ትግራይ የገባው የሻዕቢያ ጦር «ከፕሪቶርያ ውል በኋላ ከአብዛኛው ቦታ እንዲወጣ ተደርጓል።»
ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016በኤርትራ ሠራዊት የተያዙ ቀሪ አካባቢዎች ለመለየት እና መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር አብርሃም በላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለሀገር ውስጥ የመንግሥት መገናኛ ብዙሐን በትግርኛ በሰጡት ቃለመጠይቅ ከፌደራል ሐይሎች ውጭ የሆኑና ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ያሉ ታጣቂዎች የማስወጣት ሥራም እየተከወነ መሆኑ ገልፀዋል።
ለመንግሥታዊ የቴሌቭዥን ጣብያ ኢቲቪ በትግርኛ ቋንቋ ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ቃለመጠይቅ የሰጡት የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፥ በተለይም ከትግራይ በኩል በፌደራል መንግሥቱ ላይ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮችን ዳሰዋል። ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ፥ አሁንም በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ናቸው ተብለው ስለሚነሱ በትግራይ በኩል ያሉ የኢትዮጵያ ግዛቶች ማብራርያ የሰጡ ሲሆን፥ ከጦርነቱ መቆም በኋላ የኤርትራ ሠራዊት ከአብዛኛው የትግራይ ክፍል ቢወጣም፥ የቀሩ ቀበሌዎች ለመለየት ፌደራል መንግሥቱ የክልሉ አስተዳደር በጋራ እየሠሩ ስለመሆኑ አንስተዋል።
«ወደ ብዙ የትግራይ አካባቢዎች የሻዕቢያ ሐይል ገብቶ ነበር። ከፕሪቶርያ ውል በኋላ ከአብዛኛው እንዲወጣ ተደርጓል። አሁንም የቀሩ ቦታዎች አሉ። በግምገማም አይተነዋል። በግምገማ ካየነው በኋላ የቀሩ ቦታዎች መሬት ላይ ተወርዶ፥ ከፌደራል እና ከክልል በመሆን፥ የትኞቹ የትግራይ ቀበሌዎች፥ የሀገራችን መሬት ነው የሻዕቢያ ሐይል ያለበት፣ አጣርታችሁ በዝርዝር ይቅረብ መፍትሔ እንሰጥበታለን ብለን እየሠራን ነው» ብለዋል ዶክተር አብርሃም በላይ።
ከዚህ ውጭ የጦርነቱ ተፈናቃዮች መልሶ ወደ ቀያቸው ለመመለስ የፌደራሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ ስለመሆኑ በአፅንኦት የተናገሩት መከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ፥ የእስካሁን ተፈናቃዮች የመመለስ እንቅስቃሴ በተያዘለት ጊዜ ባይሳካም፥ ጥረቶች መቀጠላቸው አንስተዋል። «አወዛጋቢ ቦታዎች» ባልዋቸው አካባቢዎች ያሉ ከፌደራል መንግሥት ውጭ የሆኑ ታጣቂዎች የማስለቀቅ ሥራም እየተከወነ ስለመሆኑ ሚኒስቴሩ ተናግረዋል።
ከፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም ጋር በተያያዘ አስተያየታቸውን የሰጡት መከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፥ በውሉ መሰረት የቀሩ ቢኖሩም በርካታ ጉዳዮች ስለመፈፀማቸውም አንስተዋል። ሚኒስትሩ በተለይም አወዛጋቢ በተባሉ ቦታዎች ያሉ ከፌደራል መንግሥት ውጭ የሆኑ ታጣቂዎች መከላከያ እንደሚያስወጣቸው እየተደረገ ነው ሲሉ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም። ባለፈው ወርሐ ነሓሴ ባስተላለፉት መልእክትም ይህንኑ ብለው ነበር። ይህ እስካሁን ያልተፈፀመበትን፣ ተፈናቃዮች እስካሁን ሳይመለሱ የዘገዩበትን ምክንያት ግን ሚኒስትሩ በግልፅ አላስቀመጡም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ሳምንት የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮች በተገኙበት፥ የፕሪቶሪያውን ውል አፈፃፀም አስመልክቶ ውይይት ሊደረግ ዕቅድ መያዙን የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ገልጿል። በውይይቱም በተለይም ባልተፈፀሙ የውሉ ነጥቦች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል ሲሉ የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ለዶቼቬለ ገልፀዋል።
የሁለት ዓመቱን አስከፊ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም ላይ ከተለያዩ አካላት የተለያየ አስተያየት ይሰጣል። በመቐለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ስትራቴጂካዊ ጥናቶች መምህር የሆኑት ገብረመድህን ገብረሚካኤል፥ ውሉ በሙሉእነት እንዲተገበረ የፌደራል መንግሥቱ ሚና ሊጫወት ይገባል ይላሉ። በቅርቡ መግለጫ አውጥቶ የነበረው በኢንግሊዝ የሚገኝ የኤርትራ ኤምባሲ፥ የኤርትራ ሰራዊት የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ግዛት እንደሌለ መግለጹ ይታወሳል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ