አዲስ አበባ-የሰብአዊ መብት ጥሰት በአማራ ክልል -ሑማን ራይትስ ዋች
የኢትዮጵያ መንግስት ጦር በአማራ ክልል አድርሶታል ተብሎ የሚጠረጠረዉን «የጦር ወንጀል» የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲያጣራ ሒዩማን ራይትስ ወች ጠየቀ። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት እንደሚለዉ የኢትዮጵያ ጦር ባለፈዉ ጥር 20 አማራ ክልል መርዓዊ ከተማ ዉስጥ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል። የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈዉ የካቲት ባወጣዉ ዘገባ የመንግስት ወታደሮች መርዓዊ ከተማ ዉስጥ ጥር 20 ብቻ 45 ሰዎች ሳይገድሉ እንዳልቀረ ገምቷል።መንበሩን ኒዮርክ ያደረገዉ ሑዩማን ራይትስ ዋች እንደሚለዉ ጥር 20 የፋኖ ታጣቂዎች በከተማይቱ ላይ ጥቃት ሰንዝረዉ ካካቢዉ ከወጡ በኋላ የመንግስት ወታደሮች ለ6 ሰዓታት ባደረጉት የቤት ለቤት አሰሳና በየመንገዱ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መግደላቸዉንና ንብረት ማጥፋታቸዉን ምስክሮችና ሰለቦች አረጋግጠዉለታል። የካቲት 16 ደግሞ ፋኖ መርአዊ ከተማን እንደገና ካጠቃ በኋላ የመንግስት ወታደሮች 8 ሰዎችን በመደዳ ገድለዋል ይላል ሁማን ራይትስ ወች። የድርጅቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ላቲሺያ ባደር እንደሚሉት «የመንግስት ጦር በአማራ ክልል ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈፀመዉ የጭካኔ ግድያ፣ መንግስት በክልሉ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር እየጣርኩ ነዉ» የሚለዉን አባባሉን ባዶ ያስቀረዋል።በአማራ ክልል የደረሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ሒዩማን ራይትስ ወች ጠይቋል።ሑዩማን ራይትስ ወች ራሱ እንዳለዉ ሥለ ግድያዉ ለማጣራት 20 ሰዎችን በስልክ አነጋግሯል፤ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተለጠፉ ቪዲዮችንና የሳተላይት ምስሎችን መርምሯል።ዘገባዉን የካቲት ማብቂያ ላይ ለኢትዮጵያ መንግስት ቢልክም መልስ አለማግኘቱን አስታዉቋልም። የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ እንደዘገበዉ የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ዛሬ ቢጠየቁም «አጥጋቢ» መልስ አልሰጡም። የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ግን ባለፈው የካቲት ለዶቸ ቬለ በሰጡት መግለጫ “የመከላከያ ኃይሉ የትኛውንም ዐይነት ሲቪል ዒላማ አላደረገም” ብለዉ ነበር።
ናይሮቢ-ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር አባረረች፣ የራስዋንም ጠራች
ሶማሊያ በመቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደርን ለምክክር በሚል ከሐገሯ አባረረች፣ የራስዋንም ከአዲስ አበባ ጠራች። ፑንትላንድና ሶማሊላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆስላ ፅሕፈት ቤቶችም እንዲዘጉ አዘዘች።የሶማሊያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ሶማሊያ አዲሱን ርምጃ የወሰደችዉ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባቷ ነዉ።ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግስትነት እዉቅና ከሌለዉ ከሐርጌሳ መንግስት ወደብ ለመከራየት ከተስማማች ወዲሕ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ ግንኙነት ተበለሻሽቷል።ስምምነቱ ገቢር ከሆነ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ 20 ኪሎሜትር ወደብ ለ50 ዓመት ትኮናተራለች፣ ለሶማሊላንድ ደግሞ የመንግስትነት እዉቅና ትሰጣለች።የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ግን ስምምነቱን በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ «ወረራ» በማለት አዉግዞታል።
አዲስ አበባ-የተወሳሰበዉ የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነት
የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሞቃዲሾ ሥለማባረሩና የኢትዮጵያ የቆንስላ ፅሕፈት ቤቶችን ሥለመዝጋቱ የኢትዮጵያ መንግስት እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በይፋ ያለዉ ነገር የለም።ሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ የኢትዮጵያ የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ሥለ ጉዳዩ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ አስታዉቀዋል።የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ቃል አቀባይ ደግሞ ጋዜጠኞች ላቀረቡት ለጥያቄ መልስ አልሰጡም-እንደ ሮይተርስ።በተያያዘ ዜና የሶማሊያዋ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር የፑንትላንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከትናንት ጀምሮ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ነዉ።ፑትላንድ ባለፈዉ ቅዳሜ ከሶማሊያ ፌደራዊ ሪፐብሊክ አስተዳደር አባልነት እራስዋን አግልላለች።የጉብኝቱ ጊዜና አላማ በግልፅ ባይነገረም የሞቃዲሾ ባለስልጣናት የዛሬዉን ርምጃ የወሰዱት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችዉ የመግባቢያ ዉል ምክንያት ብቻ መሆኑ ታዛቢዎችን አጠራጥሯል።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ግን የፑንትላንድ ባለስልጣናት ጉብኝት ከዚሕ ቀደም የነበረ ግንኙነትን ለማጠናከር እንጂ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳነስ ያለመ አይደለም።
ባህርዳር-የአማራና ትግራይ ክልልሎች የድንበር ግጭት
ባለፉት ሳምንታት በአማራና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የታየዉ የግጭት አዝማሚያ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው ሲል የኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአማራና ትግራይ ክልል የታዩ «ትንኮሳዎች» ያሉት ጠብ ተቀባይነት የሌለዉና የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ብለዉታል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው አካባቢዎች በኢፌድሪ ህገመንግስት መሰረት እንደሚፈታ ያመለክታል፡፡የማንነትና የወሰን ጥያቄ ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው በህዝበ ውሳኔ ብቻ መሆኑንም ዶ/ር ለገሰ ጠቁመዋል።
የወሰንና የማንነት ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ጉዳዩ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የመከላከያ ሰራዊት ከየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር በመሆን ሰላሙን እንደሚጠብቅም ሚኒስትሩ ገልጠዋል፡፡የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን እንደዘገባዉ የአማራና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት አስተያየት ለማካተት ያደረገዉ ሙከራ አልተሳካለትም።
ብራስልስ-የኔቶ 75 ዓመት በዓል
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO-በእንግሊዝኛ ምፅሩ) የተመሠረተበት 75ኛ ዓመት ዛሬ ብራስልስ-ቤልጂግ ዉስጥ እየተከበረ ነዉ።የዓለም ብቸኛዉ የጦር ተሻራኪ ድርጅት የምሥርታ በዓልን ለማክበር የድርጅቱ አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ከትናንት ጀምሮ ብራስልስ ዉስጥ ተሰብስበዋል።ዛሬ ጠዋት «አገልግሎት ሲሰጡ ለሞቱ» የአባል ሐገራት ወታደሮች መታሰቢያ ሐዉልት አበባ ጉንጉን በማኖር የተጀመረዉ ስርዓት፣በኬክ ቆረሳ፣ በጉብኝት፣ ዉይይትና እና ንግግር ተከብሯል።ኔቶ የተመሰረተዉ የሶቭዬት ሕብረትንና የምሥራቅ አዉሮጳ ተባባሪዎቿን ኃይል እንዲቋቋም ታስቦ ነዉ።ሶቭየት ሕብረት ፈራርሳ፣ተከታዮችዋም ራሱን ኔቶን ቢቀየጡም የጦር ድርጅቱ ዛሬም በ75 ዓመቱ ከሩሲያ ጋር እንደ ተፋጠጠ ነዉ።ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶልተንበርግ እንደሚሉት ድርጅታቸዉ ለአዉሮጳና ለአሜሪካ ደሕንነትና ትብብር አስፈላጊ ነዉ።
«አዉሮጳ ለደሕንነቷ ሰሜን አሜሪካን ትፈልጋለች።ፍትሐዊ የሸክም መጋራት አስፈላጊ ነዉ።አዉሮጳ በጣም የበለጠ እያዋጣት ነዉ።በዚሕ ዓመት አብዛኞቹ የኔቶ አባላት ቢያንስ ቢያንስ ካጠቃላይ አመታዊ የሐገር ዉስጥ ምርታቸዉ 2 በመቶዉን ለመከላከያ ያዉላሉ።በዚያዉ መጠን ሰሜን አሜሪካም አዉሮጳን ትፈልጋለች።»
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 4፣ 1949 ዋሽግተን-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ሲመሰረት 12 አባላት ነበሩት።ዘንድሮ አባላቱ 32 ደርሰዋል።በዛሬዉ ድግስ ላይ የተካፈሉት የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊከን የቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት ሁለተኛ ትልቅ ሪፐብሊክ ዩክሬንም የድርጅቱ አባል መሆኗ እንደማይቀር አስታዉቀዋል።
ሎንደን-የብሪታንያ የሕግ ባለሙያዎች መንግስታቸዉ ለእስራኤል ጦር
የብሪታንያ መንግስት ለእስራኤል ጦር መሳሪያ መሸጡን እንዲያቋርጥ የብሪታንያ ዳኞችና የሕግ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት ጥያቄና ግፊት እንደቀጠለ ነዉ።ከ6 መቶ የሚበልጡ ዳኞችና የሕግ ባለሙያዎች ለጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክ መንግስት በፃፉት ባለ 17 ገፅ ደብዳቤ ብሪታንያ ለእስራኤል ጦር መሳሪያ መሸጧ ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስና በጦር ወንጀለኛ አባሪ-ተባባሪነት ያስጠይቃታል።ዛሬ ደግሞ ሶስት የቀድሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ጥሪዉን የሚያቀርበዉን የሕግ ባለሙያዎች ስብሰብ ተቀይጠዋል።እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ፍልስጤሞች ላይ የምትፈፅመዉ ግድያ፣ ግፍና የርዳታ እሕል እገዳ በቅርብ ተባባሪዎችዋ ሳይቀር እያስወቀሳት ነዉ።በሌላ ዜና የእስራኤል ጦር ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ ከገደላቸዉ 7 የርዳታ ድርጅት ሰራተኞች የ6ቱ አስከሬን ዛሬ ጠዋት ግብፅ ገብቷል።ሰባተኛዉ የዚያዉ የጋዛ ተወላጅ ነዉ።የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የእስራኤል ጦር ካለፈዉ መስከረም 26 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ላይ በከፈተዉ ጥቃት በትንሽ ግምት ከ33ሺሕ በላይ ሕዝብ ጨርሷል።ከ70 ሺሕ በላይ አቁስሏል።ሆስፒታሎች፣ ትምሕርት ቤቶች፤ የርዳታ ማከፋፋዮችን ጨምሮ አብዛኛዋን ጋዛን አዉድሟታል። የእስራኤል ባለስልጣናት እንደሚሉት እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግስታት በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ መስከረም 26 ደቡባዊ እስራኤል ላይ በከፈተዉ ጥቃት 1140 ሰዎች ገድሏል።ከ130 ያክል እስካሁን እንዳገተ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ