አርዕስተ ዜና
*የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው የአንድ የምክር ቤቱን አባል የአለመከሰስ መብት አነሳ ። ግለሰቡ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው፦ «የኮሪደር ልማት»ን ሽፋን በማድረግ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በፍትህ ሚኒስቴር በመጠርጠራቸው ነው ተብሏል ።
*የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በፕሬዚደንታዊ ምርጫው ተሸነፉ ። ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ግዛት የምርጫ ኮሚሽን ተቃዋሚው አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ በቅጽል ስማቸው «ኢሮ» የፕሬዚደንታዊ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ዛሬ ይፋ አድርጓል ።
*ሩስያ ዩክሬንን በጦር ኃይል ከወረረች ከ1000 ቀን በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩክሬን ጦር በዩናይትድ ስቴትስ የረዥም ርቀት ሚሳይል ሩስያን መምታቱን ዐሳወቀ ። የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስን ለማስፈራራት ዛሬ አዲስ የኑክሊየር መመሪያ ላይ መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል ።
ዜና በዝርዝር
አአ፥የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት አንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ተነሳ
ዛሬ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የአንድ የምክር ቤቱን አባል የአለመከሰስ መብት አነሳ ። ምክር ቤቱ አቶ ሰኢድ አሊ ከማል የተባሉት አባሉን የአለመከሰስ መብት ያነሳው ግለሰቡ «የኮሪደር ልማት»ን ሽፋን በማድረግ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በፍትህ ሚኒስቴር በመጠርጠራቸው ነው ተብሏል ። የምክር ቤቱ አባል ወንጀል መፈጸሙን የማረጋገጥ ሥልጣን የመደበኛ ፍርድ ቤቶች ሆኖ ቋሚ ኮሚቴው የተጠርጣሪ አባሉን የአለመከሰስ መብት ለማንሳት ግን በቂ አመላካች ሁኔታ ማግኘቱንም አስረድቷል ። ግለሰቡ የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሳሉ የኮሪደር ልማትን ሽፋን በማድረግ ያለአግባብር መኖሪያ ቤቶችን እና የንግድ ቤት በማፍረስ መጠርጠራቸው ተገልጧል ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብሮች ሙስና በመቀበል እና የመንግስት ይዞታን ከሕግ አግባብ ውጪ በማስተላለፍ መጠርጠራቸውም በምክር ቤቱ ተዘርዝሯል ።
«ጥር 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከሜክሲኮ እስከ ቄራ ላለው ዋና መንገድ ማስፋፊያ የሚሠራውን የኮሪደር ልማት ሽፋን 6 የመኖሪያ እና አንድ የንግድ ቤት መፍረስ የሌለባቸውን እንዲፈርሱ መመሪያ እና ትእዛዝ በመስጠት በባንክ ብድር ለገዛው እና ግምቱ 30 ሚሊዮን ለሚያወጣው ቤት 14 ሚሊየን ብር ለቤቱ ግዢ ብድር ክፍያ በመፈጸም የሙስና እና ሕገወጥ ገንዘቡን ሕጋዊ አድርጎ በማቅረብ ወንጀል መፈጸም ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል ።»
የምክር ቤቱ የሰላም ፍትኅና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ እንዳቀረበው፦ የግለሰቡ የአለመከሰስ መብት ይነሳልን ጥያቄ በፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያስላሴ ዘሚካኤል ፊርማና ማኅተም በሕግ አግባብ ጥያቄ መቅረቡን ገልጿል ። ዜናውን የላከልን የአዲስ አበባ ወኪላችን
ሥዩም ጌቱ ነው ።
ሆለታ፥ እገታ ፈጸሙ የተባሉ 3 ወጣቶች የ11 ዓመት ጽኑእ እስራት ተበየነባቸው
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በሆለታ ከተማ አስተዳደር ጋልገል ኩዩ ቀበሌ ልዩ ስሙ ካቢኔ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ወንጀል ፈችመዋል የተባሉ ሦስት ወጣቶች ላይ የ11 ዓመት ጽኑ እስራት ተበየነ ። ወጣቶች እራሳቸውን በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር በማስመሰል ወንጀሉን መፈጸማቸውም ተገልጧል ። በምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ሆለታ ከተማ የሰባት ዓመት ታዳጊን በማገት በሚሊየን ገንዘብ ጠይቀው እንደነበረም ተዘግቧል ። ጽኑእ እስራት የተበየነባቸው አጋቾች ወንጀሉን ፈጽመዋል የተባለበትን አከባቢ በሚገባ ያውቃሉ ተብሏል ። ብይን የተላለፈባቸው ወጣቶች ኤርሚያስ ሁንዴ፣ ብሩክ አብዮት እና ኢዩኤል ለማ የተባሉ መሆናቸውም ተገልጧል። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የዞኑ አቃቤሕግ ባለሥልጣን በሽምቅ መንግስትን በሚፋለሙት ታጣቂዎች ስም ሰዎችን በማገት ገንዝብ የመጠየቅ ወንጀል አሁን አሁን እየተበራከተ መምጣቱን ገልጠዋል ። በዜና መጽሄት ዝርዝር ዘገባ ይኖረናል ።
ካይሮ፥ የግብጽ ምክር ቤት የሀገሪቱን የመጀመሪያ የፍልሰተኞች ሕግ አጸደቀ
የግብጽ ምክር ቤት የሀገሪቱን የመጀመሪያ የፍልሰተኞች ሕግ አጸደቀ ። ሕጉ ፍልሰተኞች እና ስደተኞችን ለመቆጣጠር የወጣ መሆኑ ተገልጧል ። የመብት ተሟጋቾች ሕጉ ሰብአዊ መብትን ይጋፋል በሚል እንዳይጸድቅ ሲሟገቱ ነበር ። የግብጽ መንግሥት በበኩሉ፦ ሕጉ የጸደቀው የስደተኞች መብት ላይ አደጋ በመደቀኑ ነው ብሏል ። እd, የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኖች ኮሚሽን ከሆነ በአብዛኛው ከሱዳን እና ሶሪያ የሄዱ 800,000 የተመዘገቡ ስደተኞች ግብጽ ውስጥ ይገኛሉ ።
ሐርጌሳ፥የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ በምርጫው ተሸነፉ
የሶማሊላንድ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በፕሬዚደንታዊ ምርጫው ተሸነፉ ። ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ የምትጠራዉ ግዛት የምርጫ ኮሚሽን ተቃዋሚው አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ በቅጽል ስማቸው «ኢሮ» የፕሬዚደንታዊ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ዛሬ ይፋ አድርጓል ። ኢሮ በምርጫው 63.92% በማግኘት ሲያሸንፉ፥ ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ ከአሸናፊው በግማሽ ያነሰ 34.81% ድምፅ አግኝተዋል ። ሶማሊላንድ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1991 አንስቶ ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ራሷን ነጻ አገር አድርጋ ብታውጅም በየትኛውም የዓለም አገር ግን ዕውቅና አላገኘችም ። እንዲያም ሆኖ ግን በሕዝብ በሚመረጥ ፕሬዝደንት ትመራለች ። በምርጫው የተሸነፉት ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ በምርጫው ቀን ይህንኑ ተናግረዋል ።
«ዛሬ ለሶማሊላንድ ሕዝብ ታሪካዊ እና ወርቃማ ቀን ነው ። የምርጫ ቀን ነው፥ ሕዝቡ በሀገሪቱ ፕሬዚደንት እንዲሆን ለሚፈልገው ሰው ወይንም ፓርቲ ድምፅ ይሰጣል ።»
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ድምፁን በሰጠበት የሶማሊላንድ ምርጫ ውጤት ላይ የሦስቱ ፓርቲዎች ማለትም ዋዳኒ፤ ኩልሚዬ እና ካኣህ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ።ሶማሊላንድን ላለፉት ሰባት ዓመታት የመሩት ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር «የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት» መፈራረማቸው መዘገቡ ይታወሳል ። ስምምነቱ ተግባራዊ ቢሆን፦ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ዳርቻ ወታደራዊ የጦር ሠፈር እና የወደብ መገንቢያ ቦታ ታገኛለች ። ሶማሌላንድ በበኩሏ ኢትዮጵያ ከመላው ዓለም አገራት የመጀመሪያዋ ዕውቅና የምትሰጣት እንድትሆን ትሻለች ። በሶማሊላንድ ምርጫ ያሸነፉት አብዲራህማን ሞሐመድ ስምምነቱን እንደሚደግፉ ሰፋ ያለ ምልከታ ማሳየታቸውን ሮይተርስ የዜና ምንጭ አትቷል ።
ሞስኮ፥ ዩክሬን በዩናይትድ ስቴትስ ሚሳይል ሩስያን መታች
ሩስያ ዩክሬንን በጦር ኃይል ከወረረች ከ1000 ቀን በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩክሬን ጦር በዩናይትድ ስቴትስ የረዥም ርቀት ሚሳይል ሩስያን መምታቱን ዐሳወቀ ። የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስን ለማስፈራራት ዛሬ አዲስ የኑክሊየር መመሪያ ላይ መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል ። የዩናይትድ ስቴትስ ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከ1000 ቀናት ጦርነት በኋላ ዩክሬን በተደጋጋሚ ስትጠይቅ የነበረውን የረዥም ርቀት ጦር መሣሪያ ፈቅደዋል ። ሩስያ በዩክሬን በኩል ከተወነጨፉ ስድስት የረዥም ርቀት ሚሳይሎች አምስቱን አየር ላይ መትታ ማክሸፏን ገልጣለች ። እስካሁን በተደረገው ውጊያ የሩስያ ወታደሮች የዩክሬንን አንድ አምስተኛ ምድር መቆጣጠራቸውም ተዘግቧል ። ዩክሬን በአሁኑ ወቅት በጦር ግንባር በኩል በሰው ኃይል እጥረት መቸገሯንም የዩክሬን ጉዳይ ዐዋቂ ፖለቲካ ተንታኝ፣ ወታደራዊ አማካሪ እና ደራሲ ፍራንትስ ሽቴፋን ጋዲ ለሰሜን ጀርመን ማሠራጪያ ጣቢያ (NDR)ተናግረዋል ።
«በአሁኑ ወቅት ለዩክሬን ትልቁ ችግር በዚህ ላይ በደንብ ላስምርበትና፥ ከወታደራዊ ዕይታ አንጻር በጦር ግንባር ያለው የሰው ኃይል እጥረት ነው ። በዚያ ላይ ተጨማሪ የእግረኛ ጦር ሠራዊት ቢኖር እንኳ እዚያ ያሉትን የረዥም ርቀት ተጓዥ ጦር መሣሪያዎችን መተካት አይችሉም ።»
ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረ ከ33 ወራት በኋላም ቢሆን የዩናይትድ ስቴትስ የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎችን መጠቀሟ በጦርነቱ ተጽእኖ እንደሚኖረው ወታደራዊ ተንታኞች ተናግረዋል ። ያለ ዩናይትድ ስቴትስ ቀጥታ ተሳትፎ ሚሳይሎቹ ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም ያለችው ሩስያ በጦርነቱ ዩናይትድ ስቴትስ ቀጥታ ተሳትፎ አድርጋለች ብላለች ። ዩናይትድ ስቴትስ አዲሱ የሩስያ የኑክሊየር መመሪያ የሚደንቅ አይደለም ብላለች ።