረድተዋል። የተቃውሞ መንስኤ ያሉትን ደግሞ እንዲህ ያስረዳሉ።
«ሕዝቡ ምንድነው የሚፈልገው ተሀድሶ የሚባል ነገር አለ፤ የእኛ ዞን ሲቲ ዞን የሚባለው ወይም ሽኒሌ ዞን አጠቃላይ ከደወሌ እስከ ሚሌ፤ እና ሕዝብ ምንድነው የሚፈልገው በሕገ መንግሥቱ መሠረት እነሱ የመረጡትን ልጆች እንዲያስተዳድሩ ነው የሚፈልገው። አብዲ ኢሌ ምንድነው ያደረገው ራሱ ምንድነው የሚባል ተሀድሶ አመጣ እና የእኛ ሀገር ልጆች ከሀገራችን ወሰደ ወደሌላ ወሰደና ተበታተኑ ማን ነው የሚያስተዳድረው ሲቲ ዞን ወይም ሽኒሌ ዞን የአብዲ ኢሌ ሰዎች ናቸው። እና እነዚህ ሰዎች ሥርዓት የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ሕገ መንግሥቱም የማይፈቅደው ነው። ሥርዓት የሌላቸው ፣ ሰው ይበድላሉ ፣ «ኮራፕሽን ሃይ ነው» ለብዙ ዓመታት ሕዝቡ ተማረረ፤ እምቢ አለ ዛሬ።»
ሁለት አዛውንትን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ታስረው ወደጅጅጋ መወሰዳቸውንም ይናገራል። ለደይቸ ቬለ በዋትሰአፕ አስተያየት ከላኩልን አንዱ፤ ከዝርዝር ቅሬታቸው ከፊሉ
«የኢትዮ ሶማሊ ክልል ህዝብ እኮ አይደለም ፊደል ያልቆጠረው የተማረው ህዝብ ላይ እንኳን በደል ጭቆና ሰብአዊ እና ዲሞክራሲ መብት ጥሰት ኧረ ስንቱ ይፈፀምበታል። በየወሩ በአማካይ እስከ 12 % ያህል ከደሞዛችን ያለ ምንም ሪሲት ይቆረጣል። payroll አሰራራቸውም ሕገ ወጥ ነው። ሁሌ በየወሩ ምን ያህል እንደሚደርሰን አናቅም። አንዳንዴ እንኳን ለምን እንደሚቆረጥ አናቅም። ባለ ስልጣናት ልጆቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩበት ሰርግ እና ህክምና ወጭ የሚፈጽሙበት፣ ቪላ ቤት የሚሰሩበት፣ መኪና የሚገዙበት የህዝብን እና የመንግስትን ገንዘብ በድብቅ ሳይሆን በግልጽ በመጠቀም ነው።» ይላል። ሌላኛው የሶማሌ ክልል ነዋሪ መሆናቸዉን የተናገሩ እና ማንነታቸውን ለመግለፅ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ያሳሰቡን ደግሞ በሶማሌ ክልል ለተፈጠረው የሕዝብ ተቃውሞ መንስኤ ነው ያሉትን ተመሳሳይ ችግር ያጠናክራሉ።
«በአካባቢዉ የተፈጠረው ምን መሰለሽ በዘር የተከፋፈለ ነገር አለ በዚያ ጉዳይ ነው የሚሳተፉት። አሁን ከነበረው ትንሽ ተረጋግቷል።» ዛሬ ምርጫ ተካሂደዋል የሚሉ ዜናዎች ወጥተዋል፤ ያ ምርጫ ምናልባት መረጋጋት አምጥtt።ል ብለው ይገምታሉ? « አይ ቀጥታ ሰውየው ከስልጣን ከወረደ መረጋጋት ይመጣል ዋናው የሰውየው ችግር ነው። ምክንያቱም በአጠቃላይ የእሱ የሆኑ ሰዎች ናቸው ስልጣን ላይ ያሉት እና የሀብት ክፍፍል የሚያሚገኙት እነዚያ ሰዎች ብቻ ናቸው እንጂ ሌሎች የሀብቱ ተጠቃሚ አይደሉም።»
ጉዳዩን በጎሳዎች መካከል የተከሰተ አለመግባባት የሚያስመስሉት እንዳሉ ሁሉ፤ የአስተዳደር ብልሹነትና አድልዎን እንደሰበብ የጠየቀሱ አስተያየቶችም አሉ። በተለይ ሽንሌ ላይ ለተቀሰቀሰው «ተቃውሞ ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ ለወረዳዎቹ በጀት አለመሰጠቱ፤ የወረዳዎቹ አስተዳደሮች ከሌላ ዞን የመጡ መሆናቸው፤ ከሕግ ውጪ ገቢ መሰብሰባቸው፤ ልዩ ፖሊስ መታወቂያ ከሌላቸው ሰዎች ገንዘብ ይቀበላል እና ችግሩን የሚናገር ሰው ይታሰራል» የሚሉ አቤቱታዎችን የአካባቢዉ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ የላኩት ጥቆማ ይዘረዝራል።
አለ የሚባለውን የችግር መንስኤ ለመረዳት ወደኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኢድሪስ ስማኤል አብዲ የእጅ ስልክ ላይ ደጋግመን ከእሁድ ዕለት አንስተን ብንሞክርም ስልካቸው ስለማይነሳ ማብራሪያ ለማግኘት አልቻልንም። ዛሬ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን ያወጡት ዘገባ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የባለስልጣናት ሹመት እና ሽግሽግ አድርጓል። ምንጮች ለዶይቸ ቬለ እንደጠቆሙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ አብዲሀኪም አጋል በአቶ ሀምዲ አደን አብዲ ተተክተዋል። ሹም ሽሩ በክልሉ የተነሳው ተቃውሞ ያስከተለው ይሁን አይሁን ግን የተነገረ ነገር የለም።
በሌላ በኩል አርባ ምንጭ እና አካባቢው ላይ የሕዝብ ተቃውሞ መነሳቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን መሰራጨታቸው ታይቷል። ሁኔታው ለማጣራት ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመደወል ያገኘናቸው ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የዩኒቨርሲቲዉ ባልደረባ በግቢውም ሆነ በአካባቢው ምንም የተከሰተ አዲስ ነገር እንደሌለ እና ሰላም መሆኑን ገለፁልን።
በዚህ አላበቃንም ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ደወልን። ኃላፊዉ አቶ ሰሎሞን ኃይሉ አጣርተው ከደቂቃዎች በኋላ እንድንደውል በተሰጡን ቀጠሮ መልሰን ስናገኛቸው አርባ ምንጭ ላይ ተፈጠረ የተባለው በተሽከርካሪ አደጋ የሰው ሕይወት ከማለፉ ጋር የተገናኘ ነው በማለት አብራርተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ