1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንሸራተት ስጋትና መፍትሔው

ማክሰኞ፣ ግንቦት 28 2010

ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት መንሸራረት ተከስቶ ጥቂት ለማይባሉ ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። የመሬት መንሸራረት ክስተት ኢትዮጵያ ውስጥ እንግዳ እንዳልሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብንብረት እና የአፍሪቃ አደጋ መከላከል ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ዘውዱ እሸቱ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/2yz5b
Erdrutsch Äthiopien Oromia Region West Arsi Zone
ምስል West Arsi Zone Government Communication Affairs Office

የተራቆተ ተዳፋት አካባቢ ለአደጋው የተጋለጠ ነው

 በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ደን ተሸፍኖ የኖረው መሬት ከባድ ዝናብ በሚያገኘው ጊዜ፤ አንዳንዴም መሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ ሲከሰት መኖሩንም ያስረዳሉ። በደቡብ ብቻ ሳይሆን በስተሰሜን ኢትዮጵያም የመሬት መንሸራተት ሲያጋጥም ቆይቷል ነው የሚሉት።

«አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው አንደኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲኖር የመሬት መንሸራተት ይኖራል፤ ሌላው ከፍተኛ ዝናብ ባለበት አካባቢ በተለይ ገደላማ እና ቁልቁለታማ አካባቢዎች ላይ ለበርካታ ጊዜ የመሬት መንሸራተት አለ።»

ያኔም የመሬቱ አቀማመጥ ተዳፋት ወይም በጣም ቁልቁለታማ በመሆኑ አፈሩ በመንሸራተት ከበታቹ በነበረ የትኛውም አይነት አካባቢ ላይ ወርዶ ይከመራል። ስፍራው የመኖሪያ መንደር ከሆነ ታዲያ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ መገመት ነው። እንዲህ ያለው አጋጣሚ በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም መከሰቱ የተለመደ እንደሆነ ዶክተር ዘውዱ ይናገራሉ።

«እና የዚህ አይነት የመሬት መንሸራተት በአብዛኛው ተደጋጋሚ ሆኖ የሚታወቀው በምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ በካሜሩን ጋና በዚያ አካባቢ በብዛት ይከሰታል።»

የመሬት መንሸራተት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች እንዳሉት የሚናገሩት ደግሞ በአካባቢ እና የደን ምርምር ተቋም የአየር ንብረት ሳይንስ ምርምር ዳይሬክቶሬት የሥራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ናቸው።

Erdrutsch Äthiopien Oromia Region West Arsi Zone
ምዕራብ አርሲ ዞን የደረሰው የሰሞኑ የመሬት መንሸራተት ምስል West Arsi Zone Government Communication Affairs Office

«ክስተቱን ስንመለከተው አንድ ተለቅ ያለ አካባቢ፤ ተዳፋታማ የሆነ ቦታ ሊሆን ይችላል አፈሩ ላዩ ላይ ያሉት ደኖችም፣ ድንጋዩም ተያይዞ በፊት ከነበረበት ቦታ ምናልባትም ወደቁልቁለት ቦታ ሲንሸራተት እና ቦታዉን ለቅቆ ሲሄድ ነው። መንስኤው በtf,ጥሮም በሰው ሠራሽም ነው የሚሆነው።»

ሰው ሠራሹ ምክንያት በተለይ በአካባቢው የነበረው ደን መመናመን ዋነኛ መንስኤ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። የመሬት መንሸራተትም ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ደን ሸፍኖት በቆየ አካባቢ መሆኑንም ያብራራሉ። ከባለሙያዎቹ እንደተረዳነው በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄዱ ጥናቶች በየትኛው አካባቢ ምን ስጋት አለ የሚለው ተለይቶ ተቀምጧል።

Pollenflug im Frühjahr
ዛፎች የአፈር በዝናብ መከላትን ይከላከላሉምስል picture-alliance/A. Litzlbauer

የአንድ አካባቢ መሬት በተለያዩ ሥራዎች እረፍት ሲያጣ ይላሉ ባለሙያዎቹ ተፈጥሮው መረበሹ ያልተገመተ ክስተት ይጋብዛል። የመሬት ወይም የአፈር መንሸራተት በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚፈጠር መሆኑን ዳግም በማስታወስም የመሬት መንቀጥቀጥንም ሆነ ሌላውን ማስቀረት ባይቻል፤ በሰዎች እንቅስቃሴ ሰበብ ሊመጣ የሚችለውን ለመከላከል የሚያስችሉ መንገዶች አሉ።

የዛሬ አስር ቀን ገደማ በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ቱሉ ጎላ ቀበሌ የደረሰው የመሬት ወይም የአፈር መንሸራተት የአንድ ቤተሰብ በርካታ አባላትን ጨምሮ ከ20 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ከብቶች ሞተዋል ንብረት ወድሟል። ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የሚከተለውን እንዲህ ያለውን አደጋ ማስቀረት ባይቻል፤  በተለይ ስጋቱ እንዳለ በሚታወቅባቸው ስፍራዎች ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚቀነሱበትን መንገድ መፈለጉ አማራጭ እንደማይኖረውም ባለሙያዎቹ መክረዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ