አርዕስተ ዜና
*ባለፈው ሰኞ በመቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል የቅድመ ካንሰር ምርመራ የተደረገላቸውና በእሥር ላይ ያሉት አቶ ክርስትያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዛሬም ሆስፒታል ሳይወሰዱ መቅረታቸው ተነገረ ። እስረኞቹ ደም እየፈሰሳቸው ሐኪም ቤት አለመሰዳቸው «በሕይወት የመኖር መብትን የሚጣረስ ነው» ሲሉ የእስረኞቹ ጠበቃ ተናግረዋል ።
*በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቡድን «አዲስ» ያለውን የትግል አቅጣጫ እንደሚከተል ዐሳወቀ ።
*በውጭ አገራት የርዳታ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ከ280 በላይ ሠራተኞች ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ መገደላቸው ተገለጠ ።
*ጀርመን ውስጥ ከማኅበረሰቡ ጋር ያልተዋሐዱ ሶሪያውያን ሊባረሩ ይገባል ሲሉ አንድ ከፍተኛ ፖለቲከኛ ተናገሩ ። ጀርመን ውስጥ መቆየት የሚገባቸው የገዛ ወጪያቸውን ራሳቸው መሸፈን የሚችሉ፤ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት የማይሳናቸው እና ጀርመንኛ ቋንቋን የሚያውቁ መሆን ይገባቸዋልም ብለዋል ።
ዜናው በዝርዝር
አ.አ፥ ሥቃይ ላይ የሚገኙት አቶ ክርስትያን ታደለና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ሐኪም ቤት ዛሬም አልተወሰዱም
ባለፈው ሰኞ በመቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል የቅድመ ካንሰር ምርመራ የተደረገላቸውና በእሥር ላይ ያሉት አቶ ክርስትያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዛሬም ሆስፒታል ሳይወሰዱ መቅረታቸው ተነገረ ። ሁለቱም የምርመራ ውጤታቸውን ለማወቅ ለዛሬ ሐሙስ ቢቀጠሩም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ግን «አጃቢ የለኝም» በሚል ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ ሳይወስዳቸው መቅረቱን ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው ተናግረዋል ። እሥረኞችን ወደ ሌላ ቦታ እያዘዋወረ መሆኑን በመግለጽ በአጃቢ እጥረት ምክንያት ሁለቱን ተከሳሾች ወደ ሆስፒታል ያላቀረበው ማረሚያ ቤቱ ሌሎች ተከሳሾችን ግን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይዞ መቅረቡን ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ሰኞ ዕለት ቀረቡ፥ ቁስሉ አለ፥ ደሙም ብዙም ያልደረቀ መሆኑ፣ የሚንጠባጠብ መሆኑ ያንን ቁስሉንም ለማከም ተሞክሮ፤ ከዛ ደግሞ ከፍተኛ የአንጀት ቀዶ ጥገና ለማድረግ ከአንጀታቸው ውስጥ የሚቆረጥ ነገር ተቆርጦ የካንሰር ቅድመ ምርመራ ውጤት ለማወቅ፤ ሁለተኛ አሁንም የሚፈስሰውን ደም በተመለከተ ቁስሉ ለውጥ ያለው ስለመሆኑ ለማወቅ ለዛሬ ቀጠሮ ነበር ። አልወሰዷቸው ። እስረኞችን ከቦታ ቦታ እያዘዋወርን ስለሆነ አጃቢም የለም የሚወስድ መኪናም የለም በማለት ነው መልስ ነው የሰጡት ።»
ተከሳሾቹ ባለፈው ሳምንት የአንጀት ቀዶ ጥገና ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ መቅረዝ ሆስፒታሉ ውስጥ ሆነው እንዲከታተሉ ያልቻሉት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ፈቃድ ባለመስጠቱ ነው ያሉት ጠበቃው ደንበኞቻቸው ዛሬ ሆስፒታል አለመወሰዳቸው «በሕይወት የመኖር መብት ጋር የሚጋጭ» መሆኑን ገልፀዋል ።
«ይኽም በሕይወት የመኖር መብትን የሚጣረስ ነው ። ሰው እኮ በሕይወት እያለ ነው ክስ የሚሰማው ሒደቱም የሚታየው ። መቅደም ያለበት የአቃቤ ሕግ ምሥክር ለምሳሌ ያህል እንደው እጀባ የለንም ቢሉ እንኳን መቅደም ያለበት የአቃቤ ሕግ ምሥክርን ለመስማት እስረኞችን ማጓጓዝ ነው ወይንስ ደም እየፈሰሰው እና ቁስል አለው፤ እንዲሁም ደግሞ የአንጀት ቀዶ ጥገና ለማድረግ ከአንጀት የተቆረጠ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ያለውን ሰው ይዛችሁ እንድትመጡ ነው መቅደም ያለበት? እኔ ይኼ ምክንያታዊ አይደለም ነው የምለው ።»
ሁለቱ እስረኞች አዋሽ አርባ እና ሰመራ በእሥር በቆዩበት ሰዓት በደረሰባቸው የአንጀት ድርቀት በተገቢ ሕክምና እጦት የተነሳ ለከፍተኛ ሕመም እና ሥቃይ መዳረጋቸው ተገልጧል ።
መቐለ፥ በደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ሕወሓት ቡድን «አዲስ» የትግል አቅጣቻ እከተላለሁ አለ
በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቡድን «አዲስ» ያለውን የትግል አቅጣጫ እንደሚከተል ዐሳወቀ ። ቡድኑ «ሰላማዊ እና አዲስ የትግል ስልት» ያለውን መንገድ እንደሚከተልም የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዐሳውቀዋል ። ያንንም ተከትሎ ይህ የሕወሓት ቡድን፦ «የእምቢታ ዘመቻ» ማስጀመርያ ያለውን የከፍተኛ ካድሬዎቹን ስብሰባ ከትናንት ጀምሮ በመቐለ ከተማ እያካሄደ ነው ። ቡድኑ እንደገለፀው፦ በቀጣይ አጠቃላይ አባላቶቹን በማሳተፍ «የእምቢተኝነት ዘመቻ» ያለውን እንቅስቃሴ ለማድረግ ማቀዱንም ይፋ አድርጓል ። ዘመቻው፦ «እምቢ ለብሔራዊ ክህደት፣ ለአገዛዝ እና ብተና» የሚል መፈክር እንደተሰጠውም የመቐለ ወኪላችን ዘግቧል ። በዘመቻው ምን እንደሚደረግ ግን በዝርዝር የተባለ ነገር የለም ። በሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የሕወሓት ቡድን አቶ ጌታቸው ረዳ ከሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከገባ በርካታ ጊዜያት ተቆጥሯል ።
ቤርሊን፥ ከ280 በላይ የርዳታ ሠራተኞች በውጭ አገራት ሥራ ላይ ተገድለዋል
በውጭ አገራት የርዳታ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ከ280 በላይ ሠራተኞች ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ መገደላቸው ተገለጠ ። የጀርመን ቀይ መስቀል ፕሬዚደንት ጌርዳ ሐዘልፌልድት በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፍ የርዳታ ተግባራት ላይ መሠማራት አደገኛ ሁኗል ብለዋል ። በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በርዳታ ተግባር ላይ በተሠማሩበት ከተገደሉት መካከል በርካታ የቀይ መስቀል ሠራተኞች መኖራቸውንም ፕሬዚደንቷ አክለዋል ።
ቤርሊን፥ ከማኅበረሰቡ ጋር ያልተዋሐዱ ሶሪያውያን ሊባረሩ ይገባል ሲሉ አንድ የጀርመን ፖለቲከኛ ተናገሩ
ጀርመን ውስጥ ከማኅበረሰቡ ጋር ያልተዋሐዱ ሶሪያውያን ሊባረሩ ይገባል ሲሉ አንድ የጀርመን ከፍተኛ ፖለቲከኛ ተናገሩ ። የጀርመን የምርጫ ዘመቻ በጀመረበት በአሁኑ ወቅት የሶሪያ ስደተኞች ጉዳይም ዐቢይ ጉዳይ ሁኗል ። የክርስቲያን ዴሞክራቶቹ ፓርቲ (CDU) በምርጫው ከተመረጠ ከማኅበረሰቡ ጋር የተዋሐዱ ሶሪያውያን ጀርመን ውስጥ መቆየታቸውን እንደሚፈቅድ ያልተዋሐዱት ግን እንዲሚያባርር ፍንጭ ሰጥቷል ። የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ የምክር ቤት አባል ዬንስ ሽፓን ስለ ፍልሰተኞች ጉዳይ ትናንት በዶይቸ ቬለ ተጠይቀው ይህንኑ አረጋግጠዋል ። በገዛ ፈቃዳቸው ወደ ሶሪያ መመለስ ለሚፈልጉ ሰዎች ለእያንዳንዳቸው 1,000 ዩሮ ይሰጣቸው ሲሉ ፖለቲከኛው ሐሳብ ማቅረባቸው ጀርመን ውስጥ በአንዳንዶች ዘንድ ትችት አጭሮባቸዋል ። ጀርመን ውስጥ መቆየት የሚገባቸው የገዛ ወጪያቸውን ራሳቸው መሸፈን የሚችሉ፤ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት የማይሳናቸው እና ጀርመንኛ ቋንቋን የሚያውቁ መሆን ይገባቸዋልም ብለዋል ። አንዳንድ ፖለቲከኞች የዬንስ ሽፓን አስተያየት በርካታ ዓመታት ጀርመን በኖሩ ሶሪያውያን ፍልሰተኞች ዘንድ መጻኢ ዕድላቸው ላይ እርግጠኛ እንዳይሆኑ ብዥታ ይፈጥራል ብለዋል ። ሌሎች ደግሞ በጀርመን የሥራ ገበያ ሶሪያውያን የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖ የዘነጋ አስተያየት ሲሉ ተችተውታል ። በጀርመን ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ባስገደደው የባለፈው የፌዴራል ግዛቶች ምርጫ ስደተኛ እና ፍልሰተኛ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ (AfD)ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው በስደተኞች ጉዳይ በያዘው አቋም ነበር ።
ሠንዓ፥ የእሥራኤል የአየር ኃይል የሑቲ ዓማጺያን ይዞታን ደበደበ
የእሥራኤል የአየር ኃይል የሑቲ ዓማጺያን ሚሳይል ካስወነጨፉ በኋላ የመንን በቦንብ ደበደበ ። በእሥራኤል የጦር ጄቶች ድብደባ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል ። እሥራኤል የአየር ድብደባውን ሑቲዎች ለወራት ላደረጉት ትንኮሳ የበቀል ምላሽ ነው ብላለች ። የሑቲ አማጺያንን ትደግፋለች የምትባለው ኢራን የእሥራኤልን የአየር ጥቃት አውግዛለች ። የእሥራኤል የአየር ኃይል የመን ውስጥ ዛሬ ጠዋት ባካሄደው ድብደባ የተገደሉት ሰባት ሰዎች ሣሊፍ የተባለችው የወደብ ከተማ ውስጥ ነው ተብሏል፥ ሁለቱ ደግሞ ራስ ኢሳ በተባለው የነዳጅ ማውጫ ተቋም አቅራቢያ መሆኑ ተዘግቧል ። የአየር ድብደባውን ከመፈጸሙ በፊት የእሥራኤል መከላከያ ኃይል ቢያንስ አንድ ሚሳይል ከየመን መወንጨፉን በራዳር እይታው ውስጥ ማስገባቱን ዐሳውቋል ። የእሥራኤል መከላከያ የመን ውስጥ የሚገኙ የወደቦች እና የኃይል ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ዒላማዎችን አነጣጥሮ መምታቱን ይፋ አድርጓል ።
ቤልግሬድ ፥በሠርቢያ ዋና ከተማ ከጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ጀምሮ የሕዝብ ማጓጓዣ አገልግሎት ነጻ ሊሆን ነው
በሠርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ ከጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ጀምሮ የሕዝብ ማጓጓዣ አገልግሎት ነጻ እንደሚሆን ይፋ ሆነ ። አገልግሎቱ ነጻ የሚሆነው የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ ነው ተብሏል ። በዚህም መሠረት ከጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ጀምሮ ማንም ሰው ለህዝብ ማጓጓዣዎች አይከፍልም ተብሏል ። 1,7 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ከተማ አውሮጳ ውስጥ የምድር ለምድር የባቡር አገልግሎት ከሌላቸው ጥቂት ከተሞች አንዷ ናት ።ከዚህ ቀደም አውሮጳ ውስጥ ሉክዘምበርግ እና የኢስቶኒያ ዋና ከተማ ታሊንም ተመሳሳይ ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወቃል።