1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሮም ማራቶንን በባዶ እግሩ የሮጠው ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 15 2015

የረዥም አመታት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ የነበረው ኤርሚያስ አየለ ባለፈው እሁድ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም በተካሄደው የማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ አጠናቋል። ይህንን ያደረገው ለዝነኛው አበበ ቢቂላ ክብር እና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ነው ይላል።

https://p.dw.com/p/4PA6n
ኤርሚያስ አየለ
የረዥም አመታት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ የነበረው ኤርሚያስ አየለ ባለፈው እሁድ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም በተካሄደው የማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ አጠናቋል። ምስል privat

የሮም ማራቶንን በባዶ እግሩ የሮጠው ኤርሚያስ አየለ

ዝነኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ላይ በባዶ እግሩ ከሮጠ እና ከአሸነፈ 63 ዓመታት ተቆጠሩ። የአትሌቶች አባት በመባል የሚታወቀው አትሌት አበበ ቢቂላ ያኔ ሮም ላይ በባዶ እግሩ የሮጠው በወቅቱ ለሩጫ የሚስማማው ጫማ ባለማግኘቱ ነበር። ባለፈው እሁድ የሮም ማራቶንን በባዶ እግሩ የሮጠው ኤርሚያስ አየለ ደግሞ ጫማ አጥቶ ሳይሆን ለዚህ ዝነኛ ሰው ያለውን «ክብር ለመግለፅ ነው» ይላል። ይህ ድርጊቱም በዘንድሮው ሩጫ የአበበ ቢቂላ ስም ተደጋግሞ እንዲነሳ ያደረገ ይመስላል። ኤርሚያስ የሩጫውን ድባብ በጣም ወዶት ነበር። « ግራንዴ ግራንዴ ይሉ ነበር። አንዳንዶች ከየት ሀገር ነህ ሲሉኝ ሌሎች አበበ ቢቂላ ይሉ ነበር። የሚያበረታታ ነበር። ሁሉም ሰው በጫማ ስለሆነ የኔ ብቻ መሆኑ ትኩረት ስቦ ነበር። ከእኔ ጋር ሰልፊ የሚነሱም ነበሩ። »  ይላል ኤርሚያስ። ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን በማግቱም እቅዱን እንዳሳካ ያምናል።
የረዥም አመታት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ሆኖ የሰራው ኤርሚያስ አየለ ከሩጫው በፊት ለሩጫው ይፈጅብኛል ብሎ የገመተው ሰዓት አራት ሰዓት ገደማ ነበር። ይሁንና ሩጫው ከጠበቀው ጊዜ በላይ ወስዶበታል። « ማራቶን ስሮጥ የመጀመሪዬ ነው።  በታላቁ ሩጫ ሁለት ጊዜ 10 ኪሎ ሜትር በባዶ እግሬ እሮጬያለሁ። ያለፉትን ሁለት ወራት ነው ስዘጋጅ የነበረው።  ከ 35 እና ከ 36 ኪሎ ሜትር በኋላ ልምዱ ስላልነበረኝ ፈትኖኛል።  አልፎ አልፎ  የውድድር መንገዱ ኮብል ስቶን ነው። በባዶ እግር ሲሮጥ ምቾት የለውም። በባዶ እግር ሲሮጥ እንደፈለጉት መርገጥ አይቻልም። እና በእነዚህ ምክንያቶች 4 ሰዓት ከ 26 ደቂቃ ፈጅቶብኛል። »
የእሁዱን ውድድር ሞሮኳዊው ቶፊቅ ዓላም 2 ሰአት ከ07 ደቂቃ በጫማ በመሮጥ አሸንፏል። አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ኤርሚያስ በባዶ እግሩ የመሄድ ልማድ የለውም። በባዶ እግሩ  መሮጥ የጀመረው « ራሴን ልፈትን» በሚል  ታላቁ ሩጫ ላይ ለመካፈል በወሰነ ጊዜ እንደሆነ ገልፆልናል።  ከዛም ይህንን ለምን ለጥሩ አላማ አላውለውም ብሎ ተነሳ። « 10 ኪሎ ሜትሩን መሮጥ ስችል፣ 200 ኪሎ ሜትሩን በሁለት ወር በባዶ እግሬ ለልምምድ መሮጥ ስችል የሀገር ገፅታን የመገንባት አላማ ስላለኝ ወጣቶችን ለማጀገን፣ ይጠቅማል በሚል » ማራቶን ለመሮጥ ወሰንኩ ይላል። 
የ45 ዓመቱ ጎልማሳ በባዶ እግሩ መሮጥ ከጀመረ አንድ አመት ቢያልፈውም በሮም ማራቶን ላይ ለመወዳደር የወሰነው ግን  በዚህ አመት ታህሳስ ወር ላይ ነው ይላል።  ከአዘጋጁም መሳተፍ እንደሚችል ምላሽ ሲያገኝ  በቀሩት ሁለት ወራት ጠንክሮ መለማመዱን ይናገራል።  እሱም  በሳምንት «ከ 55 እስከ 60 ኪሎ ሜትር እሮጥ ነበር» ይላል። ለ 11 ዓመታት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ያገለገለው ኤርሚያስ ባለፉት ሁለት አመታት በጋራ ለመሰረተው ድርጅት እየሰራ ይገኛል። ድርጅቱ «ድንቅ ኢትዮጵያን ብራንድ ኮንሰልታንት» የሚባል ሲሆን «አላማው የሀገርን ገፅታ መገንባት ላይ ነው» ይላል።  ከሩጫ ጋር በተያያዘ ቀጣይ እቅዱ አበበ ቢቂላ የሮጣቸውን ማራቶኖች መሮጥ ነው። « ከሮም ቀጥሎ በ1956 አበበ ቢቂላ ጃፓን ቶኪዮ ላይ ሮጧል።  እና በሚቀጥለው አመት መጋቢት ወር ቶኪዮ ላይ ማራቶን ለመሮጥ አቅጄያለሁ።  ከዛም አበበ ቢቂላ ከሮም ሌላ በግሪክ አቴን ማራቶን ላይ በባዶ እግሩ ሮጧል።» ከዛም ፓሪስ ላይ። ስለሆነም እነዚህ ውድድሮች ላይ ኤርሚያስ በባዶ እግሩ ለመሮጥ እና አሁን ያስመዘገበውን ሰዓት ለማሻሻል እቅድ ይዟል።  ኤርሚያስ ካለው የረዥም አመታት የስራ ተሞክሮ ለወጣት ሯጮች የሚመክረው« ፅናት፣ በርትቶ መስራት እና ረዥም ወደፊት ማሰብን » ነው። 

ኤርሚያስ አየለ
ኤርሚያስ አየለ ከሮም ቀጥሎ በሚቀጥለው አመት መጋቢት ወር ቶኪዮ ላይ ባዶ እግሩን ማራቶን ለመሮጥ አቅዷልምስል privat
ኤርሚያስ አየለ
የረዥም አመታት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ የነበረው ኤርሚያስ አየለ ባለፈው እሁድ በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም በተካሄደው የማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ አጠናቋልምስል privat

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ