የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር መበራከት
ዓርብ፣ ኅዳር 27 2017በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የተሰዳጁ ቁጥር ከፍ ይላል የተመድ
«በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከበርካታ ችግሮች ጋር ተጋፍጠናል፤ በዚህም በዓለም ላይ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ናቸው ዋጋ የሚከፍሉት። ግጭቶች እና በርካታ ግጭቶች የሚያስከትሏቸውን ተጽዕኖዎች እያስተናገድን ነው፤ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ ቀውሶች እና የበለጠ ኃይለኛ ጭካኔንም ተጋፍጠናል።»
እንዲህ ያሉት በተመድ የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ቶም ፍሌቸር ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ረድኤት አቅራቢ ድርጅቶቹ አቅማቸውን የሚፈታተን የስደተኛ እና የተፈናቃይ ብዛት በየቦታው መኖሩ ነው የተገለጸው።
የመንግሥታቱ ድርጅቱ የስድተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በመላው ዓለም ከ123 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለግዳጅ መፈናቀል መዳረጋቸውን አመልክቷል። በያለበት እየተባባሱ የሄዱት ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች በመጪው ዓመት የሰዎችን መፈናቀል እና መሰደድ ሊያባብሰው እንደሚችልም ከወዲሁ ስጋቱን ገልጿል። የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱ ጥንቃቄና በቂ በጀት የሚያስፈልገው መሆኑን በማመልከትም በርካቶች በየቦታው ለችግር ተጋልጠው መርዳት አልቻልንም በሚል ተስፋ መቁረጥ ግን ሊታሰብ እንደማይገባ ጄኔቫ ላይ በተካሄደው የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የተገኙት የUNHCR የበላይ ሀላፊ ፊሊፖ ግራንዴ ተናግረዋል።
የስደተኞቹን ቁጥር ያበራከተው በአንድ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የግጭቶቹ መብዛት ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ቶም ፍሌቸር በበኩላቸው፤ አንዳንዶቹ ተራዝመው 10 ዓመታትን ማስቆጠራቸውንም አንስተዋል።
«ስለዚህ ሌሎች ከመጀመራቸው አስቀድሞ ግጭቶችን እየቋጨን አይደለም። እናም እነዚያ ግጭቶች ጭካኔ የተሞላባቸው በመሆናቸው ሲቪሎች ላይ የሚያስከትሉት ተጽእኖ ከባድ ነው።»
ጋዛን፤ ሱዳንን እና ዩክሬንን በምሳሌነት የጠቀሱት ሀላፊው ዓለም አቀፍ ሕግን በጣሰ አካሄዳቸው የእርዳታ ሥራን አስተጓጉለዋል ነው ያሉት።
በጅቡቲ በኩል የተበራከተው የኢትዮጵያን ስደት
ይህ በእንዲህ እንዳለምዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM በጅቡቲ በኩል ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ወገኖች ቁጥርመጨመሩን አመልክቷል። ካለፈው ሰኔ አንስቶ እስከ ዘንድሮው ጥቅምት ወር ድረስም ከ18 ሺህ እስከ 200,600 የሚሆኑ መሰዳደቸውን ገልጿል። በጥቅምት ወር ብቻም በጅቡቲ በኩል ከ44 ሺህ በላይ የተሰዳጆች እንቅስቃሴ መመዝገቡንም ባወጣው መዘዝርዝር አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል 22,617ቱ ከኢትዮጵያ የተሰደዱ መሆናቸውንም ገልጿል።
እንደድርጅቱ የስደተኞች ቁጥር የጨመረው በአማራ ትግራይ ክልሎች ባለ ግጭት ምክንያት ሲሆን ብዙዎቹ ተሰዳጆች የጅቡቲን መስመር በመምረጣቸው ነው።
የተሰዳጆችን ሁኔታ ባልሆ፣ ጋላፊ፣ ዲካሂል እና አሊ ሳቢህ በተባሉ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ እንደሚመዘግብ ያመለከተው IOM በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 ብቻ 184,720 ከኢትዮጵያ የሄዱ ሰዎች በእነዚህ ቦታዎች በኩል አልፈዋል። ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ82 በመቶ መጨመሩንም አመልክቷል። IOM እንደሚለው በእነዚህ መቆጣጠሪያ ቦታዎች ካለፉት ተሰዳጆች መካከል 69 በመቶ የሚሁት አዋቂ ወንዶች ሲሆኑ 25 በመቶው ደግሞ አዋቂ ሴቶች ናቸው። ሕጻናቱ ከሁለቱም ጾታ በጥቅሉ ስድስት በመቶ መሆናቸውንም ተገልጿል።
በጥቅምት ወር ለወትሮው በአካባቢው ተከማችተው የነበሩ ስደተኞች የየመንና የጅቡቲ ባለሥልጣናት በጋራ በሚያደርጉት የተጠናከረ ቁጥጥር ምክንያትም ወደ የመን የሚያሻግሩ ጀልባዎች ባለመኖራቸው ብዙዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውንም አመልክቷል። የየመን ባለሥልጣናት በወደብ አካባቢ የሚያደርጉት ቁጥጥር በመጥበቁም ባለፈው መስከረም ወር 1,561፤ ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ 1,567ቱ በግዳጅ እንዲመለሱ ማድረጋቸውንም ጠቅሷል። ጥቅምት ወር ላይ ከየመን በግዳጅ እንዲመለሱ ከተደረጉት መካከል 55 የሚሆኑት ባሕር ላይ ባጋጠመ አደጋ ሰምጠው መሞታቸውን ነው IOM ያመለከተው።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ