1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዛፎችን መትከል እና መጠቀም

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 8 2010

በየዓመቱ የክረምት ወራት በመጣ ቁጥር ችግኝ የመትከሉ ልማድ ይታያል። ብዙዎችን የሚያሳስባቸው ችግኙ ያለመተከሉ ሳይሆን ችግኞቹ ከምን እንደደረሱ የመከታተሉ ነገር እጅግም መሆኑ ነው። በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ ችግኝ ማፍላቱም ሆነ መትከሉ ገቢ ማስገኘት መጀመሩ ጥቂት የማይባሉትን እያነቃቃ መሆኑ ይታያል።

https://p.dw.com/p/33ACC
Tansania Projekt Baumpflanzung Reduzierung Karbondioxid
ምስል DW/V. Natalis

ችግኞች ተንከባካቢ እንዲያገኙ የኅብረተሰቡን ትኩረት መሳብ ያሻል፤

በመጤው እምቦጭ አረም ከተወረረው የጣና ሐይቅ አቅራቢያ የምርምር ሥራ ከሚያከናውኑት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት በአካባቢና የደን ምርምር ተቋም ባልደረባ አቶ አዱኛው አድማስ ከሰሞኑ ወደ ጎርጎራ በመሄድ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ኅብረተቡን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል። በዚህ ስፍራ ችግኝ ለመትከል ያነሳሳቸው ምክንያትም አለ። አቶ አዱኛው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሀገር በቀል እና በርከት ያለ የደን ክምችት ይታያል። ይህ የሆነውም ኅብረተሰቡ ከእምነቱ ጋር በተገናኘ ለሚከናወነው ነገር ጥንቃቄ በማድረጉ ነው። እሳቸው እና ባልደረቦቻቸው በጎርጎራ ደሴት ላይ የተከሏቸው ችግኞችም ስፍራው ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ነት በኅብረተሰቡ በመታጨቱ ጥበቃው ከወዲሁ ለችግኞቹ እየተደረገ ነው። ሌላው እሳቸው ያነሱት ኅብረተሰቡ ኤኮኖሚያዊ ጥቅም ከደኑ ማግኘት መቻሉም ክብካቤ እንዲያደርግ እንደሚያደሚገፋፋው አንስተዋል። የአማራ ክልል የደን ኢንተርፕራይዝ በክልሉ መንግሥት አዋጅ ቁጥር 70 ፤ 2002ዓ,ም የተቋቋመ ንግድ ላይ ያተኮረ የደን ልማት ነው። ይህ ኢንተርፕራይዝ ችግኝ እያፈላ፤ እየተከለ አሳድጎም በምርትነት እንደሚያቀርብም ይናገራሉ። በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማትም ሆነ ድርጅቶች የተተከለውን ሳይጨምር በያዝነው ዓመት ብቻ 4,9 ሚሊየን ችግኝ ተክሏል። ይህ ኢንተርፕራይዝ የራሱ መደበኛ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ቢኖሩትም ወጣቶችን በማደራጀት ችግኝ እንዲያፈሉ ያደርግ እና ከእነሱም ይገዛል። ችግኝ በማፍላቱ ተግባር ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱት ወጣቶች በደብረብርሃን አቅራቢያ ቀይት የሚገኘው አያሌው ግርማ አንዱ ነው። እነ አያሌው በዚህ ዓመት 17 ወጣቶች ሆነው 390 ሺህ ችግኝ ማፍላት ችለዋል። ችግኙንም ለፈላጊዎች ወዲያው አቅርበው በመሸጥ ወጪያቸውን ካጣጡ በኋላ ገቢውን መከፋፈላቸውንም ይናገራል።

Akazien Projekt der Ernährungs- und Landwirtschaftsorganisation FAO
ምስል FAO

ያገኙት ውጤት ስላበረታታቸውም ከመስከረም ወር ጀምሮ ተደራጅተው እና በርከት ብለው የችግኝ ማፍላቱን ተግባር አጠናክረው ለመስራት ማወዳቸውንም ገልጿል። በአሁኑ ጊዜ እንደውም ይላል ወጣቱ ጥሩ ገቢ ከደኑ ማግኘት በመቻሉ እርሱና ባልደረቦቹ በሚኖሩበት አካባቢ አርሶ አደሩም በፍላጎቱ ችግኝ ወደ መትከሉ ላይ አተኩሯል። ዘንድሮ የሕዳሴው ግድብ በደለል እንዳይ ሞላ በሚል የችግኝ ተከላ በተለያዩ አካባቢዎች መደረጉን የሚያመለክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው። የደን ተመራማሪዉ አቶ አዱኛው የተተከሉት ችግኞች የኅብረተሰቡን ትኩረት እንዲያገኙ እንዲህ ያሉ ስልቶች እንደሚጠቅሙ ጠቁመዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ