1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ የሰላም ተልዕኮ እና የጀርመን ሚና

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6 2008

የተመድ በማሊ የሚያካሂደው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እጅግ አዳጋች እየሆነ ሄዶዋል። የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት በዚችው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገር ያሰማራው ሰላም አስከባሪ ጓድ ወታደሮችም በታጣቂ ቡድኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ዒላማ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1Gpl5
Mali Deutschland Bundeswehr Ausbilder im Trainings Camp in Koulikoro
ምስል picture-alliance/dpa/P. Steffen

የማሊ የሰላም ተልዕኮ እና የጀርመን ሚና

አንድ የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ጀርመን የጓዱን ተልዕኮ ለማጠናከር ስትል በማሊ የጀመረችውን ትብብር በቅርቡ ለማስፋፋት ወስናለች።የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እንዳስታወቁት፣ ሃገራቸው የብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮችን የቱዋሬግ ዓማፅያን ወደሚንቀሳቀሱበት እና የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ወዳልሆነበት ሰሜናዊ ማሊ ለመላክ በማሰላሰል ላይ ትገኛለች። እስካሁን በደቡብ ማሊ የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮን ተቀላቅሎ የተሰማሩት 200 የጀርመን ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች በቅርቡ በምህፃሩ «ሚኑስማ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ በሰሜን ማሊ የጀመረውን ተልዕኮ በማጠናከር ስራ ሊተባበሩ ስለሚችሉበት ጉዳይ በቅርቡ ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችል ነው የተገለጸው።

የጀርመን የፍሪድሪሽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ያን ፋህልቡሽ የጀርመን መከላከያ ሰራዊት ሚኑስማን መተባበሩ ለማሊ የፀጥታ ሁኔታ ጠቃሚ ነው ይላሉ።

Symbolbild - Minusma Mali
ምስል Getty Images/AFP/H. Kouyate

«ሚኑስማ በተቻለው መጠን በማሊ የተወሰነ መረጋጋት ለማውረድ፣ የማሊን የመንግሥት መዋቅር ለማበረታታት እና ለማረጋገጥ እየሞከረ ነው። የማሊ መንግሥት በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሰሜኑ ክፍል ይህንን ለማድረግ ብቁ አይደለም።»

የዓለሙ መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ከረጅም እና ቀላል ያለነበረ ድርድር በኋላ ሰሜናዊ ማሊን ለማረጋጋት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነትን በመቆጣጠር ላይ ይገኛሉ። እንደሚታወሰው፣ የማሊ መንግሥት እና በርካታ በሃገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የቱዋሬግ ዓማፅያን ቡድኖች የሚጠቃለሉበት በምህፃሩ «ሲ ኤም ኤ» የሚባለውየአዛዋድ ንቅናቄዎች አስተባባሪ ህብረት ባለፈው ሰኔ ወር ነበር የሰላሙን ስምምነት የተፈራረሙት፣ በጎርጎሮሲያዊው 2012 ዓም የተፈጠረውን ውዝግብ ማብቃት ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሰላም ስምምነት ለሰሜናዊ ማሊ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር ይሰጣል።

ጀርመን በተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ ትብብሯን ከአሁን በበለጠ መልኩ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ባለፉት ጊዚያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ የተለያዩ ጉባዔዎች ላይ ሲናገሩ ተሰምተዋል። ከዚህ በመነሳት ባለፉት ጊዚያት የጀርመናውያኑ ፕሬስ በርሊን የሚገኘው የሃገሩ መከላከያ ሚንስቴር ብሔራዊው የመከላከያ ሠራዊት በማሊ የጀመረውን ትብብር ሳያስፋፋ እንደማይቀር ጠቁመው ነበር።

Algerien Mali Waffenruhe in Algier vereinbart Bilal Ag Acherif und Ramtane Lamamra
ምስል F. Batiche/AFP/Getty Images

ጀርመን የማሊ ተልዕኮዋን በማጠናከር ተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮችን በመላክ አለመላኩ ጥያቄ ላይ ውሳኔ ከማሳለፏ በፊት ፣ ሁኔታውን በቦታው በመገኘት ለመመዘን ትችል ዘንድ ወደ ማሊ አንድ የመከላከያ ሚንስቴር ጠበብት ቡድን ልካ ነበር። ይኸው የመከላከያ ሚንስቴር የጠበብት ቡድን ባለፈው ሳምንት የምርምሩን ውጤት ይዞ ወደ በርሊን የተመለሰ ሲሆን፣ ቡድኑ ያቀረባቸው ሀሳቦች ተቀባይነት ካገኙ ፣ ጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም ሳያበቃ በፊት አንድ የጀርመን ቃኚ ጦር ቡድን ወደ ማሊ ይላካል። በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም መጀመሪያ በሰላም ማስከበሩ ተግባር ለተሰማራው ጓድ ድጋፍ ፣ እንዲሁም፣ ጓዱ ለሚጠቀምበት የጦር ቁሳቁስ ከለላ የሚሰጡ የጦር ቡድኖችን አስከትሎ፣ ከዚያ በሚቀጥለው ሚያዝያ እና ሰኔ መካከልም አንድ የተጠናከረ የስለላ መረጃ ሰብሳቢ ሊያሰማራ ይችላል ነው የሚባለው። በዚህም የጀርመን ወታደሮች አደገኛ በሚባለው ሰሜናዊ ማሊ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊላኩ እንደሚችሉ ተጠቁሞዋል።

የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት በሚፈቅደው ተልዕኮ መሠረት፡ እስከ ሶስት መቶ ሀምሳ የሚሆኑ ጅመናውያን ወታደሮች ድረስ ማሊ ውስጥ ሊሰማሩ ይችላሉ። የማሊን ፀጥታ ሁኔታ ከብዙ ጊዜ አንስተው የሚከታተሉት በማሊ መዲና ባማኮ የጀርመን የፍሪድሪሽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ያን ፋህልቡሽ የጀርመን ብሔራዊ ጦር ወታደሮች በማሊ « ሚኑሰማ» በሚያካሂደው ተልዕኮ ውስጥ ወደፊት በውጊያ ተግባር ይሰማራሉ ብለው እንደማያምኑ በመግለጽ፡ አሁን ወደ ሰሜን ሚሊ ሊስፋፋ ይችላል የሚባለው የጀርመን ትብብር ለጀርመናውያኑ ወታደሮች ያን ያህል አደገኛ እንደማይሆን አመልክተዋል።

Tuareg-Truppen Mali
ምስል picture alliance/Ferhat Bouda

« እኔ እንደሚገባኝ፡ የጀርመን ትብብር በሰሜን ማሊ ለተሰማሩት የኔዘርላንድስ ወታደሮች አስፈላጊውን በማቅረብ ላይ የሚያተኩር ይመስለኛል። ይህ እውነት ከሆነ፡ ጀርመናውያኑ ወታደሮች በውጊያ አይሳተፉም፡ በዚህም የተነሳ የጀርመን ወታደር ሕይወት የሚጠፋበት አጋጣሚ በጣም ንዑስ ነው። »

የጀርመን ወታደሮች በሰሜን ማሊ ብዙ መንደሮች እና ከተሞች በቀላሉ የማይደረስባቸው በመሆኑ በተዋጊ ሄሊኮፕተሮች የሚታገዙትን የኔዘርላንድስ ወታደሮች የመርዳት ተልዕኮ ሊያካሂዱ እንደሚችሉ ነው የሚጠበቀው።

አንቶንዮ ካሽካሽ/አርያም ተክሌ