1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕዳር 22 ቀን 2017 የዓለም ዜና

ልደት አበበ
እሑድ፣ ኅዳር 22 2017

የሰላም ስምምነት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል ፣ ትራምፕ የብሪክስ አባላትን አስጠነቀቁ፣ ማሊ፤ በሰው አልባ አይሮፕላን በርካታ የቱአሬግ አማፂያን ተገደሉ፣ እስራኤል ከየመን የተወነጨፈ ሚሳኤል ማክሸፏን ገለፀች፣ በቫሌንሲያ ማራቶን መገርቱ አለሙ ወርቅ አሸነፈች

https://p.dw.com/p/4nckZ

የሰላም ስምምነት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት  መካከል

 

በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በኦሮሞ  ነጻነት ሰራዊት  መካከል የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግስት በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በኦሮሚያ የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በክልሉ መንግስት በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰላማዊ መንገድ ትግልን ለመረጡ ምስጋና አለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በኦሮሞ  ነጻነት ሰራዊት በኩል ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ተገኝተው የፈረሙት የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ ናቸው ። አቶ ሰኚም በዚህ ወቅት ለዚህ ስምምነት ያበቃን የህዝቡ ጥሪና እየደረሰበት ያለው ስቃይ ነው ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቃል አቃባይ አቶ ጂሬኛ ጉደታ በበኩላቸው ቡድናቸው ዛሬ ተደረሰ ስለተባለው ስምምነት መረጃ እንደሌለው ገልጸዋል።

 

ትራምፕ የብሪክስ አባላትን አስጠነቀቁ

ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የብሪክስ አባላትን አስጠነቀቁ።  ትራምፕ በማህበራዊ መገናኛ ገፃቸው ትናንት ማምሻውን ባስተላለፉት መልዕክት የብሪክስ አባል ሀገራት የአሜሪካን ዶላር የሚፎካከር ማንኛውንም መገበያያ ገንዘብ የሚጠቀሙ ከሆነ ሀገራቱ እስከ መቶ ፐርሰንት የቀረጥ ክፍያ ይጠብቃቸዋል፤ አልያም ጨርሶ ምርቶቻቸውን ለዩናይትድ ስቴትስ እንዳያቀርቡ ይደረጋሉ። ስለሆነም እነዚህ አገሮች ካሁኑ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳውቁ ትራምፕ አሳስበዋል። ከስድስት ሳምንት በፊት በሩሲያ በተካሄደው የብሪክስ አባል ሃገራት ጉባኤ ላይ ቡድኑ በጉባኤው በተለይ የምዕራቡን ዓለም ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም በሩሲያ አነሳሽነት የቀረበው አማራጭ የክፍያ ስረዓት ትኩረት ስቦ ነበር። በብራዚል ፣ ሩሲያ ፣ ህንድ ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ ጥምረት የተመሰረተው ብሪክስ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢራን ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በማካተት የአባላቱን ቁጥር 9 ሲያደርስ ቱርክ ፣ አዛርባጃን እና ማሌዢያ ቡድኑን ለመቀላቀል ማመልከቻቸውን አስገብተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።  

 

ማሊ፤ በሰው አልባ አይሮፕላን በርካታ የቱአሬግ አማፂያን ተገደሉ

 

የማሊ ጦር በሰው አልባ አይሮፕላን በፈፀመው ጥቃት በርካታ የቱአሬግ አማፂያን ተገደሉ። አንድ የሀገሪቱ ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ሰራተኛ እና የአይን እማኞች ለሮይተርስ ዜና ምንጭ እንዳረጋገጡት ዛሬ ጠዋት በተፈፀመው የድሮን ጥቃት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል አንድ ከፍተኛ የቱአሬግ አዛዥን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልተገለፁ አማፂያን ተገድለዋል።  ጥቃቱ የተፈፀመው በአልጄሪያ ድንበር አካባቢ የምትገኘው የማሊ ቲንዛኦአቴን ከተማ ሲሆን አንድ በቦታው የነበረ የሮይተርስ ጋዜጠኛም በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጧል። በጥቃቱ ተገድለዋል የተባሉት እና  ጋቲያ በመባል የሚታወቁት የቱአሬግ አማፂያን አዛዥ አል ማሙድ  የቀድሞ የመንግስት ደጋፊ ሚሊሻያ አባል የነበሩ ሲሆን  ከአንድ አመት በፊት ቡድኑን ከድተው ተገንጣይ  አማፂያንን ተቀላቅለዋል።   የማሊ ጦር በዚህ ላይ በይፋ ያለው ነገር የለም።

 

እስራኤል ከየመን የተወነጨፈ ሚሳኤል ማክሸፏን ገለፀች

እስራኤል ከየመን የተወነጨፈ ሚሳኤል ማክሸፏን ገለፀች። እንደ የእስራኤል ጦሩ ገለፃ ዛሬ እሁድ ማለዳ ላይ የተወነጨፈውን ሚሳኤል እስራኤል ከመድረሱ በፊት ማክሸፍ ተችሏል።  ሚሳኤሉ የተተኮሰው በኢራን የሚደገፈው እና የመን ውስጥ የሚገኘው የሁቲ ቡድን እንደሆነም ሮይተርስ ዜና ምንጭ ዘግቧል። ዘግየት ብለው ይህን በመግለጫ ያረጋገጡት ሁቲዎች የባሊስቲክ ሚሳኤል መጠቀማቸውን እና ኢላማቸውም ቲላቪቭ ላይ ወሳኝ የሆነ ቦታ እንደነበር አረጋግጠዋል።  ሁቲዎች ለፍልስጤማውያን ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት በተደጋጋሚ በሀማስ እና እስራኤል መካከል ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ወደ እስራኤል ተኩሰዋል።

በሊባኖሱ ሄዝቦላህ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ጦር መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ባለበት በአሁኑ ሰዓት እስራኤል በጋዛ የምትወስደውን ወታደራዊ ርምጃ ቀጥላለች።  ጦሩ በጋዛ ሰርጥ የተለያዩ አካባቢዎች ከአየር በወሰደው ርምጃ ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት ለፍልስጤም ስደተኞች (UNRWA) ከሆነ  በጋዛ ሰርጥ የሚደረገው የእርዳታ አቅርቦት ለሰራተኞቹ ደህንነት ሲባል ተቋርጧል። ድርጅቱ እንዳለው የታጠቁ ቡድኖች ዘረፋ ፈፅመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲካሄድ እና በሀማስ እጅ የሚገኙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ  የሚካሄደው ድርድር ቀጥሏል።  ከስምምነት ላይ ለመድረስ እየተሰራ ቢሆንም “እስካሁን ግን ከዚያ አልደረስንም” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ዛሬ እሁድ ለሀገራቸው መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል። «ይህን ለማድረግ በንቃት እየሰራን ነው» ያሉት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን  ከክልሉ ቁልፍ ተዋናዮች ጋር ውይይት እንዳለ እና ዛሬም እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል።  የሀማስ ተወካዮች ለድርድር ካይሮ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል።

 

በቫሌንሲያ ማራቶን መገርቱ አለሙ ወርቅ አሸነፈች

በስፔን ቫሌንሲያ የተካሄደውን የማራቶን ውድድር በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ መገርቱ አለሙ ፤ በወንዶች ደግሞ ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳቄ አንደኛ በመውጣት አሸነፉ። መገርቱ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2 ሰዓት ከ 16 ደቂቃ ከ 49 ሰከንድ ሲሆን ዩጋንዳዊቷ ስቴላ ቼሳንግ ሁለተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያዊቷ ጡሩዬ መስፍን ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።

ዛሬ በወንዶች ማራቶን አሸናፊ የሆነው ኬንያዊው ሰባስትያን ሳዌ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ 02 ደቂቃ ከ 05 ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን ይህም በወንዶች የማራቶን ታሪክ  አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። 33 ሰከንድ ዘግየት ብሎ የገባው ኢትዮጵያዊ ደሬሳ ገለታ ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኬንያዊ ዳንኤል ማታይኮ ደግሞ ሶስተኛ ሆኗል።

ዛሬ የቫሌንሲያ ማራቶን የተካሄደባት የስፔን ከተማ ከአንድ ወር በፊት ብርቱ የጎርፍ አደጋ ማስተናገዷ ይታወሳል። በጎርፍ አደጋው ​​230 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን  መንገዶች እና ቤቶች በጎርፍ ተወስደዋል ፣ ንብረትም ወድሟል።

 

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።