1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በምክክር መድረኮች የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን መለየትና አጀንዳ ማሰባሰብ ጀምረናል።»

ሰኞ፣ ግንቦት 21 2015

ኮሚሽኑ ወደፊት በሚካሄዱ የምክክር መድረኮች የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን መለየትና እና አጀንዳ ማሰባሰብ መጀመሩን አስታወቀ ፡፡የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ በመጀመሪያው ዙር በአራት ክልልች ፣ በቀጣይ ደግሞ በተቀሩት ክልሎች እንደሚካሄድ ዛሬ በሀዋሳ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሦስት የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4Rw6a
Äthiopien Kommission für den nationalen Dialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

«በምክክር መድረኮች የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን መለየትና አጀንዳ ማሰባሰብ ጀምረናል።»ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን

በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች አጅግ መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ሥምምነት እንደሌላቸው ይነገራል ፡፡ “ ሊህቃኑ እና ፖለቲከኞቹ “  ከታሪክ እስከ ሠነደቅ ዓላማ ሕገ መንግሥት እስከ አስተዳደር ወሰኖች ከሚስማሙባቸው ይልቅ የማይግባቡባቸው ጉዳዮች ይበዛሉ ፡፡ የአገሪቱ መንግሥት ለአለመግባባት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል ያለውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአንድ ዓመት በፊት ገደማ በማቋቋም ወደ ሥራ አስገብቷል ይገኛል ፡፡ 

የተሳታፊዎች ልየታ እና የአጀንዳ መረጣ  
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ለሚካሄዱ የምክክር መድረኮች የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን የመለየትና እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን አስታወቋል ፡፡ዛሬ በሀዋሳ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሦስት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በቀጣይ ለሚካሄዱ የምክክር መድረኮችን የሚካፈሉ ተሳታፊዎችን የመለየትና እና አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን አስታወቀዋል ፡፡ ኮሚሽኑ ከአንድ ዓመት በላይ ከሆነው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በኋላ አሁን ላይ ወደ ዋናው የምክክር ተግባር እየገባ ይገኛል ያሉት ከኮሚሽነሮቹ አንዱ ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ “ የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ በመጀመሪያው ዙር በአራት ክልሎች የሚከናወን ይሆናል ፡፡ እነሱም የሲዳማ ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፣ የሐረሪ ክልሎች እና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ናቸው ፡፡ ሥራው በነገው ዕለት ከሲዳማ የሚጀመር ይሆናል፡፡ ከክልሉ 37 ወረዳዎች የተወከሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በጋር ይገናኛሉ ፡፡ በሂደቱም  አለን የሚሏቸውን አጀንዳዎች የመለየት ተግባር ይከናወናል ፡፡ በቀጣይ በተቀሩት ክልሎች ተመሳሳይ የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ የሚከናወን ይሆናል “ ብለዋል፡፡

Äthiopien Kommission für den nationalen Dialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አዳዲስ ፊቶች 
በኢትዮጵያ የሚነሱ አገራዊ ጉዳዮች ከብዙሃኑ ድምፅ ይልቅ በፖለቲካኞ እና አክቲቪስት በሚባሉ ግለሰቦች የሚዘወሩ ናቸው የሚሉ ብዙዎች ናቸው ፡፡  አሁን ኮሚሽኑ የሚያካሂደው ምክክር ምን ያህል ከእነዚህ አካላት ተፅኖ የጸዳ ሊሆን ይችላል የሚለው አሁንም የብዙዎች ሥጋትና ጥርጣሬ እንደሆነ ይገኛል ፡፡ በዛሬው የሀዋሳ ጋዤጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት ሌላኛው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ተገኔወርቅ ጌቱ  ግን ይህ ሥጋት ሊሆን አይገባም ይላሉ ፡፡ ፖለቲካኛውና አንቂው በሂደቱ ሊሳተፍ ይችላሉ ነገር ግን ማዘዝ / dictate /  ማድረግ አይችሉም ያሉት ዶክተር ተገኔ “ አጀንዳው የሊህቃኑ ሊሆን የሚችልበት ዕድል የጠበበ ነው ፡፡ ከዛ ይልቅ ገበሬው ፣ ወጣቱ ፣ ሴቱ አካል ጉዳተኛው የተለያየ ሃይማኖት ፣ የተለያያ ብሄር ያላቸው ሰዎች የሚሳተፉበት ነው ፡፡ ሊህቃኑና ፖለቲከኖች አስተዋፅዎ ማድረግ ይችላሉ ፡፡ ነገር ግን ሂደቱ ሁሉን አቀፍ / inclusive  / ሥለሆነ ተፅኖ ሊያደርጉ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ የለም ፡፡ ከአንድ መቶ አሥር ሚሊየን በላይ ህዝብ አንድ ሚሊዮን ህዝብ በማይሞላ ክፍል ውሳኔ ሚሰጥበት ሁኔታ አይኖርም “ ብለዋል ፡፡  

የትግራይ ክልል እስከአሁን ለምን ወደ  ምክክሩ አልመጣም ? 
በሀዋሳው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋዜጠኞች ከተነሱት ጥያቄ መካከል የትግራይ ክልል እስከአሁን በሂደቱ ለምን አልተካተተም ? የሚለው አንዱ ነው ፡፡ ትግራይ ክልል በተጨባጭ ምክንያቶች  ወደ ኋላ የቀረበት ሁኔታ ነበር ያሉት ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዱ ዶክተር ዮናስ አደይ “ አሁን ግን ሂደቱን ለመጀመር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ምለሽ እየጠበቅን እንገኛለን ፡፡ ለዚህም ወደ ክልሉ በመጓዝ ከአስተዳደሩ ጋር ገንቢ ውይይቶችን አድረገናል ፡፡ በቅርቡ ሥራችንን እንጀምራለን የሚል እምነት አለን “ ብለዋል  ፡፡  
ሸዋንግዛው ወጋየሁ  

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ