ውይይት፦ አከራካሪው የትምህርት እና ስልጠና ፍኖተ ካርታ
እሑድ፣ ነሐሴ 26 2011በፌደራል የትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት የተረቀቀው “የትምህርት እና ስልጠና ፍኖተ- ካርታ” በሥርዓተ ትምህርት፣ በመማር ማስተማር ሥነ ዘዴ እንደዚሁም በተማሪዎች ምዘና እና ፈተና ላይ ሊቀረፉ ይገባሉ የተባሉ ችግሮች የተለዩበት ነው ተብሏል። ፍኖተ ካርታው በእጩ መምህራን እና ስልጠና ላይ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ያላቸውን ማሻሻያዎችም አመልክቷል።
አዲሱ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አጠቃላይ የትምህርት መዋቅሩን ይቀይራል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት 7ኛ እና 8ኛ ክፍል እንደዚሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል እንደሚሰጥ በፍኖተ ካርታው ተቀምጧል። ከዚህ ለውጥ ጋር በተያያዘ እንዲቀሩ ከተደረጉ አሰራሮች መካከል በምሳሌነት ለመጥቀስ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአንድ አስተማሪ ሁሉንም የትምህርት አይነቶች ማስተማር (self-contained)፣ በ10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እና የሁለተኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርት ይገኙበታል። ይህን እና ሌሎቹንም ምክረ ሀሳቦች የተመለከቱ ታዛቢዎች ይህ ቀድሞ ወደ ነበረው የትምህርት ስርዓት መመለስ እንጂ ለውጥ አይደለም ይላሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ በፍኖተ ካርታው 36 ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች መለየታቸውን አስታውቋል። በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ የተነገረለት ይህ ፍኖተ ካርታ የመጪውን የ2012 ዓመት በመሸጋገሪያነት ከተጠቀመ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል። ሚኒስቴሩ በቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት በአጠቃላይ የትምህርት መዋቅር ላይ ለውጥ የሚደረግባቸውን ጉዳዮች ለህዝብ ይፋ ካደረገ በኋላ ፍኖተ ካርታው መወያያ ሆኖ ሰንብቷል።
ከሰሞኑ በብዛት ሲያነጋግር የከረመው የአማርኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ በፍኖተ ካርታው የቀረበው ሀሳብ ነው። “ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር ይገባቸዋል፤ ሌላ ቋንቋ ሊጫንባቸው አይገባም” የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ትምህርታቸውን “በፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋ” ቢከታተሉ አሊያም ሁሉንም የሚያግባባ ቋንቋን ቢማሩ ተግባቦታቸውን እንዲያጎለብቱ ያግዛል ሲሉ የሚከራከሩም አሉ።
የቋንቋ እና የማንነት ጉዳዮችን የሚያስነሱ፣ ፖለቲካዊ አንደምታ ያላቸውን ጉዳዮች በፍኖተ ካርታው በዚህ ጊዜ ከማካተት ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን የትምህርት ጥራት እንደዚሁም የመምህራንን ትምህርት እና ህይወት ማሻሻል ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባ ነበር የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። የተማሪዎች እንግሊዘኛ ቋንቋ ብቃትን፣ የሳይንስ እና ሂሳብ ትምህርት ተቀባይነትን፣ የተማሪዎች የክፍል ተሳትፎ ማሻሻልን የመሳሰሉ ያለ ውዝግብ ሊከናወኑ የሚችሉ ነገሮችን ቅድሚያ መስጠት እንደሚቻልም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
በሳምንታዊው የ“እንወያይ” መሰናዷችን ትኩረት ጎራ ለይቶ ሲያከራከር የሰነበተውን የቋንቋ ጉዳይ እና ሌሎችም ፍኖተ- ካርታውን የለውጥ ምክረ ሀሳቦች እንመለከታለን። የውይይቱ ተሳታፊዎች አቶ ከበደ ሶርሳ፣ በአምቦ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና ማበልጸጊያ ዳይሬክተር፣ ሲያኔ አንለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስርዓተ ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ እና አቶ ሰለሞን ወንድሙ የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ ናቸው።
ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ተስፋለም ወልደየስ