የሐምሌ 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሐምሌ 29 2016የፓሪስ ኦሎምፒክ ቀጥሏል ። በዐሥር ሺህ ሜትር የወንዶች ፉክክር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ኢትዮጵያ በሴቶቹ አምስት ሺህ እና ስምንት መቶ ሜትር ፉክክር ምሽቱን ተጨማሪ ሜዳሊያ ትጠብቃለች ። የ37 ዓመቱ ኖቫክ ጄኮቪች የማታ ማታ በሜዳ ቴኒስ ድል ተቀዳጅቷል ። በፓሪስ ኦሎምፒክ የትሪያትሎን ተፎካካሪ ተሳተፉ አትሌቶች ከወንዙ ጋ በተገናኛ ለሕመም መዳረጋቸው ተዘግቧል ። በፓሪስ እና አካባቢዋ ወንዞችን ለማጽዳት ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ መውጣቱ ቀደም ሲል ተገልጦ ነበር ።
የፓሪስ ኦሎምፒክ
በኦሎምፒክ ውድድር ታሪክ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በሲድኒ እና ቤጂንግ አራት አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ያስመዘገባቸው ውጤቶች አመርቂ ተብለው ተመዝግበዋል ። ዛሬ ማታ በሴቶች የ5000 ሜትር እና የ800 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ ።
በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ በዩጂን የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ጉዳፍ ፀጋዬ እና ኬኒያዊቷ የሪዮ ዴ ጄኔሮ ኦሎምፒክ ክብረወሰን ባለድል ቪቪያን ጄፕኬሚ ቼሩዮት ተሳታፊ ናቸው ። እነ መዲና ኢሳ እና እጅጋየሁ ታዬም ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ ። የኔዘርላንዷ ሲፋን ሐሰን እና ኬንያዊቷ ኪፕዬጎ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ። በሴቶች 800 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ኢትዮፕያ በፅጌ ዱጉማ እና ወርቅነሽ መለሠ ተወክላለች ። በርቀቱ የዓለም እና የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች በቼኳ ጃርሚላ ክራቶችቪሎቫ 1983 ሙይንሽን እና በሩስያዊቷ ናዴዣኦሊዛሬንኮ በ198 ሞስኮ ኦሎምፒክ የተያዘ ነው ። የሁለቱም በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ነው ።
ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በብዛት የሚጠበቁበት የፓሪስ ኦሎምፒክ ፉክክር ቀጥሏል ። ኢትዮጵያ እስካሁን በወንዶች 10,000 ሜትር የፍጻሜ ፉክክር በበሪሁ አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች ። በፍጻሜው ስለተገኘው እና ስለሌሎች ውድድሮች ከፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ጋ ቃለ መጠይቅ አድርገናል ወደዚያው እንለፍ ።
በርምጃ እና ውኃ ዋና ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተፎካካሪ ነበሩ ። በተለይ በአትሌት ምሥጋናው ዋቁማ ስድስተኛ ደረጃ የተገኘበት የርምጃ ፉክክር ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ ኦሎምፒክ ብቅ ያለችበት በመሆኑ ውጤቱ የሚወደስ ነው ። አትሌት ምሥጋናው ዋቁማ በቅርቡ በተኪያሄደው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የርምጃ ፉክክር ባለድል ነው ። በመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ሊና ዓለማየሁም በዋና ውድድር በፓሪስ ኦሎምፒክ መሳተፏም አበረታች ነው ።
ዩጋንዳዊው እንደምን ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አፍትሎ ወጣ?
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እስከ ውድድሩ መገባደጃ ድረስ በአብዛኛው ፊታውራሪ በነበሩበት የ10,000 ሜትር የወንዶች የፍጻሜ ፉክክር በአጨራረስ ብቃት ዩጋንዳ ወርቁን ከኢትዮጵያ ፈልቅቃ ወስዳለች ። በ10,000 ሜትር የዓለም ፍጻሜ የሁለት ጊዜ ባለድሉ ጆሹዋ ቺፕቼጌ በውድድሩ መገባደጃ ልክ እንደነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ የአሯሯጥ ስልት በድንገት አፈትልኮ በመውጣት አሸናፊ ሁኗል ። ጆሹዋ ዓርብ ዕለት ያሸነፈውም 26 ደቂቃ ከ43.14 በመግባት ነው ።
በሪሁ አረጋዊም ጆሹዋን በመከተል ከኋላ ተፈትልኮ ከፊት ለፊቱ የነበሩትን አትሌቶች በመደረብ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል ። በጆሹዋ የተበለጠው በማይክሮ ሰከንዶች ሲሆን የገባበት ሰአት 26:43.44 ነው ። ምናልባትም በሪሁ አፈትልኮ የወጣበት ሁኔታ ቀድሞ የተከወነ ቢሆን ኑሮ ከጆሹዋ ቀድሞም በማሸነፍ ክብረወሰኑ ለእሱ ይሆን ነበር ። በዚህ ረገድ አትሌቶቹ በተናጠል አሰልጣኞች መሰልጠናቸው አስተዋጽዖ ሳያደርግ አይቀርም መባሉን ሃይማኖት ጠቁማለች ። በፓሪስ ኦሎምፒክ አትሌቶቹ ለረዥም ጊዜ ከፊት ሆነው ውድድሩን ለመምራት ኃላፊነት የወሰደው ማነው የሚለውም እያነጋገረ ነው ። በ10,000 ሜትር የፍጻሜ ፉክክር ሰለሞን ባረጋ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊ ተሳታፊ ነበሩ ።
የሜዳ ቴኒስ
የ37 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ የምንጊዜም ብርቱ ተፎካካሪ ኖቫክ ጄኮቪች ስፔናዊውን ሮላንድ ጋሮስ በመርታት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል ። ሠርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ባለድል ስፔናዊውን የ21 ዓመት ወጣት የረታው ለሁለት ጊዜ 7-6 እና 7-6 በማሸነፍ ነው ። ኖቫክ ጄኮቪች ለሠርቢያ ሁለተኛ ወርቅ ነው ያስገኘው ። ከትናንቱ ድል በኋላ ኖቫክ ጄኮቪች በደስታ ፊቱን በነች ፎጣ ሸፍኖ ሲንሰቀሰቅ እና እጆቹ ሲንቀጠቀጡ ታይቷል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ካገኘ ወዲህ በኦሎምፒክ ድል ሲያስመዘግብ ይህ የመጀመሪያው ነው ።
ላለፉት ሦስት የኦሎምፒክ ውድድሮችም ማጣሪያውና ሳያልፍ በመቅረቱ ለ37 ዓመቱ አትሌት የትናንቱ የኦሎምፒክ ድል እጅግ በልዩ ሁኔታ የሚታይ ነው ። የሐምሌ 22 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የውኃ ዋና
የፓሪስ ኦሎምፒክ የወንዞች ተፋሰሶችን ከብክለት ለማጽዳት በሚል 1,5 ቢሊዮን ዶላር እንደፈሰሰ ተነግሮ ነበር ። ሆኖም በትሪያትሎን ተሳታፊ የነበሩ ተወዳዳሪዎች በባክቴሪያ የተነሳ ለሕመም መዳረጋቸው አነጋጋሪ ሁኗል ። ቤልጂየም ሰኞ ዕለት አንድተፎካካሪዋ በመታመሙ ዋና፤ ሩጫ እና ብስክሌት ግልቢያን በሚያጣምረው የትሪያትሎን ፉክክር ላይ አልተወዳደረችም ። የስዊትዘርላንድ፤ የኖርዌይ የትሪያትሎን ቡድን አባላትም በባክቴሪያ መታመማቸው ያ ሁሉ ገንዘብ የተከሰከሰበት የወንዙ ጥራት ጉዳይ አነጋጋቲነቱ ቀጥሏል ።
ቡጢ
የአልጀሪያዋ ቡጢኛ የጾታ ጉዳይ በፓሪስ የኦሎምፒክ ውድድር ውዝግብ አስነስቷል ። አልጀሪያዊቷ ቡጢኛ ኢማኔ ከሊፋ እና የታይዋኗ ቡጢኛ ሊን ዩ-ቲንግ በፓሪስ ኦሎምፒክ መወዳደር ነበረባቸው አልነበረባቸው አጨቃጭቋል ። ሁለቱ ቡጢኞች ባለፈው ዓመት በተደረገው የዓለም የሴቶች የቡጢ ፍልሚያ ላይ የጾታ ብቃት መመዘኛዎችን አላሟሉም በሚል እገዳ ተጥሎባቸው ሳይወዳደሩ ቆይተው ነበር ። የዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ቅድመ ዝግጅት
በተለይ በተክለ ሰውነት ገዘፍ ያለችው የአልጀሪያዋ ቡጢኛ ከጣሊያናዊቷ ተጋጣሚ ጋ ያደረገችው ቡጢ የተጠናቀቀው አንድ ደቂቃም ሳይሞላ ነበር ። ምክንያቱ ደግሞ ጣሊያናዊቷ ቡጢኛ አንጄላ ካሪኒ ያረፈባት ቡጢ ከዚህ ቀደም ከሴቶች ተወዳዳሪዎች ከሚሰነዘረው የተለየ በመሆኑ ለሕይወቴ ሰግቼ ነው ብላለች ። የዓለም ቡጢ ማኅበር ሁለቱ ቡጢኞች እንዳይወዳደሩ በሚል የከለከለውን በፓሪስ ኦሎምፒክ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሽሮ ተፎካካሪዎች ማድረጉ አወዛግቧል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ሃይማኖት ጥሩነህ
ሸዋዬ ለገሰ