ርዕደ መሬት በዳውሮ ዞን
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2016በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ዛሬ ጠዋት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ። የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ የተከሰተው የዞኑ ዋና ከተማ ተርጫን ጨምሮ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ነው ።
ጠዋት በግምት አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከሁለት እስከ ሦስት ሰከንድ የሚደርስ ንዝረት መከሰቱን የተናገሩት ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች «በንዝረቱ የመኖሪያ ቤት ግድግዳዎችና የቤት ዕቃዎች ተንቀጥቅጠዋል ። አንዳንድ ነዋሪዎችም በድንጋጤ ከቤት በመውጣት ለመሮጥ ሲሞክሩ ተስተውለዋል » ብለዋል ።
መጠነ ርዕደት
የመሬት መንቀጥቀጡ መከሰቱን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ለማ መሠለ «ያም ሆኖ ንዝረቱ በነዋሪው ላይ ካስከተለው ጊዜያዊ መደናገጥ ውጭ በሰው ሕይወትም ሆነ ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አልተመዘገበም» ብለዋል ፡፡
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለሞያና ተመራማሪ ዶክተር አታላይ አየለ ዛሬ ጠዋት አንድ ሰዓት ከሃያ አራት ደቂቃ ላይ በዳውሮ ዞን በሬክተር እስኬል 3 ነጥብ 0 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተናግረዋል ፡፡
የእርግብግቢት ሥሜቱ ተርጫን ጨምሮ በሌሎች አጎራባች ከተሞች ቢከሰትም ዋናው የንዝረቱ ማዕከል ግን ከከተሞቹ እስከ 30 ኪሎ ሜትር በሚገመት ርቀት ላይ የተከሰተ መሆኑ የጠቀሱት ዶክተር አታላይ ይህም በሰው ሕይወትም ሆነ በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልበት ደረጃው ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
የሰምጥ ሸለቆ ሥጋት
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለሞያና ተመራማሪ ዶክተር አታላይ አየለ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭነት አለው ይላሉ ፡፡ በዚህ አካባቢ ለሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ከዓመታት በፊት በኮድ የተደገፈና ወጥ መመዘኛ ያለው መመሪያ መዘጋጁትን የጠቀሱት ባለሙያው " ይሁንእንጂ መመሪያው እስከአሁን ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ፡፡ ምክንያቱም ግንባታውን የሚያከናውኑት የመንግሥትም ተቋማትም ሆኑ የግል ባለሀብቶች ተጨማሪ ወጪን የሚጠይቃቸው በመሆኑ ነው ፡፡ በእኛ አገር ሰው በቀላል ወጪ መገንባቱን ነው የሚያየው ፡፡ አካባቢው ለርዕደ መሬት የተጋለጠ በመሆኑ ክስተቱ ሊፈጠር ይችላል ፡፡ ይህ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው " ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋንግዛው ወጋየሁ