1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት፣ጉድለቱና ፈተናዉ

እሑድ፣ ኅዳር 18 2015

ስስምምነቱ እንቅፋት ይገጥመዋል የሚለዉ ጥርጣሬ በግልፅ እየተነገረ ነዉ።በተለይ በናይሮቢዉ ስምምነት «የዉጪ ኃይል» ተብሎ የተጠቀሰዉ የኤትራትራ ጦር በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቆ ለመዉጣት ስለመዘጋጀት አለመዘጋጀቱ የአዲስ አበባም ሆነ ያስመራ ባለስልጣናት በግልፅ አለማስታወቃቸዉ ጥርጣሬዉን ወደ ስጋት እየቀየረዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4K5fH
Äthiopien Tigray-Region | zerstörter Panzer
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

«የስምምነቱ ጅምር ገቢራዊነት ተስፋ ሰጪ ነዉ» ተወያዮች

 

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተፈራረሙትን የሰላም ዉል ቀስቀስ በቀስም ቢሆን ገቢር እያደረጉ ነዉ።የርዳታ የመድሐኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና እሕል ወደ ትግራይ መግባት ጀምሯል።የኢትዮጵያ ዓየር መንገድም ወደ ትግራይ በረራ እንደሚጀምር አስታዉቋል።ለትግራይ ታጣቂዎች ስለሰላም ስምምነቱ ይዘትና አስፈላጊነት ገለፃና ማብራሪያ መሰጠቱን፣ተዋጊዎቹ ከየጦር ግንባሩ እንዲያፈገፍጉ መደረጉንም አዛዦቹ አስታዉቀዋል።የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎች ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ገቢር እንደሚያደርጉም በየፊናቸዉ ቃል እየገቡ ነዉ።

 

ይሁንና ስስምምነቱ እንቅፋት ይገጥመዋል የሚለዉ ጥርጣሬ በግልፅ እየተነገረ ነዉ።በተለይ በናይሮቢዉ ስምምነት «የዉጪ ኃይል» ተብሎ የተጠቀሰዉ የኤትራትራ ጦር በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቆ ለመዉጣት ስለመዘጋጀት አለመዘጋጀቱ የአዲስ አበባም ሆነ ያስመራ ባለስልጣናት በግልፅ አለማስታወቃቸዉ ጥርጣሬዉን ወደ ስጋት እየቀየረዉ ነዉ።

 

የህወሓት ባለስልጣናት ባለፈዉ ሳማንት በሰጡት መግለጫ የኤርትራ ጦር በሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግፍ ያደርሳል በማለት ወቅሰዋልም።በስምምነቱ መሰረት የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱት የዉጪ ኃይልና ከፌደራሉ መከላከያ ሰራዊት ዉጪ ትግራይ ዉስጥ የሰፈሩ ታጣቂዎች ክልሉን ለቅቀዉ ሲወጡ ነዉ።

Symbolbild | Gewalt gegen Frauen
ምስል Karl-Josef Hildenbrand/dpa/picture alliance

የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ በተደጋጋሚ እያሳሰቡ፣ አስመሮች ስምምነቱን ከጣሱ ዋሽግተኖች በኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉ እየዛቱም ነዉ።

 

በጦርነቱ ወቅቱ ብዙ የተነገረ፣የተዘገበ፣ ብዙዎችን ያሳዘነዉ ግን በቅጡ ያልተጠናዉ የጦር ወንጀልና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ጉዳይ በድርድሩ ሒደትና በስምምነቱ ሰነድ ብዙም አለመጠቀሱም እያነጋገረ ነዉ።ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት 30 ዓመታት በተደረጉ ጦርነቶች፣ግጭቶች፣ ዉዝግቦችና የአስተዳደር ጭቆናዎች በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸዉ፣ አካላቸዉ መጉደሉ፣ መሰቃየታቸዉ፣ የሴቶች መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ ግፎች መፈፀማቸዉን እንሰማለን።

 

ይሁንና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ በየአካባቢዉ በነበሩ የጎሳ ግጭቶች፣ኢሕአዴግ መራሹ አስተዳደር ያደረሳቸዉ ግፎች፣አስተዳደሩን በመቃወም በተደረጉ ሰልፎች የተገደሉ፣የቆሰሉና የተሰቃዩ ሰዎች ካፍታ ዜናነት አልፎ ፍትሕ ሲያገኙ በግልፅ አላየንም። ባለፈዉ ሁለት ዓመት በተደረገዉ ዉጊያ የደረሰዉ የሰብአዊ መብት ጥሰትስ እንደከዚሕ ቀደሙ እንደዋዛ ይታለፍ ይሆን?  የዉይይታችን ትኩረት ነዉ።ሶስት እንግዶች አሉን።

ነጋሽ መሐመድ