1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"አስቸኳይ መፍትሔ የሚሹ" የመብት ጥሰቶች

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2016

በምስራቅ ወለጋ ዞን ሰቡሲሬ ወረዳ ሞቶ ቀበሌ ሚያዚያ 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም 14 የአካባቢው ነዋሪዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን እንዲሁም በምዕራብ አርሲ ዞን ታጣቂዎች በሰዎች ላይ ግድያ፣ እገታ እና የአካል ጉዳት መፈፀማቸውን ገልጾ፤ 5 ሰዎች በዚሁ ዞን በታጣቂዎች መገደላቸውን ኢሰመጉ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4fOfE
Logo des Ethiopian Human Rights Council
ምስል Ethiopian Human Rights Council

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጽሟቸውን ግድያዎች እና ሕገ ወጥ እሥሮች እንዲቆሙ መጠየቁ


መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያና ክልሎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ታጣቂዎች የሚፈጽሟቸውን ግድያዎች እና ሕገ ወጥ እሥሮች እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ጠየቀ።
መሰል ወንጀል ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የጠየቀው ኢሰመጉ፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሚያዚያ ወር በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ እና በምዕራብ አርሲ ዞኖች 19 ሰዎች መግደላቸውን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አፈናዎችን እና ድብደባዎችን እንዲያስቆሙ ያሳሰበው የመብት ድርጅቱ፣ የሰዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እንዲከበርም ወትውቷል። ኢሰመጉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ በሚገኘው አማራ ክልል ውስጥ የሚፈጸሙየሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንየአዋጁ መርማሪ ቦርድ አጣርቶ ወንጀለኞች የሚጠየቁበትን ምክር እንዲያቀርብም በመግለጫው ጠይቋል።


ኢሰመጉ ደርሰዋል ያላቸው የመብት ጥሰቶች
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በሕይወት የመኖር እና የአካል ደህንነት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በተመለከተውና "አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው የመብት ጉዳዮች" በሚል ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት "በምስራቅ ወለጋ ዞን ሰቡሲሬ ወረዳ ሞቶ ቀበሌ ሚያዚያ 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም 14 የአካባቢው ነዋሪዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን እንዲሁም በምዕራብ አርሲ ዞን ታጣቂዎች በሰዎች ላይ ግድያ፣እገታ እና የአካል ጉዳት መፈፀማቸውን ገልጾ፤ 5 ሰዎች በዚሁ ዞን በታጣቂዎች መገደላቸውን"ም አስታውቋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ባለው ግጭት "በሰዎች ላይ የሚደርሰው ግድያ፣ እገታ፣ የጅምላ እስር፣ የንብረት ውድመት፣ በየከተሞች የቦንብ ፍንዳታና የመንገዶች መዘጋት እንደቀጠለ መሆኑን" እና ሰዎች ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ እንደማይችሉ፣ አሽከርካሪዎች እንደሚታገቱ ኢሰመጉ ጠቅሷል።
ተመሳሳይ እሥሮች ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መበራከቱንም ኢሰመጉ ገልጿል። የተቋሙን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹን ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።

ኢሰመጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መብቶች በተመለከተው የመግለጫው ክፍል በራያ አላማጣ ወረዳ በተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ወደ ቆቦ እና ሰቆጣ ከተማ መሸሻቸውን ጠቅሷል።

ኢሰመጉ ለመንግሥት ያቀረበው ጥሪ


ኢሰመጉ የፌደራሉ መንግሥት በተለይ በሁለቱ ትልልቅ ክልሎች በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎች እየተፈፀሙ ያሉ ግድያዎችከሕግ ውጭ ያላቸው እሥሮች እና ድብደባዎችን እንዲያስቆም፤ አጥፊዎችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቋል።
ሁሉም የመንግሥት አካላት የሰዎችን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያሳሰበው የመብት ድርጅቱ ፣ እገታዎች እንዲቆሙ ፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እና የመሥራት መብትም እንዲጠበቅ ጠይቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ባለው አማራ ክልል በሰዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው የዘፈቀደ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በአዋጁ መርማሪ ቦርድ ተገቢው ክትትልና ማጣራት ተደርጎ  ጥሰት ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ለሚመለከተው አካል በፍጥነት እንዲያቀርብም ጠይቋል።
ኢሰመጉ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት አካላት ምላሽ ለማግኘት "በተደጋጋሚ" አደረግሁት ያለው ጥረት ሊሳካ አለመቻሉን አስታውቋል። እኛም ለጉዳዩ ምላሽ የሚሰጠን አካል ማግኘት አልቻልንም።
ሰለሞን ሙጩ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር