1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃድያ ዞን መምህራን እና ሐኪሞች የደሞዝ ጥያቄ ከምን ደረሰ?

ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2016

አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በሥራ ማቆም አድማ ላይ የሰነበቱት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን በሦስት ወረዳዎች የሚገኙ መምህራንና ሀኪሞች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። መምህራንና ሐኪሞቹ ከትናንት ጀምሮ ወደ ሥራ መመለስ የጀመሩት ውዝፍ የሦስት ወራት ደሞዝ እንዲከፈላቸው ላቀረቡት ጥያቄ ቢያንስ የሁለት ወራት ክፍያው ተፈጻሚ በመሆኑ ነው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4ZadB
ፎቶ፤ ሆሳዕና ከተማ
አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በሥራ ማቆም አድማ ላይ የሰነበቱት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን በሦስት ወረዳዎች የሚገኙ መምህራንና ሀኪሞች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። ፎቶ፤ ሆሳዕና ከተማምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የመንግሥት ሠራተኞች ጉዳይ

ላለፈው አንድ ወር በሥራ ማቆም አድማ ላይ የሰነበቱት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን በሦስት ወረዳዎች የሚገኙ መምህራንና ሀኪሞች ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። በአድማ ላይ የነበሩት በዞኑ በምሥራቅ ባድዋቾ ፣ ምዕራብ ባድዋቾ እና ዱና ወረዳዎች ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙትና በሺህዎች የሚቆጠሩት መምህራን እና ሀኪሞች ናቸው። የአካባቢው አስተዳደር ከነሐሴ ወር ጀምሮ መክፈል የሚገባውን የሠራተኞች ወርሃዊ ደሞዝ አለመክፈሉ ለሥራ ማቆም አድማው ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።

ወደ ሥራ መመለስ

መምህራኑና ሐኪሞቹ ከትናንት ጀምሮ ወደ ሥራ እየተመለሱ የሚገኙት ከአንደ ወር የሥራ ማቆም አድማ በኋላ ነው። ሠራተኞቹ ወደ ሥራ መመለስ የጀመሩት ውዝፍ የሦስት ወራት ደሞዝ እንዲከፈላቸው ላቀረቡት ጥያቄ ቢያንስ የሁለት ወራት ክፍያው ተፈጻሚ በመሆኑ ነው ተብሏል።

የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ የመምህራን ማህበር ሊቀመንበር መንግሥቱ ገዶሬ  በወረዳው መምህራን ወደ ሥራ ተመልሰው ትምህርት መጀመሩን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል። በወረዳቸው በአርባ አምስት ትምህርት ቤቶች ከሚገኙ መምህራን ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት መካሄዱን የጠቀሱት የማህበሩ ሊቀመንበር «አሁን የነሀሴ እና የመስከረም ደሞዝ ክፍያ ተፈጽሟል። ቀሪውን የጥቅምት ወር ደግሞ እየሠራን ለመጠየቅ ከሥምምነት ላይ ደርሰናል። በዚህም ከትናንት ጀምሮ ወደ ሥራችን ተመልሰናል። በተለይ ዛሬ ደግሞ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሥራው እየተካሄደ ይገኛል» ብለዋል።

እፎይታ

አቶ በቀለ ዎርዶሎ በምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ  የአንጅሎ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጆች ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። አቶ በቀለ በወረዳቸው ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ላለፈው አንደ ወር የተካሄደው የሥራ ማቆም አድማ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጉዳት ላይ መጣሉን ይናገራሉ ። « በአድማው ምክንያት ትምህርት በመዘጋቱ ልጆቻችን እቤት ለመዋል ተገደው ነበር» የሚሉት አቶ በቀለ «በተለይ ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች ወደ ኋላ እንዲቀሩ ምክንያት ሆኗል። በተመሳሳይ ሁኔታ የህክምና ተቋማት በአድማው ምክንያት በመዘጋታቸው ነዋሪው ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል። አሁን ግን የትምህርትም ሆነ የጤና ተቋማቱ ዳግም ተከፍተው ሥራ በመጀመራቸው እፎይታ አግኝተናል» ብለዋል።

ሃዲያ ዞን ሆሳዕና
ሃዲያ ዞን ሆሳዕና ምስል Hadeya zone communication affairs

ዘላቂ መፍትሄ  

ዶቼ ቬለ ዳግም በተጀመረው ትምህርት ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቃቸውና ሥማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሁለት መምህራን ወደ ሥራ የተመለሱት ጥያቄያቸው በሙሉ ምላሽ በማግኘቱ ሳይሆን ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ በማሰብ ነው ይላሉ። በተመሳሳይ መልኩ በወረዳዎቹ ወደ ሥራ ገበታቸው የተመለሱት የህክምና ባለሙያዎችም እንደመምህራኑ ሁሉ  ወደ ሥራቸው የተመለሱት በምላሹ ረክተው እንዳልሆነ ይናገራሉ። ይልቁንም በህክምና እጦት የሚቸገረውን ነዋሪ ለመረዳት ካደረባቸው የዜግነት ግዴታ የተነሳ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።

በመምህራኑና በህክምና ባለሙያዎቹ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን የወረዳ ፣ የሃድያ ዞን መስተዳድርን እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልየሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ዶቼ ቬለ  ከትናንት ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ የሚሰጥ አካል ግን ሊገኝ አልቻለም።  መምህራንና የህክምና ባለሙያዎቹ ግን ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚስተዋለው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ካላገኘ አሁንም ዞሮ ተመሳሳይ ሁኔታ  ሊያጋጥም  ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል። በቀጣይ የማዳበሪያ ዕዳ በሚል የወረዳውን በጀት ቀውስ ውስጥ የከተተውን ችግር ከበላይ የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር በመነጋገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ሊሰጥ እንደሚገባም ሠራተኞቹ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በአራት አዳዲስ ክልሎች የተዋቀረው የቀድሞው የደቡብ ክልል ቀደምሲል የወረዳዎችን በጀት በዋስትና በማሲያዝ የወሰደውን በቢሊየን ብር የሚቆጠር የአፈር ማዳበሪ ዕዳ በወቅቱ ባለመመለሱ  ዕዳው ወደ አዳዲሶቹ ክልሎች መተላለፉ ይታወቃል። በተለይም በሃድያ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች  ዕዳው  ከወረዳዎቹ በጀት ሲቀነስ የሠራተኞቹን ደሞዝ አብሮ በመቀነሱ ሠራተኞች በየጊዜው ለደሞዝ እጦት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ