የሕክምና የባለሙያው ውሎ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2012በመላው ዓለም በኮቪድ 19 ማለትም ኮሮና ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3,6 ሚሊየን መብለጡን፤ የሟቾችም ብዛት ከ252 ሺህ ማለፉን የጆንሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ከሰዓታት በፊት ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ተሐዋሲው በየሃገራቱ በተስፋፋት በዚህ ወቅት ሰዎችን በማስታመሙ ዘርፍ የተሠማሩት የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሌሎችን ሕይወት ለማትረፍ እየሠሩ ነው።
ኮቪድ 19 ማለትም የኮሮና ተሐዋሲ ወደ ኢትዮጵያን መግባቱን ተከትሎ ችግሩን ለመቆጣጠር የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተለይ ወረርሽኙ የከፋ ከሆነ ሊያስከትለው የሚችለውን ቀውስ ቀድሞ ለመከላከል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማግለያና ማገገሚያ ቦታዎች በከፍተኛ ትኩረት ሲዘጋጁ ሰንብተዋል። የመታከሚያ ሆስፒታሎች ተለይተዋል፣ የኮሮና ተሐዋሲ መመርመሪያ መሳሪያዎችም በአንዳንድ አካባቢዎች ሥራ ጀምረዋል፣ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳትም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሮችም እየተካሄዱ ነው፤ በዚህ ረገድ ባለሀብቶች፣ ግለሰቦችና ድርጅቶችም የየራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው።
እንደሌሎች አከባቢዎች ሁሉ በአማራ ክልልም የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ለህሙማኑ መታከሚያ የሚሆን ሆስፒታል ማዘጋጀትና ባለሙያዎችን መመደብ አንዱ ነው። በክልሉ የመጀመሪያው የኮሮና ተሐዋሲ ታማሚዎች መታከሚያ እንዲሆን ባሕርዳር ከተማ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው የመከላከያ ሆስፒታል የተመረጠ ሲሆን ከ40 በላይ የህክምና ባለሙያዎችና 35 ያህል ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ባለሙያዎች ለግዳጁ ተሰማርተዋል። ህክምናውን ሲሰጡ ከነበሩ የጤና ባለሙያዎች መካከል ከአንድ ወር በላይ በሆስፒታሉ ከቆዩት ከዶ/ር አዲሱ መለሰ ይገኙበታል። ትውልዳቸው በአማራ ክልል ማዕላዊ ጎንደር ደንቢያ ወረዳ የሆነው ዶ/ር አዲሱ፤ ጠቅላላ ሐኪም ሲሆኑ መደበኛ የሥራ ቦታቸው ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ነው። ባለትዳርና የ10 ወር ወንድ ልጅ አባትም ናቸው። የዕለቱ የጤና እና አካባቢ መሰናዶ ኢትዮጵያ ውስጥ በባሕር ዳር የመከላከያ ሆስፒታል የኮሮና ታማሚዎችን በሙያቸው ሲረዱ የነበሩ ሀኪምን ተሞክሮ ያጋራናል። የህክምና ባለሙያውን ያነጋገራቸው ዓለምነው መኮንን ጥንቅሩን ልኮልናል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ