አርዕስተ ዜና
*በአማራ ክልል ጎጃም ቀጣና በፋኖ ትዕዛዝ ለሳምንት ተዘግቶ የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጠ ። መንገዶቹ መከፈታቸውን አንዳንድ ተገልጋዮች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።
*የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚፈቅድ አዋጅ ዛሬ ጸደቀ ። አዋጁ በሦስት ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁ ተገልጧል ።
*ሩስያ ከፍተኛ የጦር መኮንኗን ሞስኮ ውስጥ በተጠመደ ቦንብ ፍንዳታ አጣች ። የ54 ዓመቱ ሩስያዊ ሊውቴናንት ጄኔራል ከረዳታቸው ጋር ዛሬ ጠዋት የተገደሉት በእግር ተረግጦ በሚገፋ የኤሌክትሪክ መጓጓዣ ወይንም ስኩተር ላይ በተጠመደ ፈንጂ ፍንዳታ መሆኑ ተዘግቧል ።
ዜናው በዝርዝር
ባሕርዳር፥ ፋኖ የጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ተነሳ
በአማራ ክልል ጎጃም ቀጣና በፋኖ ትዕዛዝ ለሳምንት ተዘግቶ የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አንዳንድ ተገልጋዮች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። «ለምን ባለፈው ሳምንት እንቀስቃሴ አቆማችሁ ተብለን በፀጥታ አካላት አገልግሎት መስጠት አልቻልንም» ያሉ አሽከርካሪዎች ደግሞ ቅሬታቸውን ገልጠዋል ። ከሕዳር 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም እስከ ትናንት ታኅሣሥ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የፋኖ ኃይሎች ባስተላልፉት ትዕዛዝ በብዙ የጎጃም ቀጣናዎች የእንቀስቃሴ ገደቦች ተጥለው ቆይተዋል ። በእነዚህ ቀናት በኅብረተሰቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና መድረሱን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ሰሞኑን ገልፀውልን ነበር ። እገዳው ከዛሬ ጀምሮ በመነሳቱ በአብዛኛዎቹ የጎጃም አካባቢዎች የመጓጓዣ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የደንብጫ፣ የቢቸና እና የደብረወርቅ ከተሞች ነዋሪዎችና ተሳፋሪዎች ተናግረዋል ።
«ትራንስፖርት የመንግሥታ ያልሆነ ወይንም የሕዝብ ጭነቶች ምናምን እንደፈለገ እየተንቀሳቀሱ ነው ። የሕዝብ መኪኖች ደግሞ ሲቸንቶ ሲንቀሳቀሱ ዐይቻለሁ ። መናኸሪያ አካባቢ ወደ ደብረወርቅ አቅጣጫ ፊታቸውን አዙረው ዕያየሁ ነው ። አሁን ክፍት ነው፥ ደህና ነው ። እዛ ውስጥ ያሉትም እየተንቀሳቀሱ ነው ። ወደ ባሕርዳርም የሚመጣ ዐይቻለሁ፥ ወደ ግንደ-ወይንም ዐይቻለሁ ። ከደብረ-ወርቅ ቢቸና ከቢቸና ደብረ-ወርቅ አለ ። »
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ ከባሕርዳር ወደ አዴትና ሞጣ መስመር የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች የነበሩ ቢሆንም ሥራ አቁማችሁ ነበር በሚል የፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እንደሚፈጽሙ አንድ አሽከርካሪ ተናግረዋል ።
«አልሄድንም እዛ መከላከያ እና አድማ ብተናው እየተማቱ፥ በዚህ ምክንያት ። »
ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስና ድምፃቸው በአየር ላይ እንዳይውል ያስጠነቀቁን አንድ አሽከርካሪ ዛሬ ረፋድ 5 ሰዓት አካባቢ «አዴት ሀና» በተባለ ቦታ ላይ በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎች ጉዞ ከጀመሩ በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ በመንግሥት የፀጥታ አካላት መከልከላቸውን ገልጠዋል ። ለምን አሽከርካሪዎች በባሕርዳር - አዴት - ሞጣ መስመር አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን ያደረግነው የስልክ ጥሪ ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም ።
አ.አ፥ ኢትዮጵያ የባንክ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ክፍት የሚያደርግ አዋጅ ጸደቀ
የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚፈቅድ አዋጅ ዛሬ ጸደቀ ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የሚፈቅድ የባንክ ሥራ አዋጅን እና የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ማጽደቁ ተገልጧል ። በምክር ቤቱ በሦስት ተቃውሞ፤ በአብላጫ ድምፅ የጸደቀው አዋጅ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ገብተው በባንኩ ዘርፍ እንዲሰማሩ መንገድ ይከፍታል ተብሏል ። በምክር ቤቱ የዛሬ ውሎ፦ የአዋጁ መጽደቅ « የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ በማሳተፍ» ሊፈጠር ይችላል በተባለው መሻሻል «ለኢኮኖሚው ዕድገት ፋይዳው የጎላ» እንደሆነ ተገልጧል ። የምክር ቤት አባላት፦ «በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ፈቃድ መስጠቱ» ሊፈጥር ይችላል ስላሉት ሥጋትም ተናግረዋል ። «የሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል መረዳት ይገባል ሲሉ» የምክር ቤት አባላት ማስገንዘባቸውም ተዘግቧል ።
ምያንማር፥ ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ተማጽኖ
ምያንማር ውስጥ ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የሚመለከት የልዕኩ ቡድን ወደ ስፍራው ሊላክ ስለመሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለፀላቸው ቤተሰቦቻቸው በሀገሪቱ የሚገኙ ሰዎች ተናገሩ ። ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከ60 በላይ ቤተሰቦች ዛሬ ማግሰኞ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሄድ ጥያቄ አቅርበዋል ። የሚመለከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ለማነጋገር ተወክለው ወደ ውስጥ ከገቡ ሰዎች መካከል ታናሽ ወንድማቸው ምያንማር የተጓዘባቸው አቶ አስጨናቂ በቀለ የልዑካን ቡድኑ መቼ እንደሚጓዝ ጥያቄ አለማቅረባቸውን ጠቅሰዋል ። ሆኖም መንግሥት ቤተሰቦቻቸውን ካሉበት አስወጥቶ ለማምጣት ጉዳዩን በትኩረት እንደያዘው ተገልጾልናል ብለዋል ።
«ትናንትና የተወሰነ የሚሄድ ልዑካን ቡድን ዲፕሎማቶች ሄደው፤ እዛ ጉዳዩን አጥንተው፤ መነጋገር ካለበት አካላ ጋር ተነጋግረው ውጤት ለማምጣት መንገድ እንደጀመሩ ትናንት እንደፀደቀ ነግረውናል ። በዛ መንገድ ሄደው፤ ልጆቻችንን እንደሚያመጡ ነግረውናል ።»
የተሻለ የሥራ ዕድል ታገኛላችሁ በሚል በተለያየ ጊዜ ወደ ምያንማር የተጓዙ ወጣቶች ያለምንም ደሞዝ በቀን ከ18 ሰዓታት በላይ እንዲሠሩ እየተገደዱ «የከፋ ሁኔታ ውስጥ» መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ከዚህ በፊት ደጋግመው ገልፀዋል ። እነዚህ ዜጎች «በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች» ማታለል ደርሶባቸው መሄዳቸውን የገለፀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር «በችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለማስለቀቅ ጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከምያንማር የውጭ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስቴሮች ጋር የበይነ መረብ ስብሰባ» ማድረግ መጀመሩን ባለፈው ሳምንት መግለጡ ይታወሳል ።
ቤርሊን፥ የጀርመን ዋነኞቹ ፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻቸውን ሊያስተዋውቁ ነው
በጀርመን የፌዴራል ምክር ቤት (Bundestag) ትናንት ቤርሊን ውስጥ በተደረገው ታሪካዊ ድምፅ አሰጣጥ መራሔ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የመተማመኛ ድምፅ በማጣታቸው ዛሬ የምርጫ ዘመቻ ጀምሯል ። የክርስቲያን ዴሞክራቶች እና ክርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት (CDU/CSU)፤ የሶሻል ዴሞክራቶቹ (SPD)እንዲሁም አረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ዛሬ የምርጫ መርሐ ግብራቸውን ማስተዋወቅ ጀምረዋል ። ዖላፍ ሾልትስ ትናንት ታኅሣሥ 7 ቀን፣ የፌዴራል ጀርመን ታዕታይ ምክር ቤትን መተማመኛ ድምፅ ጠይቀው በመነፈጋቸው አዲስ አገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል ። በምክር ቤት የሶሻል ዴሞክራቶቹ (SPD)እና የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት(CDU)ቡድኖች እንዲሁም የአረንጓዴ ፓርቲዎቹም ምርጫው እሁድ፤ የካቲት 16 ቀን፤ 2017 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑ ቀደም ሲል ተዘግቧል ። አሁን የሚጠበቀው የጀርመን ርእሰ-ብሔር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ዳግም ምርጫው ይካሄድ አለያም አይካሄድ የሚለውን በ21 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ነው ። ምርጫው እንዲካሄድ የሚወስኑ ከሆነም በመጀመሪያ ምክር ቤቱን በይፋ ይበትናሉ ። ሽታየን ማየር ምርጫው በተቆረጠለት ቀን እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ቀደም ሲል ፍንጮችን ዐሳይተዋል ።
ሞስኮ፥ ከፍተኛ የጦር መኮንኗን ሞስኮ ውስጥ በተጠመደ ቦንብ ፍንዳታ ተገደሉ
ሩስያ ከፍተኛ የጦር መኮንኗን ሞስኮ ውስጥ በተጠመደ ቦንብ ፍንዳታ አጣች ። የ54 ዓመቱ ሩስያዊ የጦር መኮንኑ የተገደሉት በእግር ተረግጦ በሚገፋ የኤሌክትሪክ መጓጓዣ ወይንም ስኩተር ላይ በተጠመደ ፈንጂ ፍንዳታ መሆኑ ተዘግቧል ። በቦንብ ጥቃቱ የተገደሉት ሩስያዊ መኮንን የኒኩሊዬር፤ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል ጥበቃ ጓድ ኃላፊ ሊውቴናንት ጄኔራል ኢግር ኪሪዮቭ ናቸው ተብሏል ። የዩክሬን የደኅንነት አባላት ጄነራሉ ሞስኮው ውስጥ የተገደሉት በዩክሬን የደኅንነት አባላት ልዩ ዘመቻ መሆኑን ለሮይተርስ የዜና ምንጭ ተናግረዋል ። የሩስያ መገናኛ አውታሮች እደዘገቡት ሌላ አንድ ሰውም በጥቃቱ ተገድሏል ። የሩስያ የምርመራ ኮሚቴ ተወካይዋ ስቬትላና ፔትሬንኮ ዛሬ የደረሰውን ጥቃት አረጋግጠዋል ።
«የሩስያ የምርመራ ኮሚቴ ለሞስኮ፥ ዋና የምርመራ ክፍል፦ የሁለቱ ወታደሮች ግድያን እየመረመረ ነው ። በምርመራው መሠረት ሞስኮ ሪዛንስክ ፕሮስፔክት ባቡር ጣቢያ አጠገብ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ ደጃፍ ቦንብ ተጠምዶ ነበር ። ዛሬ ጠዋት (ማግሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን፣ 2017 ዓ.ም )በደረሰው የቦንብ ፍንዳታም የሬስያ ፌዴሬሽን የኒኩሊዬር፤ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል ጥበቃ ጓድ ኃላፊ ሊውቴናንት ጄኔራል ኢግር ኪሪዮቭ እና ረዳታቸው ተገድለዋል ።»
የሩስያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንሥትር የነበሩት የሩስያ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ ድሚትሪ ሜድቬዴቭ የዩክሬን አመራር ለድርጊታቸው ብርቱ የበቀል ጥቃት ይጠብቃቸዋል ሲሉ ዝተዋል ። ሞስኮ መኖሪያ መንደር ውስጥ የቦንብ ጥቃቱ የደረሰው የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጦራቸው ዩክሬን ውስጥ ስላገኘው ስኬት በቴሌቪዥን በተናገሩ በነጋታው ነው ።
ዋሽንግተን፥እሥራኤልና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርጉ ጫፍ ደርሰዋል ተባለ
እሥራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ጫፍ መድረሳቸውን አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን ተናገሩ ። የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ዛሬ ለፎክስ ኒውስ ተናገሩ ሲል ሮይተርስ የዜና ምንጭ እንደዘገበው፦ ተስፋ ማድረጉ ላይ ጥንቃቄ ቢያሻውም ስምምነቱ ግን ጫፍ ላይ ደርሷል ብለዋል ። የፍልስጥኤሙ ሐማስ በበኩሉ እሥራኤል ተጨማሪ መደራደሪያ ሐሳብ ካላቀረበች በተኩስ አቁም እና ታጋቾችን በመልቀቁ በኩል ለመደራደር ዝግጁ ነን ማለቱ ተዘግቧል ።