1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ትሩፋት ኤኮኖሚያዊ እሴቱ ስንት ይሆን?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5 2015

በፕሪቶሪያ በተፈረመ ሥምምነት ጋብ ያለው የኢትዮጵያ ጦርነት ካስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር ፈጣን ዕድገት አስመዘገበ የሚባለውን ኤኮኖሚ ክፉኛ ጎድቶታል። ኤኮኖሚው ከጦርነት በፊት የነበረውን እድገት እና ለመጪዎቹ ዓመታት የተተነበየለትን ያነጻጸሩ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ኪሳራው ከፍተኛ እንደሆነ ያምናሉ።

https://p.dw.com/p/4KwMo
Tigray I zerstörter Panzer
ምስል Tiksa Negeri/File Photo/REUTERS

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የሰላም ትሩፋት ኤኮኖሚያዊ እሴቱ ስንት ይሆን?

ኢትዮጵያ እና ጦርነት የደቆሳቸው የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ከተፈረመ ሁለት ወራት ያስቆጠረውን በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት ፍሬ በጉጉት እየጠበቁ ነው። በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተፈረመው ሥምምነት አተገባበር ዘገምተኛ ቢሆንም የዕርዳታ አቅርቦትን ጨምሮ መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል። ወጋገን ባንክ እና አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በትግራይ ክልል ተቋርጦ የቆየ ሥራቸውን "በቅርቡ" ለመጀመር ቅድመ-ዝግጅት እንዳጠናቀቁ አስታውቀዋል። አገሪቱ ሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት የወደመውን መልሶ ለመገንባት 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ያስፈልጋታል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ታገኝ የነበረው እና በጦርነቱ የቀነሰው ብድር እና ዕርዳታ የፕሪቶሪያው ሥምምነት ከተፈረመ በኋላ "መሻሻል" ያሳይ ይሆናል ብለው ተስፋ እንዳደረጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ባለፈው ሣምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገልጸዋል።

በአሜሪካ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና ከፕሬዝደንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ታኅሳስ 4 ቀን 2015 ሲገናኙ የሥምምነቱ አተገባበር ዋንኛ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ነበር።

ብሊንከን ሥምምነቱ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆን እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪዎች ግጭት ወደ ነበረባቸው አካባቢዎች መጓዝ እንዲፈቀድላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ የመውጣት አስፈላጊነት ዐቢይ እና ብሊንከን ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።

ከተፈረመ ሁለት ወራት ያስቆጠረው ሥምምነት ጦርነቱን ጋብ አድርጎ ተስፋ ቢያጭርም በፕሪቶሪያ የተደረገውን ድርድር የታዘቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሐና ቴቴህ ግን የመጨረሻው ሰነድ እንደማይሆን እምነታቸው ነው።

መቀመጫውን በደብሊን አየርላንድ ያደረገው የዓለም አቀፍ እና አውሮፓ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ባቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ስለ ሰላም ሥምምነቱ ማብራሪያ የሰጡት ልዩ መልዕክተኛዋ "ግጭት በቋሚነት ለማቆም የተፈረመው ሥምምነት ከሰላም ሥምምነት ለመድረስ እጅግ ጠቃሚ የመጀመሪያ እርምጃ ቢሆንም ሰነዱ የትጥቅ አፈታት፣ የታጣቂዎች አበታተን እና መልሶ ማዋሀድን ለመሳሰሉ ጉዳዮች ሌሎች ገጽታዎች እንዲሁም በሁለቱ ወገኖች መካከል ላሉ ዋንኛ የፖለቲካ እና የአስተዳደር ልዩነቶች መፍትሔ ለማበጀት ሌሎች ውይይቶች እና ድርድሮች እንዲደረጉ ያቅዳል" ሲሉ ተናግረዋል። በፕሪቶሪያ የተፈረመው ሥምምነት "የመጨረሻ ሰነድ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም" ያሉት ሐና ቴቴህ "መሠረታዊ ሰነድ ነው፤ ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች የሚደራደሩበት ብቸኛው ሥምምነት አይደለም ብዬ አስባለሁ" ሲሉ አስረድተዋል።

የፕሪቶሪያው በቋሚነት ግጭት የማቆም ሥምምነት አተገባበርም ይሁን እንደ ሐና ቴቴህ ያሉ ዲፕሎማቶች ይደረጋሉ የሚሏቸው ተጨማሪ ውይይቶች እና ድርድሮች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ላይ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሐብቱ ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረቦች የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴፋን ዴርኮን እና ዶክተር ክርስቲያን ሜየር የፕሪቶሪያው ሥምምነት ለኢትዮጵያ ሰላም እና መልሶ ማገገም እጅግ ጠቃሚ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ እምነታቸው ነው።

የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና በዕዳ ክፍያ ቀውስ ከገባበት ጫና አላቆ ማክሮ ኤኮኖሚውን ማረጋጋት ዶክተር ክርስቲያን እንደሚሉት የአጭር ጊዜ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ከዚህ ቀደም ወደነበረው ፈጣን ኤኮኖሚያዊ ዕድገት መመልስ ካልቻለ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 125 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሊያጣ እንደሚችል ፕሮፌሰር ስቴፋን ዴርኮን እና ዶክተር ክርስቲያን ሜየር ይሞግታሉ።

ይኸ የሚሰላው ግን ሰላም ሰፍኖ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ሊኖረው ከሚችል የዕድገት እምቅ አቅም አኳያ ነው። በሁለቱ ልሒቃን ስሌት መሠረት ምጣኔ ሐብቱ በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ሰፍኖ እንደከዚህ ቀደሙ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ካልቻለ በጎርጎሮሳዊው 2027 ሊደርስበት ከሚችለው አኳያ 19 በመቶ ያነሰ ይሆናል።  ዶክተር ክርስቲያን እንደሚሉት ስሌቱ የተሰራው ግጭት ባልነበረባቸው ዓመታት የነበረውን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለመጪዎቹ ዓመታት ለኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ከሰራው ትንበያ በማነጻጸር ነው።

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈራረሙ በኋላ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሐና ቴቴህ በፕሪቶሪያ የተፈረመው ሥምምነት "የመጨረሻ ሰነድ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም" ያሉት ሐና ቴቴህ "መሠረታዊ ሰነድ ነው፤ ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች የሚደራደሩበት ብቸኛው ሥምምነት አይደለም ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

በጎርጎሮሳዊው በ2018/2019 ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት በአማካኝ በዓመት 4.4 በመቶ ዕድገት እንደነበራቸው ዶክተር ክርስቲያን አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በአንጻሩ በ8.4 በመቶ አድጓል። ይኸ 4 በመቶ ገደማ ልዩነት አለው። ከ2005 እስከ 2010 ወይም ከ2005 እስከ 2015 በነበሩት ዓመታት ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ አገራት አኳያ "ኢትዮጵያ እጅግ በፈጠነ ሁኔታ አድጋለች።" ይኸ የዕድገት መጠን ግን ከደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተስተጓጉሏል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በ2023 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ5.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርጓል። ዶክተር ክርስቲያን እንደሚሉት ይኸ የዕድገት መቀነስ አንድም "በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጽዕኖ" የተከሰተ ነው።  ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ የተዘዋዋሪ ተጽዕኖ አገሪቱ ከዓለም አቀፍ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ገንዘብ ማግኘት አለመቻሏ፤ የማክሮ ኤኮኖሚው አለመረጋጋት፣ የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ እጦት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አለመኖርን ለዕድገቱ መቀነስ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ጉዳዮች ናቸው። "ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለመጪዎቹ ዓመታት በሰጠው የዕድገት ትንበያ እና ግጭት ባልነበረባቸው ዓመታት የነበረው ፈጣን ዕድገት መካከል ያለው ልዩነት የሰላም ትሩፋት ነው። ኤኮኖሚው ሊያጣ የሚችለውም ያንን ልዩነት ነው" ሲሉ ዶክተር ክርስቲያን ሜየር ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ደብረ ማርቆስ ገበያ
የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና በዕዳ ክፍያ ቀውስ ከገባበት ጫና አላቆ ማክሮ ኤኮኖሚውን ማረጋጋት ዶክተር ክርስቲያን እንደሚሉት የአጭር ጊዜ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።ምስል DW/E. Bekele

ይኸ ስሌት ጦርነቱ በደረሰባቸው የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች በመሠረተ-ልማቶች ላይ የደረሰ ውድመት ያስከተለውን ኪሳራ የሚያካትት አይደለም። ይኸን ኪሳራ ማስላት በአሁኑ ወቅት ለምጣኔ ሐብት ባለሙያዎቹ ፈታኝ ሆኖባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የኪሳራውን መጠን የሚያሳይ "ተዓማኒ ግምት እጦት" አንዱ ምክንያት ነው። 

ሁለቱ የምጣኔ ሐብት ልሒቃን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለአጠቃላይ የቀጠናውን መጻኢ እጣ ፈንታ አቅጣጫ ሊያበጅ ይችላል በሚሉት ሒደት ጣልቃ ሳይገቡ በኤኮኖሚያዊ እገዛ ሥምምነቱን ሊደግፉ እንደሚገባ ይሞግታሉ። "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ በማቅረብ ኤኮኖሚያዊውን ፋይዳ እና የሰላም ትሩፋቱን እጅግ ግልጽ ማድረግ ይችላል" የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው "የኢትዮጵያ መንግሥት በወገኑ የፕሪቶሪያውን ሥምምነት ግልጽ እና ቁርጠኛ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ አለበት" ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዋሽንግተን ከአሜሪካ ሹማምንት ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች በፕሪቶሪያው ድርድር የተሳተፉት የፍትኅ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪው ሬድዋን ሑሴን እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማሞ ምኅረቱ ተገኝተዋል። የዋሽንግተኑ ጉባኤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ጥረት የሚያደርግበት እንደሚሆን ይጠበቃል። 

እሸቴ በቀለ