1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕወሓት የ41 ቀናት ስብሰባ ተጠናቀቀ

ሐሙስ፣ ጥር 23 2016

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለ41 ቀናት አደረግኩት ካለው ስብሰባ በኃላ ባወጣው መግለጫ በፓርቲው ውስጥ የአመራር ማስተካከያ ለማድረግ መስማማቱን ገልጧል። በተለያዩ ጉዳዮችን የዳሰሰበትን መግለጫ ትናንንት ያወጣው ሕወሓት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሙሉእነት እንዲተገበርም ጥሪ አቅርቧል።

https://p.dw.com/p/4bw4O
የመቀሌ ከተማ
የመቀሌ ከተማ፤ ትግራይ ክልልምስል Million Haileselassie/DW

የ41 ቀኑ የሕወሓት ስብሰባ ተጠናቀቀ

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለ41 ቀናት አደረግኩት ካለው ስብሰባ በኃላ ባወጣው መግለጫ በፓርቲው ውስጥ የአመራር ማስተካከያ ለማድረግ መስማማቱን ገልጧል። በተለያዩ ጉዳዮችን የዳሰሰበትን መግለጫ ትናንንት ያወጣው ሕወሓት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሙሉእነት እንዲተገበርም ጥሪ አቅርቧል። ከአንድ ወር በላይ የፈጀውን የሕወሓት ስብሰባን በተመለከተ የመቀሌ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል ።

ሕዳር 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም እንደተጀመረ የተገለፀው እና እንደ የሕወሓት መግለጫ ገለፃ 41 ቀናት የፈጀው የሕወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር፣ የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ ሹሞች፣ የቀድሞ የፓርቲው አመራር እና ሌሎች የተሳተፉበት ልዩ ስብሰባ መጠናቀቁን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ትናንት ማምሻውን ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ ዐስታውቋል። መደረግ የነበረበት ስብሰባ ቢሆንም፥ ትግራይ በድርቅና ረሃብ ባለችበት ለ41 ቀናት የዘለቀ ስብሰባ በመቀመጡ ይቅርታ የጠየቀው ህወሓት፥ "ከአሁን በኃላ ግን በሙሉ አቅማችን የህዝባችን ችግር በመፍታት ላይ እንጠመዳለን" ሲል ቃል ገብቷል።

 በዚሁ ልዩ መድረኩ የተነሱ እና መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ብሎ 6 ነጥቦች ያስቀመጠው ሕወሓት፥ በስብሰባው ዓለምአቀፋዊ፣ ቀጠናዊ፣ ሀገራዊና ውስጣዊ ጉዳዮች ተነስተው ለትግራይ የሚኖረው ትርጉም በጥልቀት ተዳሰው ሲል አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በመድረኩ ህወሓት "የስትራተጂ አመራር ድክመት" እንዳለበት ተነስቶ መግባባት እንደተደረሰበት የገለፀ ሲሆን ይህም ለፀረ ዴሞክራሲ ባህርያት ማደግ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር መንገስ፣ ለቡድናዊነት እና ሌሎች ችግሮች እንደዳረጉት አምኗል።

ከዚህ በዘለለ የፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም በሚመለከት ግምገማ ማካሄዱ፣ በውሉ መሰረት ተፈናቃዮች አለመመለሳቸው፣ የትግራይ ግዛት አለመመለሱ፣ በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች የተጠያቂነት ጉዳይ ችላ መባሉ፣ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ቀጣይ ፖለቲካዊ ድርድሮች አለመካሄዳቸው መነሳቱ ህወሓት ትላንት ባወጣው መግለጫ ዐስታውቋል ።

የፕሪቶሪያው ውል ሲፈረም
የፕሪቶሪያው ውል ሲፈረም፦ ፎቶ ከማኅደርምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

ማራቶን በተባለው ስብሰባ በትግራይ በፓርቲ እና መንግስት መካከል ያለ መዘበራረቅ እንዲቀር፥ አሰራር እንዲበጅ መግባባት ላይ መደረሱ፣ ከግምገማና ነቀፌታ በኃላ በህወሓት ስትራቴጂካዊ አመራር ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ተሰብሳቢው መወሰኑ፣ በቀጣይ ወደ ፓርቲ ጉባኤ ለመግባት ዝግጅት እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉ ሕወሓት በመግለጫው አውስቷል።

በሕወሓቱ ረዥም ስብሰባ እና ያወጣው መግለጫ ዙርያ አስተያየት የጠየቅናቸው በመቐለ ዩኒቨርሰቲ የሕግና ስነመንግስት ኮሌጅ መምህሩ አፅበሃ ተኽለ፥ የህወሓት መግለጫ ይዘት እና የስብሰባው ውሳኔዎች ፓርቲው አሁንም ራሱን ሊቀይር አለመቻሉ ማሳያ ብለውታል።

ሌላው ያነጋገርናቸው የሕግ ምሁሩ ሙስጠፋ ዓብዱ በበኩላቸው፥ የስብሰባው ሂደት ሲገመግሙ መወነጃጀል የነገሰበት፣ ሁሉም ችግሮች ለአንድ ወገን ብቻ አሳልፎ የመስጠት ሁኔታ ይታይበት የነበረ ሲሉ ይገልፁታል። ከዚህ በተጨማሪ የሕግ ሙሁሩ ሙስጠፋ ህወሓት ከድክመቶቹ ወጥቶ እንደ የፕሪቶርያ ውል ፈራሚ ሚናው በተገቢው ሁኔታ ሊወጣ እንደሚጠበቅበት ይገልፃሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ