የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የባንክ ሒሳብ ዳግም ታገደ
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፈዉ ዓመት ማብቂያ ያደረገዉ ጠቅላላ ጉባኤ፣ዉሳኔዎችና የኮሚቴዉ የባንክ ሒሳብ በፍርድ ቤት ታገደ።ባለፈዉ ኃምሌና ነሐሴ ፓሪስ-ፈረሳይ ባስተናገደችዉ የዓለም የኦሎሚፒያ ዉድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ዝቅተኛ ዉጤት ካመጡ ወዲሕ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለሥልጣናት ላይ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት እየተሰነዘረ ነዉ።የኮሚቴዉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሰዉ በማዘዋወርና ሐብት በማባከን ጥርጣሬ ተከስሰዋልም።የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ የከሳሽ ጠበቆችን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ትናንት አዲስ አበባ ያስቻለዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባኤን፣ ውሳኔዎቹንና የኮሚቴዉን የባንክ ሒሳብ አግዷል።የኮሚቴዉ ባለሥልጣናት ሥለፍርድ ቤቱ ዉሳኔ አስተያየታቸዉን እንዲሰጡ ስልክ ቢደወልላቸዉም አልተገኙም።ትናንት ግን ኮሚቴዉ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለተሳተፉ አትሌቶች እና አሰልጣኞች ዕዉቅና እና የሽልማት ሰጥቷል።
ሞቃዲሾ-የሶማሊያ ፖሊስ ሕግ ወጥ ጦር መሳሪያ ያዘ
የሶማሊያ ፖሊስ በሕገ-ወጥ መንገድ «ወደ ሐገር የገባ» ያለዉን በርካታ ጠመንጃ፣ ከባድ መሳሪያና ጥይቶች መያዙን አስታወቀ።ፖሊስ እንዳለዉ ትናት ርዕሠ ከተማ ሞቃዲሾ ዉስጥ የተያዘዉን ጦር መሳሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ አስገብተዉ ለመሸጥ የተዘጋጁ አራት ሰዎችም ታሥረዋል።ፖሊስ ያዝኳቸዉ ያላቸዉን 33 AK47 ( ወይም ክላሺንኮቭ) ጠመንጃዎች፣ PKM አዉቶማቲክ መትረየስና በርካታ ጥይቶችን የሚያሳይ ቪዲዮ የሶማሊያ መንግሥት በሚቆጣጠረዉ SNTV በተባለዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ አሰራጭቷል።የሞቃዲሾ ፖሊስ አዛዥ መሕዲ ዓሊ ሙእሚን የከተማይቱ የፖሊስ ኃይል ሕገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች ዝዉዉርን እንደሚቆጣጠር፣ ነጋዴዎችንም እንደሚያስር ዝተዋል።ባለፈዉ ኃምሌ «ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የገባ» የተባለ በርካታ ጦር መሳሪያ ጋልጉዱድ ግዛት ዉስጥ በሶማሊያ የጎሳ ታጣቂዎች ተይዞ ነበር።ጦር መሳሪያዉ ከተያዘ በኋላ የሶማሊያ የሚንስትሮች ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ሽያጭና ዝዉዉርን የሚያግድ ደንብ አዉጥቷል።
ማድሪድ-የስጳኛ ነብስ አድን ሰራተኞች 500 ስደተኛ አዳኑ
የስጳኝ የባሕር ላይ አደጋ መከላከያ ሠራተኞች የሜድትራኒያን ባሕርን ለሟቋረጥ ሲቀዝፉ ለአደጋ የተጋለጡ 500 ስደተኞችን አዳኑ።የአደጋ ሠራተኞቹ ኃላፊዎች እንዳሉት ሕይወታቸዉ ከዳነዉ ስደተኞች 300 ያክሉ ላ ሬስቲጋ ወደተባለችዉ የወደብ ከተማ ተወስደዋል።ሌሎቹ ስደተኞች ደግሞ በአራት አነስተኛ መርከቦች ተሳፍረዉ ወደ ካናሪ ደሴት ተልከዋል።ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የአፍሪቃ ስደተኞች እንደነገሩ በተሰራ የእንጨት ጀልባ እየተጓዙ ወደ ተለያዩ የስጳኝ ተጫፋሪ ደሴቶች ገብተዋል።የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) እንዳለዉ ካለፈዉ ጥር እስከ ዘንድሮዉ መስከረም አጋማሽ ድረስ 27 ሺሕ ስደተኞች ከአፍሪቃ ስጳኝ ገብተዋል።አብዛኞቹ ስደተኞች ስጳኝ የሚገቡት ወይም ወደ ስጳኝ የሚጓዙት ከደቡብ የጊኒ፣ ከሰሜን የሞሮኮ ጠረፎች ከሚያዋስኑት የባሕር በሮች በጀልባ እየቀዘፉ ነዉ።
ማሊ-የከብት ገበያዎች ታገዱ፣ ሟቾቹ 70 ደረሱ
የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በሐገሪቱ ርዕሰ ከተማ ባማኮ ዉስጥ የሚቆሙ 7 የቁም ከብቶች ገበያዎችን አገደ።መንግሥት ገበያዎቹን ያገደዉ ከክብት ሻጮች ጋር ተመሳስለዉ ወደ ከተማይቱ የገቡ ደፈጣ ተዋጊዎች ባለፈዉ ማክሰኞ አንድ የፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያን በማጥቃታቸዉ ነዉ።ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት አላቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች በአንድ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ በከፈቱት ጥቃት 70 ሰዎች ገድለዋል።እዚያዉ ባማኮ የሚገኙ ምዕራባዉያን ዲዕሎማቶች እንዳሉት ደፈጣ ተዋጊዎቹ ከገደሏቸዉ ሰዎች ቢያንስ 60ዎቹ ሥልጠና ላይ የነበሩ ምልምል ፖሊሶች ነበሩ።ባለፈዉ ሳምንት የማሊ ወታደራዊ ሁንታ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ጦራቸዉ የደፈጣ ተዋጊዎቹን የመዋጋት አቅም ክፉኛ አዳክሞታል ብለዉ ነበር።
ቴል አቪቭ/ ቤይሩት-የእስራኤልና የሒዝቦላሕ ዉጊያ
እስራኤልና የሊባኖስ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቦላሕ የገጠሙት ዉጊያ ዛሬ ተጠናክሮ ዉሏል።ሒዝቦላሕ ዛሬ ሲነጋጋ ጀምሮ ሰሜናዊ እስራኤልን በ140 ሮኬቶችና ሚሳዬሎች ደብድቧል።ሒዝቦላሕ እንዳስታወቀዉ በሶስት ዙር የከፈተዉ ጥቃት ሰሜን እስራኤል ዉስጥ በተጠመዱ የአየር መከላከያ፣ የከባድ መሳሪያ መተኮሻና በሌሎች ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ያነጣጠረ ነበር።የእስራኤል ጦር ኃይል እንዳለዉ ደግሞ ሒዝቡላሕ ከተኮሳቸዉ ሚሳዬሎች 120ዉ በጎላን ኮረብቶች፣ ሳፋድና የላይኛዉ ጋሊሌ በተባሉ አካባቢዎች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ።የተቀሩት 20 ሚሳዬሎች ሜሮን እና ኔቱዋ የተባሉ አካባቢዎችን ኢላማ ያደረጉ ነበሩ።ሚሳዬሎቹ በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ያደረሱት ጉዳት ሥለመኖር አለመኖሩ የእስራኤል ባለሥልጣናት ያሉት ነገር የለም።ሒዝቦላሕ ግን ሰዎችን «እያደነ የሚገድለዉን» የእስራኤልን የሥለላ ድርጅት የሰሜን ቅርንጫፍ ዋና መስሪያ ቤትን መምታቱን አስታዉቋል።እስራኤል ሰሞኑን ደቡባዊ ሊባኖስ ላይ በከፈተችዉ ጥቃት የሒዝቦላሕን ሚሲዬል ማወንጨፊያዎች ማዉደሟን አስታዉቃ ነበር።
ቤይሩት-የእስራኤል አፀፋ ጥቃት
እስራኤል ዛሬ ደግሞ የሊባኖስን ርዕሰ ከተማ ቤይሩትን በጦር ጄቶች፣ የሶሪያን ዋና ከተማ ደማስቆን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን ደብድባለች።የሊባኖስ የጤና ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ በድብደባዉ ቤይሩት ዉስጥ 8 ሰዎች ተገድለዋል።ሌሎች 60 ሰዎች ቆስለዋል።ከሟቾቹ አንዱ የሒዝቦላሕ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።ደማስቆ-ሶሪያ ዉስጥ ደግሞ አንድ የሒዝቦላሕ ተዋጊ መገደሉን ቡድኑ አስታዉቋል።የእስራኤልና የሒዝቦላሕ ዉጊያ በመባባሱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሊያደርጉት ያቀዱትን ጉዞ ቢያንስ ባንድ ቀን ለማራዘም ተገድደዋል።ዩናይትድ ስቴትስ በበኩላ ዜጎችዋ ወደ ሊባኖስ እንዳይጓዙ በጥብቅ አሳስባለች።
ኪቭ-የአዉሮጳ ሕብረት ለዩክሬን 35 ቢሊዮን ዩሮ ሊያበድር ነዉ
የአዉሮጳ ሕብረት ለዩክሬን 35 ቢሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ብድር እንደሚሰጥ አስታወቀ።ገንዘቡ የቡድን 7 አባል ሐገራት ለዩክሬን ሊሰጡት ያቀዱት ብድር አካል ነዉ።የ7ቱ ሐገራት መሪዎች ባለፈዉ ሰኔ ለዩክሬን 50 ቢሊዮን ዶላር ለማበደር ቃል ገብተዋል።የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን ዛሬ ዩክሬንን ሲጎበኙ እንዳስታወቁት ሕብረታቸዉ ለዩክሬን ለሚሰጠዉ ብድር፣ ሩሲያ ዩክሬንን በመዉረሯ ሰበብ ምዕራባዉያን መንግሥታት ካገዱት የሩሲያ ሐብት የሚገኘዉን ወለድ እንደመያዣ ይጠቀሙበታል።
«የአዉሮጳ ሕብረት፣ ቡድን 7 ለዩክሬን ለማበደር ቃል ገባዉ 35 ቢሊዮን ዩሮዉን ማበደር የሚያስችለዉን ዕቅድ ኮሚሽኑ አፅድቋል።ታላቅ እመርታ ነዉ።ብድሩን ባጭር ጊዜ ዉስጥ ለዩክሬን እንደምሰጥ እርግጠኛ ነን።ብድሩ ከታገደዉ የሩሲያ ንብረት የሚደገፍ ነዉ።»
ፎን ዴር ላይን አክለዉ እንዳሉት ዩክሬን በተለይ የኃይል ማመንጫ ተቋማትን ለመጠገን የምታደርገዉን «ደፋር» ያሉትን ጥረት ሕብረታቸዉ ይደግፋል።
ሞስኮ- ሩሲያ ተጨማሪ የዩክሬንን ግዛት ያዘች፣ ኩርስክን ባጭር ጊዜ ዳግም ለመቆጣጠር ዛተች
በዉጊያዉ አዉድ የሩሲያ ጦር ዛሬ ዤላኔ የተባለች የምሥራቃዊ ዩክሬን ግዛት ከተማን ተቆጣጥሯል።የሩሲያ ባለሥልጣናት እንዳሉት ጦራቸዉ የዩክሬን ጦር ባለፈዉ ነሐሴ መጀመሪያ የወረራትን የኩርስክ ግዛትንም ባጭር ጊዜ መልሶ ይቆጣጠራል።ይሁንና የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ልዩ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የጦራቸዉን የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ መናገር አልፈለጉም።
«የጦር ኃይሎቻችን ሥራቸዉን እያከናወኑ ነዉ።ያጠናቅቁታል።(ኩርስክን) መልሰዉ ይቆጣጠራሉ።እንዴት? የጦሩ እቅድ በይፋ አይነገርም።እንደሚቆጣጠሩት ግን አንጠራጠርም።የዩክሬን ታጣቂዎች በሚቆጣጠሩት አካባቢ ያለዉ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነዉ።ይኽ ሁኔታ ጊዜዉ ሲፈቅድ ይቀየራል።»
ይሕ በንዲሕ እንዳለ በምዕራባዉያን መንግሥታት የምትረዳዉ ዩክሬን የሩሲያን የቅርብ ወዳጅና ጎረቤት ቤሎሩስን ካጠቃች ሩሲያ ጠንካራ አፀፋ እርምጃ እንደምትወስድ የሩሲያ ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።
ነጋሽ መሐመድ