1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016

በካፍ እገዳ የተጣለበት የአዲስ አበባ ስታዲየም በርካታ እድሳቶች ቢደረጉለትም ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም ። ለመሆኑ ደጋፊዎች ስታዲየሙ ውስጥ ለምን እንዲታደሙ አልተደረገም? የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በቡድኑ ታሪክ እጅግ ፈጣን በተባለ ግብ የፈረንሳይ አቻውን አሸንፏል ። ሌሎችም፦

https://p.dw.com/p/4e6Sj
እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየም
እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየም በርቀትምስል Omna Tadel

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በካፍ እገዳ የተጣለበት የአዲስ አበባ ስታዲየም በርካታ እድሳቶች ቢደረጉለትም ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም ። አዲስ የተገጠሙት የስታዲየሙ ወንበሮች ባለፈው ሳምንት ከሌሶቶ ጋ በነበረው የወዳጅነት ግጥሚያ ባዶ ነበሩ ። ለመሆኑ ደጋፊዎች ስታዲየሙ ውስጥ ለምን እንዲታደሙ አልተደረገም?  እድሳቱስ ምን ይመስላል? በስታዲየሙ ታድሞ ከነበረ የስፖርት ጋዜጠኛ ጋ ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። በ13ኛው አፍሪቃ ጨዋታዎች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለስ ተገልጧል ። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በቡድኑ ታሪክ እጅግ ፈጣን በተባለ ግብ የፈረንሳይ አቻውን አሸንፏል ። ኢትዮጵያውያን  በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በተለያዩ የዓለማት ሃገራት የተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ላይ አሸንፈዋል ።

አትሌቲክስ

ጋና አክራ ውስጥ በተከናወነው የመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች ተሳትፎ የስምንተኛ ደረጃ ያገኘው የኢትዮጵያ ቡድን ልዑክ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ እንደሚገባ ተዘገበ ። በውድድሩ የኢትዮጵያ ቡድን 9 የወርቅ፤ 8 የብር፤ 5 የነሐስ በድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን አግኝቷል ። ሞሪሺየስ በ9 የወርቅ፤ ኬንያ በ8 እንዲሁም ኤርትራ በ7 የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያን ተከትለው ከ9ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። 

እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየም
እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየም በርቀትምስል Omna Tadel

በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት 1ኛ የወጣችው ግብጽን የሚስተካከል አልተገኘም ። ግብፅ በአጠቃላይ 192 ሜዳሊያዎችን ስትሰበስብ 103ቱ የወርቅ ናቸው ። ቀሪዎቹ 47 የብር እና 42 የነሐስ ። ናይጄሪያ በ47 የወርቅ ሜዳሊያ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፤ ደቡብ አፍሪቃ በ32 የወርቅ ሜዳሊያ የሦስተኛ ደረጃ ይዛ ውድድሯን አጠናቃለች ።

ባለፈው ቅዳሜ በተጠናቀቀው የአፍሪቃ ጨዋታዎች፦ እግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፤ ነጻ ትግል፤ ባድሜንተን፤ የውኃ ዋና፤ ጁዶ፤ ቴኳንዶ፤ ብስክሌት፤ ቴኒስን ጨምሮ በ23 የስፖርት ዘርፎች ግጥሚያዎች ይኖራሉ ።  የኢትዮጵያ ቡድን የተሳተፈባቸው የውድድር ዘርፎች፦እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውኃ ዋና፣ የጠረጴዛ እና የሜዳ ቴኒስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ዓለም ዓቀፍ ቴኳንዶ እና ቡጢ ናቸው ። አብዛኞቹ ሜዳሊያዎች የተገኙትም በዋናነት በሩጫው ዘርፍ ነው ።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በተለያዩ የዓለማት ሃገራት የተደረጉ የሩጫ ውድድሮች ላይ አሸነፊ ሆነዋል ። ትናት እሁድ የቻይና ውዢ ከተማ ውስጥ በተካሄደው የማራቶን ውድድር አትሌት ታዱ አባተ ቀዳሚ በመሆን አሸንፏል። ታዱ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት 06 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ወስዶበታል። በውድድሩ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አባይ ዓለሙ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ሆኗል። ኬንያዊው ኒኮላስ ኪሪዋ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በውድድሩ በሴቶች ዘርፍ ኬንያዊቷ ቬሮኒካ ንጄሪ ማይና 2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ በመሮጥ አሸንፋለች። ሌላኛዋ የቻይና ከተማ ቼንግዱ ባስተናገደችው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል። ውድድሩን ያሸነፈው ፈቃዱ መርጋ በ2 ሰዓት 16 ደቂቃ ከ9 ሰከንድ በማጠናቀቅ ነው ። አትሌት በለጠ መኮንን ደግሞ 2ኛ ወጥቷል ።የመጋቢት 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየም
እድሳት የተደረገለት የአዲስ አበባ ስታዲየም በርቀትምስል Omna Tadel

ከዚያው ከቻይና ሳንወጣ ሁዋን ከተማ ውስጥ በተደረገ ሌላ የማራቶን ውድድርም በሴቶች ምድብ አትሌት ማሬ ዲባባ  ቀዳሚ ሆና ጨርሳለች ። ማሬ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት 25 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ወስዶባታል። ጣልያን ሚላን ባስተናገደችው በሌላ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ አትሌት አንችናሉ ደሴ 1 ሰዓት 07 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት አሸንፋለች ።

እግር ኳስ

የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም ።

ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አላሟላም በሚል ጨዋታዎችን እንዳያካሂድ በካፍ ታግዶ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ላለፉት ሦስት ዓመታት በዕድሳት ላይ ቆይቷል ። የዓለምአቀፍ እና አህጉራዊ ውድድሮች ለማስተናግድ ብቁ እንዲሆን ለማስቻል ሥራዎች መሠራታቸውን የኢፌድሪ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ጠቁሟል ። በአሁኑ ወቅት የስታዲየሙ እድሳት 97 በመቶ ላይ ይገኛልም ብሏል ። ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ጥቂት ወራት ብቻ እንደሚፈጅም ተጠቁሟል ። የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከሌሶቶ ጋ መጀመሪያ 2 ለ1 ተሸንፎ በመልሱ ጨዋታ 2 ለ1 ሲያሸንፍ አዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታውንም የስታዲየሙንም ይዞታ ተመልክቷል ።  

ከስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ጋ የተደረገው ሙሉ ቃለ-መጠይቅ

ዖምና እንደተመለከተው ከሆነ፦ የስታዲየሙ የመሮጫ ሳር ግን የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌድሬሽን ያስቀመጠውን መመሪያ የሚያሟላ አይደለም ። ኢትዮጵያ ከሌሶቶ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በተለይም ኳስ ለመቆጣጠር እጅግ የማይመቻ ሜዳ መሆኑ ታይቷል ።

በዕድሳቱ ስታዲየሙ አዲስ የተመልካቾች ወንበር፣ የክቡር ትሪቡን መቀመጫዎች፣ ለመገናኛ አውታር ተቋማት የሚገለግሉ ክፍሎች ተሠርተውለታል ። የመልበሻ ክፍሎቹም እንዲሰፉ ተደርገዋል ። የመሮጫ መም ሥራም እንዲመኖር ይጠበቃል ። የመጋቢት 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የአዲስ አበባ ስታዲየምን ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልቶ ለማጠናቀቅ ቀሪ ሥራዎች ከሦስት ወራት በላይ እንደማይፈጅ በባሕል እና ስፖርት ሚንስትር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ከዚህ ቀደም ለዶይቸ ቬለ ዐስታውቀው ነበር ። ሚኒስቴር ዴኤታው በተለይ ከዶይቸ ቬለ (DW) ጋ ዛሬ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ ያ ግምታዊ ሐሳባቸው መሆኑንም አክለው ነበር ።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በወዳጅነት ግጥሚያ ቅዳሜ ዕለት ፈረንሳይን ሊዮን ውስጥ ማሸነፉ ለቡድኑ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጠ ። ባለፉት ጊዜያት ተደጋጋሚ ሽንፈትን ላስተናገደው ቡድን በእርግጥም ድሉ በራስ መተማመን ለማጎልበት እንደሚረዳው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን ተናግረዋል ።

ለሦስት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ርቆ የነበረው የቶኒ ክሮስ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ዳግም መመለስ ለቡድኑ ወሳኝ መሆኑ ይነገራል
ለሦስት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ርቆ የነበረው የቶኒ ክሮስ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ዳግም መመለስ ለቡድኑ ወሳኝ መሆኑ ይነገራልምስል Alexander Hassenstein/Getty Images

«የአሰላለፍ ለውጡን ያሰበበት የቡድናችን መደበኛ አሰልጣን ማድስ ቡትገራይት ነው እጅግ ድንቅ ሥራ ነው! ለቡድናችን በራስ መተማመን ወሳኝ የሆነ ፍጹም ምርጥ ግብ።»

የብሔራዊ ቡድኑ እና የሪያል ማድሪድ አማካይ ተጨዋች ቶኒ ክሮስ የቅዳሜው ድል ጀርመን በቅርቡ በምታዘጋጀው የአውሮጳ እግር ኳስ ፉክክር ላይም  አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብሏል ።

«አንድ ወሳኝ ርምጃ ወደፊት የተራ,መድን ይመስለኛል ከአውሮጳ ዋንጫ ውድድር በፊት የመጨረሻ እድላችን እንደነበር ለሁላችንም ቀስ ብሎ ተገልጦልን ነበር ስሜቱንም በትንሹም ቢሆን ለአውሮጳ ውድድሩ ይዘነው እንሄዳለን ። » የካቲት 26 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ለሦስት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ርቆ የነበረው የቶኒ ክሮስ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ዳግም መመለስ  ለቡድኑ ወሳኝ መሆኑ አሰልጣኙ ተናግረዋል ። በጀርመን ፈጣኑ ግብ በሰባት ሰከንዶች ውስጥ ሲቆጠር ኳሱን በቀጥታ ከመሀል ለግቶ ለግብ አስቆጣሪው ፍሎሪያን ቪርትስ ያደረሰው ይኸው ቶኒ ክሮስ ነው ። ካይ ሐቫርትስ ሁለተኛውን ግብ በ48ኛው ደቂቃ ላይ ለጀርመን አስቆጥሯል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከ70 ዓመታት በኋላ በመለያው ላይ ከሚያደርገው የአዲዳስ ምልክት ወደ ተቀናቃኙ ናይክ መቀየሩ ጀርመን ውስጥ ብዙ መነጋገሪያ ሆኗል
የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከ70 ዓመታት በኋላ በመለያው ላይ ከሚያደርገው የአዲዳስ ምልክት ወደ ተቀናቃኙ ናይክ መቀየሩ ጀርመን ውስጥ ብዙ መነጋገሪያ ሆኗልምስል picture alliance/dpa/Revierfoto

በነገራችን ላይ የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከ70 ዓመታት በኋላ በመለያው ላይ ከሚያደርገው የአዲዳስ ምልክት ወደ ተቀናቃኙ ናይክ መቀየሩ ጀርመን ውስጥ ብዙ መነጋገሪያ ሆኗል።  በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎች ዓርማው መለወጡ እንዳበሳጫቸው ገልጠዋል።  ብሔራዊ ቡድኑ መለያው ላይ የአዲዳስ ዓርማን ትቶ ወደ ናይክ የለወጠው ናይክ ድርጅት አዲዳስ ከሚከፍለው የማስታወቂያ ክፍያ በዓመት 100 ሚሊዮን ዩሮ ግድም የበለጠ ለመክፈል በመስማማቱ ነው ተብሏል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ