1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዝግ ስብሰባ የቀጠለው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2016

ማክሰኞ የተጀመረው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በዝግ ስብሰባ ቀጥቷል። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊትም የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸውን ከጉባኤው ማግለላቸውን በይፋ አስታውቀዋል። ከእነሱ በተጨማሪ ከተለያዩ አካባቢዎች በጉባኤው ሊሳተፉ ይጠበቁ የነበሩ የፓርቲው አባላት በጉባኤው ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

https://p.dw.com/p/4jSXJ
Äthiopien Märtyrerdenkmal in Mekele
ምስል Million Haileselassie/DW

በዝግ ስብሰባ የቀጠለው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ

 እነዚህ ራሳቸውን ከጉባኤው ያገለሉ የህወሓት አባላት እና አመራሮች፥ ጉባኤው የተወሰነ አመራርን ለማጥቃት በችኮላ የተጠራ መድረክ ነው ሲሉ ያወግዛሉ።  

አነጋጋሪ የሆነው 14ተኛው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ፥ ለመገናኛ ብዙሐን ክፍት ከነበረው የትላንቱ የመክፈቻ ስነስርዓቱ በኃላ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ለሁሉም ሚድያዎች ዝግ ሆኖ እየቀጠለ ይገኛል። በጉባኤው መገኘት የነበረባቸው ምክትል ሊቀመንበር፣  በርካታ የማእከላይ ኮሚቴ አባላት ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተባሉ ሌሎች እየተሳተፉ እንዳልሆነ የተገለፀ ሲሆን፥ በዚህ ውዝግብ መሀልም ግን ጉባኤው ቀጥሏል። በተለይም ከትግራይ ደቡባዊ እና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች በርካታ ወረዳዎች በጉባኤው ሊሳተፉ የነበሩ የህወሓት አባላት በጉባኤው ላይ ያላቸው ቅሬታ በመግለፅ ከመድረኩ የቀሩ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል የሆኑ ያነጋገርናቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የማይጨው ከተማ ከንቲባ አቶ የማነ ንጉስ፥ ጉባኤው የተወሰነ ቡድን ለማጥቃት በችኮላ የተጠራ በመሆኑ እሳቸው ጨምሮ በርካቶች ተቃውሞዋቸውን በመግለፅ ከመድረኩ መቅረታቸው ገልፀውልናል።

«ህወሓትን ወደከፋ ችግር የሚያስገባ»

ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው ከፓርቲው ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን ተቃውሞ እየገጠመው ያለ ሲሆን፥ የህወሓት ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን ሊቀመንበር አቶ ተክለብርሃን አርአያ ጉባኤው በተጀመረበት ትላንት ለመገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ፥ 14ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተብሎ የተጀመረው ስብሰባ ህወሓትን ወደከፋ ችግር የሚያስገባ በማለት ጉባኤው አውግዘዋል።

የህወሓት 14ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሰዎች ተሰብስበው
የህወሓት 14ተኛ ጠቅላላ ጉባኤምስል Million Haileselassie/DW

አቶ ተክለብርሃን አርአያ "አንድነታችን ይዘን፣ የፕሪቶርያው ውል  ማእከል አድርገን፣ ለአላዊነታችን አረጋግጠን በተጨማሪም አንድ ላይ በመንቀሳቀስ ሕጋዊ እውቅናችን መልሰን ሊደረግ የሚገባው ነው። ይህ ግን ወደ ቅርቃር ውስጥ የሚያስገባን ነው። ስለዚህ ይህ ተግባብተን ወደ አንድ መንገድ መጥተን ልናደርገው ይገባ የነበረ ነው። ላይ ያለው አመራሩ ብቻ ሳይሆን ታች ያለው አባልም ጭምር መግባባት የፈጠረበት ሊሆን ይገባ ነበር" ብለዋል።

ህወሓት እያካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ምን አሉ?

ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው ተቃውመው ከመድረኩ ከቀሩት መካከል ከሆኑት የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ባሰራጩት ፅሑፍ፥ መደረግ የጀመረው ጉባኤ በጥድፍያ፣ የጋራ መግባባት ሳይደረስበት፣ አደራጀነው ባሉት ኔትዎርክ ይቃወሙናል ያሉት የተወሰነ መሪነት ለማስወገድ ብቻ የሚደረግ ጉባኤ ብለው የተቹት ሲሆን፥ ይህም የከፋ አደጋ የሚፈጥር እና ሊወገዝ የሚገባው ሲሉ ገልፀውታል።

ያነጋገርናቸው የማይጨው ከተማ ከንቲባ እና የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ የማነ ንጉስ፥ ከጉባኤው ራሳቸው ማግለላቸው ትክክለኛ አቋም አድርገው እንደሚወስዱት፥ ፓርቲው ወደ አደገኛ መንገድ እየመሩ ያሉ የህወሓት አመራሮችን ግን መታገላቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጨምሮ ከፓርቲው አባላት እና ከፍተኛ አመራሮች ጭምር ተቃውሞ የገጠመው የህወሓቱ ጉባኤ መች እንደሚጠናቀቅ የተባለ ነገር የለም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ