የሰኔ 3 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሰኔ 3 2016የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ባለፈው ሳምንት ባደረጋቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለት ግጥሚያዎች የጅቡቲንም ማሸነፍ አለመቻሉ አነጋግሯል ። የአውሮጳ እግር ኳስ የፊታችን ዓርብ ይጀምራል ። አዘጋጇ ጀርመን ውስጥ የእግር ኳስ ደጋፊው ድባብ ምን ይመስላል? እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ጀርመን የአዓለም እግር ኳስ ጨዋታን ስታዘጋጅ የነበረው ደማቅ ድባብስ ይመለስ ይሆን? ዳሰሳ ይኖረናል ። በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመናዊው አሌክሳንደር ዝቬሬቭ በ21 ዓመቱ ስፔናዊ ካርሎስ አልካራዝ ሽንፈት ገጥሞታል ። አሌክሳንደር ዝቬሬቭ በፍጻሜው ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የቀድሞ የሴት ጓደኛው ላይ አካላዊ በደል ፈጽሟል በሚልም በፍርድ ቤትም ሙግት ይጠብቀዋል ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ 4ኛ የምድብ ጨዋታውን ትናንት ከጎረቤት ጅቡቲ ጋ አድርጎ አንድ እኩል ተለያይቷል ። ሞሮኮ ውስጥ በኤል አብዲ ስታዲየም በተከናወነው ግጥሚያ በጋብርኤል ዳድዚ 28ኛው ደቂቃ ላይ ቅድሚያ ግብ ያስቆጠረችው ንዑሷ ጅቡቲ ነበረች ። ለኢትዮጵያ አቻ የምታደርገውን ግብ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ምንይሉ ወንድሙ ነው ። የኢትዮጵያ ቡድን ባለፈው ሳምንት ከጊኒ ቢሳው ጋ በቢሳው ሴፕቴምበር 24 ስታዲየም ተጋጥሞ ያለምንም ግብ መለያየቱ ይታወሳል ። ለመሆኑ በሁለቱ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አቋም ምን ይመስላል? በይበልጥ መሻሻል የሚገባውስ በየትኛው መስመር ላይ ነው? የስፖርት ዘጋቢ ዖምና ታደለ ሁለቱንም ጨዋታዎች ተከታትሏል ። በጅቡቲ ግጥሚያ ያጣነው እጅግ የሚያስቆች ነው ብሏል ።
እስካሁን በነበሩ አራት ግጥሚያዎች፦ ኢትዮጵያ በ3 ጅቡቲ በ1 ነጥብ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ከምድቡ ስድስት ተጋጣሚዎች ሌሎቹ ሦስት ሦስት ግጥሚያዎችን አከናውነዋል ። በዚህም መሠረት፦ ግብጽ በዘጠኝ ነጥብ ምድቡን ትመራለች ። ጊኒ ቢሳው በአምስት ነጥብ ትከተላለች ። ቡርኪና ፋሶ እና ሴራሊዮን አራት አራት ነጥብ ሲኖራቸው በግብ ክፍያ ልዩነት የሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል ።
የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያዎች
በአውሮጳ እግር ኳስ የመክፈቻ ጨዋታ አዘጋጇ ጀርመን የፊታችን ዐርብ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ምሽት አምስት ሰአት ላይ ከስኮትላንድ ጋ ትጋጠማለች ። በነጋታው ቅዳሜ ደግሞ ሐንጋሪ ከስዊትዘርላንድ፤ ስፔን ከክሮሺያ እንዲሁም ጣሊያን ከአልባኒያ ጋ ይጫወታሉ ። እሁድ ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች ሲኖሩ፦ ተጋጣሚዎቹም ፖላንድ ከኔዘርላንድ፤ ስሎቬኒያ ከዴንማርክ እንዲሁም ሠርቢያ ከእንግሊዝ ናቸው ። በዘንድሮው ውድድር ለዋንጫ የመድረስ እድል አላቸው ተብለው በዋናነት ከሚጠበቁት ቡድኖች መካከል ቀዳሚዋ ፈረንሣይ ናት ። በፊፋ መስፈርት አርጀንቲናን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ቤልጂየም ሦስተኛ፤ እንግሊዝ አራተኛ እንዲሁም ፖርቹጋል ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ናቸው። ጀርመን በፊፋ መስፈርት ደረጃዋ 16ኛ ነው ። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግና የአውሮጳ ሊግ ፍልሚያዎች
በጀርመን ድባቡ ምን ይመስላል?
ጀርመን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 የዓለም ዋንጫን ባዘጋጀችበት ወቅት የነበረው አይነት ድባብ በአውሮጳ እግር ኳስ ውድድሩ እንደማይጠበቅ ነው ብዙዎች ግምታቸውን ያሰፈሩት ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥፋት እና ጸጸት በኋላ በጀርመን ብሔራዊ የሀገር ስሜት ያለመሸማቀቅ እና ፍርሐት አደባባይ የታየበት፤ የጀርመን ሰንደቅ ዓላማ በየቦታው የተውለበለበበት ወቅት ነበር ። አሁን ያ ዘንድሮ የሚታይ አይመስልም ።
ከ18 ዓመታት በፊት ጀርመን ለዋንጫ ደርሳ በጣሊያን በተሸነፈችበት ወቅት የነበረው ድባብ እጅግ ልዩ ነበር ። በተለይ በግማሽ ፍጻሜ ወቅት ብቻ በታዋቂው የበርሊኑ ብራንደርቡርግ መግቢያ አደባባይ 900,000 ስፖርት አፍቃሪዎች ተሰብስበው ጨዋታውን መከታተላቸው በታሪክ ሰፍሯል ። በየመዝናኛ ቦታዎች እና አደባባዮችም ኳስ ተመልካቹ እለት በእለት ነበር የሚጎርፈው ።
በፍራንትስ ቤከን ባወር የሚመራው ቡድን በቀጣዩ የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ በምክትሉ ዮአሒም ሎይቭ አሰልጣኝነት የሦስተኛ ደረጃን ይዞ ብርታቱን ያሳየበት ወቅት ነበር ። ብራዚል ባዘጋጀችው የ2014 የዓለም ዋንጫ ደግሞ ዋንጫውን በመውሰድ መላ ጀርመንን አስፈንጥዘዋል ። የእነ ፊሊፕ ላም፤ ፔር ሜርቴሳከር፤ ሚሮስላቭ ክሎዘ፤ ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር እና ሉቃስ ፖዶልስኪ ብቃት የታየበት፤ ለጀርመን ልዩ የእግር ኳስ ዘመን ። በቀጣዮቹ የ2018 እና 2022 የዓለም ዋንጫ ግን የጀርመን ቡድን ከምድብ ማጣሪያው እንኳን ማለፍ አቅቶት ወዲያው ነበር የተሰናበተው ። የዚያ ሰሞን ስነ ልቦና አሁንም ድረስ ቡድኑን ተከትሎ እያስጨነቀው ይመስላል ። ባለፈው ዐርብ ቡድኑ ከግሪክ ጋ ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 2 ለ1 ቢያሸንፍም አቋሙ ግን ደጋፊዎቹን አላስደሰተም ። ሜዳ ላይ እንደውም ተቃውሟቸውን በጩኸት የሚያሰሙ ነበር ። የግንቦት 26 ቀን 2016 ዓም የስፖርት ጥንቅር
ለፀጥታው ጥበቃ 22,000 የሚጠጉ ፖሊሶች ተሰናድተዋል
ለ51ዱ የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ በጀርመን ዐሥር ስታዲየሞች ተዘጋጅተዋል ። የቤርሊኑ ከ71 ሺህ በላይ ተመልካች በመያዝ ተፎካካሪ የለውም ። ሙይንሽን እና ዶርትሙንድ እያንዳንዳቸው 62 ሺህ ተመልካቾችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች አላቸው ። ሽቱትጋርት፤ ሐምቡርግ፤ ዶይስልዶርፍ፤ ፍራንክፉርት፤ ኮሎኝ፤ ላይፕትሲሽ እና ጌልዘንኪርሸ ውስጥ የሚገኙ ስታዲየሞች ላይም ጥበቃው ከወዲሁ መጠናከሩ ተገልጧል ። የጀርመን የፌዴራል የሀገር ውስጥ ሚንስትሯ ናንሲ ፋይዘር የፀጥታው ጉዳይ ከምንም በላይ ነው ብለዋል ።
«በጀርመን የአውሮጳ እግር ኳስ የፀጥታ ጥበቃ ለእኛ ከምንም በላይ ከፍተና ቦታ የምንሰጠው ነው ። በጨዋታዎቹ ወቅት የፌዴራሉ እና ክፍላተ ሃገራት ፀጥታውን ለመጠበቅ የትብብር ሥራቸው እስካሁን አመርቂ ነው ። ሊታሰቡ የሚችሉ አደጋዎች ላይ ትኩረት በመስጠት የፀጥታ አካላቶቻችን በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ ናቸው ።»
በጀርመን ለዚሁ የእግር ኳስ ግጥሚያ የፀጥታ ጥበቃ ፖሊሶች የረፍት ጊዜ እንዳይወስዱ ተደርገዋል ። በየቀኑም ወደ 22, 000 የሚጠጉ ፖሊሶች ጥበቃ ያደርጋሉ ተብሏል ።
በነገራችን ላይ አድማጮች፦ በአውሮጳ የእግር ኳስ ግጥሚያ ላይ ለረዥም ዘመን ከተጫወቱ ታዋቂ ተጨዋቾችአንዳንዶቹን ዘንድሮም ድጋሚ የምናያቸው ይሆናል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ የእግር ኳስ ግጥሚያ በተጨዋችነት ለበርካታ ዓመታት በመሳተፍ የፖርቹጋሉ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ የደረሰ የለም ። ዘንድሮ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ39 ዓመቱ በአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር ለስድስተኛ ጊዜ ይሰለፋል ማለት ነው ።
የሜዳ ቴኒስ
በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ስፔናዊው ካርሎስ አልካራዝ ጀርመናዊው አሌክሳንደር ዝቬሬቭን አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል ። የ21 ዓመቱ ካርሎስ ለድል የበቃው ለአራት ዙር በዘለቀው ፉክክር ሦስቱን በማሸነፍ ነው ። ከዓለማችን የሜዳ ቴኒስ ድንቅ ተጨዋቾች በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አሌክዛንደር ዝቬሬቭ በፓሪስ የፈረንሳይ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ላይ ሲደርስ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜው ነው ። በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ በርካታ ዋንጫዎችን በመውሰድ የሚታወቀው ራፋኤል ናዳል ስኬት በደበዘዘበት፤ ኖቫክ ጄኮቪች በጉዳት በተሰናበተበት ግጥሚያ ዘንድሮ ለአሌክሳንደር ዝቬሬቭ በስፍራው የመጀመሪያ ዋንጫውን ይወስዳል ተብሎ ተገምቶም ነበር ። በዋንጫ ግጥሚያው ያልተሳካለት አሌክሳንደር የቀድሞ የሴት ጓደኛውን በድሏል በሚል በፍርድ ቤት ክስ ይጠብቀዋል ። የ27 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ ድንቅ ተጨዋች በእርግጥ ክሱን ከዚህ ቀደም ተቀባይነት የሌለው ሲል አጣጥሏል ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን ግን አለመቀበል አይችልም ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ