1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ግጭት ያስነሳው ውዝግብ

እሑድ፣ ነሐሴ 29 2014

በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ነሃሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ማክሰኞ ከማለዳ ጀምሮ የታጠቁ አካላት በጅምላ ንጹሃን ላይ በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 55 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ ይሁንና ከአከባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ጥቃቱን ባደረሱ ታጣቂዎች ማንነት ላይ የሚያወዛግብ አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4GO3p
Äthiopien | Straßenszene in Mendi
ምስል Negassa Deslagen/DW

የሐሙሩ ግድያ እና የተነሱ አወዛጋቢ አስተያየቶች

በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ነሃሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ማክሰኞ ከማለዳ ጀምሮ የታጠቁ አካላት በጅምላ ንጹሃን ላይ በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 55 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡

ይሁንና ከአከባቢው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ጥቃቱን ባደረሱ ታጣቂዎች ማንነት ላይ የሚያወዛግብ አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡

ሰሞኑን አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ተፈናቃዮች “የፋኖ ታጣቂ” ባሏቸው ግድያና መፈናቀል እንደ ደረሰባቸው ሲገልጹ፤ በሌላ በኩል አስተያየታቸውን የሚሰጡ የአማራ ተወላጅ ተፈናቃዮች ደግሞ አስቀድሞ በእለቱ በአገምሳ ከተማ ላይ ግጭት የቀሰቀሱ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ሸነ) የተባሉ ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ፡፡

የአሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ተፈናቃይ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ለአንድ ዓመት ያህል የአከባቢው ማህበረሰብ በፀጥታ ችግር ምክኒያት አስከፊ የተባለ የፀጥታ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ባለፈው እሁድ ነሃሴ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የአከባቢውን ፀጥታ ሲያስከብሩ የነበሩ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት ከከተማዋ መነሳታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው ታጣቂዎች በከተማዋ መፈራረቃቸውን ነው የአይን እማኞች የገለጹት፡፡

“እሁድ ማታ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለሌላ ግዳጅ ትፈለጋላችሁ ተብለው ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ መንግስት ‘ሸነ’ ያላቸው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ሰኞ ጠዋቱን ገብተው ከተማዋን ተቆጣጠሩዋት፡፡” አቶ ንጉሴ ባንጃ የተባሉ የአይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት ነው፡፡ የአይን እማኙ አክለውም እንዳብራሩት ታጣቂዎቹ ከተማዋ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ ወደ 59 መሳሪያ ከማህበረሰቡ አስፈትተው በዚያው ሰኞ ቀን ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል፡፡

አቶ ንጉሴ አክለው በሰጡን አስተያየታቸው፤ “ማክሰኞ ጠዋት ደግሞ ፋኖ ነን ያሉ የታጠቁ አካላት ወደ ከተማዋ ገብተው ከኦነግ ጋር አብራችኋል በሚል በመደዳው ከተማዋ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ከ15 ሺህ የማያንሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል” ነው ያሉት፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ከኪረሙ ወረዳ ሃሮ ቀበሌ የመጡ ናቸው፡፡

ይሁንና በሌላ በኩል አስተያየታቸውን ከአገምሳ ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ወረዳ የተጠለሉት የአመራ ተወላጆች በሰጡን አስተያየት አስቀድሞ ሰኞ እለት በአገምሳ ከተማ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ኦነግ ሸነ ያሏቸው ታጣቂዎች እገታ በመፈጸማቸው ማክሰኞ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመደወል የድረሱልን ጥሪ በማቅረባቸው ነው የተኩስ ልውውጥ ተፈጽሞ ያስለቀቁአቸው፡፡

ስማቸውን ለደህንነታቸው ብለው ይቆይ ያሉን አስተያየት ሰጪው የመንግስት ጸጥታ አካል እሁድ አመሻሽ 2፡00 ገደማ ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ሰኞ ወደ ከተማዋ ገብተው አከባቢውን የተቆጣጠሩት የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብለው እራሳቸውን የሚጠሩ “ሸነ” የተባሉ ታጣቂዎች ናቸው ብለዋል፡፡

“ታጣቂ ቡድኑ ስድስት ሰዎችን በብሔር ለይቶ ገድሏል” ያሉን እኚው አስተያየት ሰጪ፤ ሰኞ ነሃሴ 23 ቀን 2014 በኖሩበት አገምሳ ከተማ ከታገቱት አንዱ መሆናቸውን እና አጎራባች ኪረሙ ወረዳ ወዳሉ ወደ ቤተሰቦቻቸው ደውለው በተኩስ ልውውጥ ማክሰኞ ጠዋት እንዳስለቀቁዋቸውም አክለው አንስተዋል፡፡

እንደ የአማራ ተወላጅ አስተያየት ሰጪዎች በማክሰኞው ግጭት በአገምሳ ከተማ እስካሁን አስከሬናቸው ያልተነሳ ስለመኖሩም አስረድተዋል፡፡

የአገምሳ ከተማ ተፈናቃዩ አቶ ንጉሴ ግን ‘ፋኖ’ ያሏቸው ከአጎራባች ወረዳ የመጡቱ መላውን የከተማዋ ነዋሪ ላይ ከፍተዋል ባሉት ጥቃት “እንድንፈናቀል ዳርገውናል” ያሏቸው ሃይል ቁጥራቸው የበዛ ነው ይላሉ፡፡

የአመራ ተወላጅ ተፈናቃይ አስተያየት ሰጪው በፊናቸው ከዚህ የሚቃረን አስተያየት ነው የሚሰጡት፡፡ “ከተማዋ ውስጥ የታገቱ አመሮችን ለማስለቀቅ የመጣው ማህበረሰብ ወዲያውኑ ከተማዋን ሲለቅ እስካሁንም ከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሸነ ነው” ሲሉ ነው አስተያየት የሰጡት፡፡

ነዋሪዎቹ ይህን መሰል የፀጥታ ችግር ለነሱ አዲስ ነገር ሳይሆን ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ጊዜያት የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡

በዚሁ በሰሞነኛው የአገምሳ ከተማ ግጭት በኋላም በአከባቢው ላይ የደረሰ የመንግስት የፀጥታ አካል የለም የሚሉት እኚው ተፈናቃዮች አሁንም የበዛ የፀጥታ ስጋት ላይ መሆናቸውን ገልጸው መንግስት እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሰሞነኛው የአገምሳ ከተማ ጥቃት ከጠፋው የሰው ህይወት በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ ተቋማት፣ ከብቶችና የተለያዩ ሃብት ዘረፋ እና ውድመት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ለፀጥታ ችግሩ መከሰት የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች አከባቢውን ለቀው የመውጣት ውሳኔን ይነቅፋሉ፡፡ አስቀድሞም ከአንድ ዓመት በላይ በአከባቢው በቆየው የፀጥታ ችግር በርካታ ሰው ወደ ከተማዋ ተጠልለው እንዲቆዩ እንዳስገደዳቸው በመግለጽም፤ አሁን ላይ ግን በከተማዋ ላይ ባነጣጠረው ጥቃት ነዋሪዎች ወደየጫካው ነፍሳቸውን ለማዳን መሸሻቸው ነው የተብራራው፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአሙሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ታዬ ስለሁኔታው ማብራሪያቸውን እንዲሰጡ ከዶይቼ ቬለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ሳይሰጡ፤ ከህበረተሰቡ ጋር በውይይት ላይ መሆናቸውን በመግለጽ አስተያየታቸውን ሳያጋሩን ቀርተዋል፡፡ ከዚያም በተደጋጋሚ ብንደውልላቸውም ስልካቸው አይመልስም፡፡

ለሆሮ ጉዱሩ የጸጥታና አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ለኦሮሚያ የፀጥታ ዘርፍ እና ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት እንዲሁም ለፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊዎችም ደውለን ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም እስካሁን አልሰመረልንም፡፡

ሰሞኑን የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ባለስልጣናት በሻምቡ ከተማ በየደረጃው ካሉ የመንግስት ሰራተኞች ጋር ባደረጉት ውይይት በአሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ እና ጃርዳጋ ጃርቴ ወረዳ “የአማራ ጽንፈኛ ኃይሎች እና ሸነ” ያሏቸው የታጠቁ አካላት ‘ዘግናኝ’ የተባለ ድርጊት ማህበረሰብ ላይ ፈጽመዋል መባሉን ክልላዊው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን.) ዘግቧል፡፡

መንግስት ‘ሸኔ’ በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ሰሞኑን ከ60 በላይ ንጹሃን የኦሮሞ ነዋሪዎች “በፋኖ ታጣቂዎች” ተገድለዋል ሲሉ በትዊተር ባሰራጩት መረጃ ከሰዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ግድያ ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተዘገቡ ግጭቶች በተለይም በዋናነት የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ በተለያዩ የወለጋ ዞኖች ተዘግበው ያውቃሉ፡፡

የሁማን ራይትስ ዋች እንኳ ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ሰኔ 11 ቀን 2014 የታጠቀ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን ሲገድሉ መንግስት በቂ ጥበቃ አላደረገላቸውም ሲል ወቅሷል፡፡

የ400 ሰዎች ህይወት በቀጠፈው በምእራብ ወለጋው የቶሌ ጥቃት «ማንነታቸው ያልታወቁ» ባላቸው ታጣቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ቢያንስ አምስት መንደሮች ውስጥ መውደማቸውን እና ንብረቶቻቸው መዘረፋቸውን ሁማን ራይትስ ዋች ከሳተላይት ምስል ትንተና ማረጋገጡን ገልጿል።

ከዚሁ የጅምላ ግድያ በኋላም ባለፈው ሃምሌ በቀለም ወለጋ ሃዋ ገላን ቀበሌ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈ ጥቃት መፈጸሙ አይዘነጋም፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ