የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይዞታ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2015የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልሰት ጉዳዮች መስሪያ ቤት እንዳስታወቀው ከዚህ ዓመት ሰኔ እስከ መስከረም ብቻ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ወዳልቆመባት የመን የገባው ስደተኛ ቁጥር፣ ከ15,770 ይበልጣል። ከነዚህም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ናቸው።ከዚህ ዓመት ጥር ወዲህ የመን ባህር ዳርቻዎች የደረሱ ስደተኞች አጠቃላይ ቁጥር ከ42 ሺህ በላይ ነው።ለብዙ ዓመታት የመን በስደተኝነት የምትኖረውን ኤደንን ከዛሬ አራት ወር በፊት ስናነጋግራት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ከሰጠው የየመን መንግሥት መናገሻ አደን የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነበረች።ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ኤደን አሁን ነው ሰንዓ ያለችው ። እስከ ዛሬ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት በሁቱ አማጽያን ይዞታ ስር በምትገኘው በሰንዓ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የነበረችው ኤደን ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሚያመዝኑበት በአንድ መጠለያ ውስጥ እሳት ተነስቶ የሰዎች ሕይወት ከጠፋና ጥቂት የማይባሉም ለአካል ጉዳት ከተዳረጉ በኋላ ተቃውሞ በማሰማታችን ከሰንዓ ወደ አደን ተባረርን ትላለች ።
በአደን የአኗኗሩ ሁኔታ ሙቀቱና መጠለያው ስልላተመቻቸው ከጥቂት ወራት በፊት ካለምንም ረዳት በራሳችን ወደ ሰንዓ ተመለስን ብላለች ኤደን። ይሁንና በሰንዓ እንደ አደን መጠለያም ይሁን የምግብ ራሽን የላቸውም።አሁን ራሳቸውን የሚያስተዳድሩት በቀን ስራ ነው። ኤደን እንደምትለው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሰንዓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሺህዎች የሚቆጠሩ ናቸው።
የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት የተመድ ወደ ሀገራቸው ለመሄድ ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው እየመለሰ ነው። ይሁንና ወደ ሀገራቸው ከተሸኙት ኢትዮጵያውያን መካከል፣ከዚህ ቀደም የመን በገቡበት ፣እጅግ አደገኛ የበረሃና የባህር ጉዞ ተመልሰው የሚመጡ ብዙዎች ናቸው ይላሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወደህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከየመን ሚሊሽያዎች ጋር ተሰልፈው ይዋጋሉም ብለዋል። ወደ አርባ አምስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የመን መኖራቸውን የነገሩን እኚህ ኢትዮጵያዊ እንደሚሉት በፊት ጥቂቱ ነበሩ ለውጊያ የሚሰለፉት። አሁን ግን ቁጥራቸው እየጨመረ ነው ። በሰንዓ የምግብ ቤት ባለቤት የሆኑት እኚህ ኢትዮጵያዊት እንደሚሉት ሰሞኑን ደግሞ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች እየታፈሱ ነው።የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁኔታ በጣም ያሳስባቸዋል ።
በቀን ስራ የምትኖረው የኤደን ልጆች 15፣11ና 9 ዓመት ናቸው። ሦስቱም የተወለዱት የመን ነው፤ ግን አይማሩም ። የመጀመሪያ ልጇ እስከ ሦስተኛ ክፍል ተምሯል።የተቀሩት ሁለቱ ፊደል ብቻ ነው የቆጠሩት። ኤደንን ፣የልጆቻችሁም ሆነ የእናንተ እጣ ፈንታ አያሳስባችሁም? ወደ ሀገራችሁ የመመለስ ሃሳብስ የላችሁም ብያት ነበር። ኤደን እንዳለችው በቅርቡ የተመድ እርዳታ እንሰጣችኋለን ተመዝገቡ ብሏቸው ተመዝገበው እየተጠባበቁ ነው።ይህም ለእነ ኤደን ከምንም የሚሻል ተስፋ ሆኗል።
ሒሩት መለሰ