የሞቃዲሾና አስመራ ንግግር አንድምታ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 19 2017የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህክ መሃሙድ ከሰሞኑ ወደ አስመራ አቅንተው እሮብ እለት ከኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መክረዋል፡፡መሪዎቹ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ብሎም ዓለማቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተዘግቧል። የእሮቡን የፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህክ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ውይይትን ተከትሎ የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሪዎቹ የውይይት ማጠንጠኛ የሶማሊያ መረጋጋት ለአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ያለውን ሚና ያጎላ ነው ይላል፡፡ "የሶማሊያን መረጋጋት ማረጋገጥ ለቀጣናው ሰላም ቁልፍ ነው" ያለው የኤርትራ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱ መሪዎች በዚህ ዙሪያ በጥልቀት መምከራቸውን አስረድቷል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር ከሁለት ወራት በፊት በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ሻክሮ ውጥረት ሲነግስ ግብጽ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ በአስመራ በደረሱት ስምምነት በወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲና ፖለቲካዊ ዘርፎች እንደሚተባበሩ አስረድተው ነበር፡፡
ምን ተወያይተው ይሁን?
ምንም እንኳ የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሪዎቹ ውይይት ላይ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ቢቆጠብም እየተገባደደ ባለው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ የተፈራረሙትን ስምምነትም አንስተው መምከራቸውን የዲፕሎማቲክ ምንጮች መረጃ ያሳያል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት ትውልደ ኤርትራዊው የጂኦፖለቲካዊ ተንታኝ አብዱራህማን ሰዒድ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የመሪዎቹ ውይይት ሁለት ርዕሶች ላይ እንደሚያጠነጥን እሙን ነው ይላሉ፡፡ “ውይይቱ አንደኛው በአንካራ ስምምነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተለይም ስለደህንነት የጋራ ስምምነት ያላቸው አገራት ስለሆኑ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አስመራ ሲያቀኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን በተመሳሳ እለት ወደ ካይሮ ልከዋል፡፡ እናም የአሁኑ ውይይት የጋራ ስምምነት ያላቸው ሶስቱ አገራት በተለይም ሁለቱ ኤርትራ እና ግብጽ ስለአንካራው ስምምነት ማብራሪያ ስለሚያስፈልጋቸው መነሳቱ ግልጽ ነው”ይላሉ፡፡
የአንካራው ስምምነት ግብጽና ኤርታራን ቅር ያሰኝ ይሆን?
የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ አብዱራህማን ሰዒድ ከግብጽ እና ኤርትራ ጋር የጋራ ስምምነት የነበራት ሶማሊያ ሳይጠበቅ ወደ ቱርክ ተጉዛ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሁለቱን አገራት ቅሬታ ውስጥ ሳያስገባቸውም አልቀረም ባይ ናቸው፡፡ “ ቅሬታ ሊሰማቸው ይችላል፤ ምክንያቱም ሀሰን ሼህክ መሃሙድ ሳያማክራቸው ነው ድንገት አንካራ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡ እናም የፕሬዝናንቱና ውጪ ጉዳዩ የሁለቱ አገራት ጉዞ እሱን ጉዳይ ለማስተባብል ይመስላል” ሲሉም ጉዳዩ ከአንካራው ስምምነት ጋር በቀጥታ ሊገናኝ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ንግግር አንድምታ
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ያሰሩት ስምምነት ምናልባትም አስቀድሞ ሶስቱ አገራት በአስመራ ያኖሩትን የሶስትዮሽ ስምምነት ይሽር ይሆን በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የፖለቲካ ተንታኙ፤ ለዚህ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል፡፡ “የአስመራውና የአንካራው ስምምነቶች ተደጋጋፊ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚለውን ሃሳባቸውን ያጋሩን አቶ አብዱራሃማን፤ ምናልባትም ኢትዮጵያን ወደ አንካራው ስምምነት የወሰዳት የአስመራው ስምምነት ሊሆን እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የአንካራው ስምምነት ቀጣይ ቴክንካዊ ውይይት እና ስለ ግብጽ ወታደሮች የሶማሊያ ተሳትፎም ሌላው ሊነሳ የሚችል ጉዳይ ነው በማለትም በቀጣይ የሚፈጠሩ ጉዳዮች አንዱን ስምምነት አዳክሞ ሌላውን ልያጠነክር የሚችልበትም እድል መኖሩን አመልክተዋል፡፡
የአገራቱ ውይይት ግብጽ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ተልእኮ ለማዋጣት በምትጥርበት በአሁን ወቅት መሆኑም ልብ ይለዋል፡፡ ኤርትራ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ ሰራዊትን ቢያንስ ላለፉት አራት ኣመታት ስታሰለጥን ቆይታለች፡፡ ይህ ደግሞ የባህር ሃይልና ሜካናይዝድንም ያጠቃልላል፡፡ ሀሰን ሼህ መሃሙድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ሶስት ዓመታቸውን ሳይደፍኑ እንኳ ስምንት ጊዜ ወደ አስመራ ተመላልሰዋል፡፡ አራቱ ደግሞ በዚህ ኣመት ብቻ መሆኑ ነው፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር