1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥሪ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10 2014

የፌዴራል መንሥስት እና ትግራይን እየመራ የሚገኘው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ለድርድር ያሳዩትን ተነሳሽነት እንደሚያደንቅ የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጠ። ምክር ቤቱ ሁለቱም ወገኖች በድርድር ሂደቱ ላይ በቅን ልቦና እንዲሳተፉ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4Fb0M
Äthiopien Addis Abeba Nationaler Dialog
ምስል Solomon Muchie/DW

ሁለቱ አካላት ለድርድር ያሳዩትን ተነሳሽነት እንደሚያደንቅ ገልጧል

የፌዴራል መንሥስት እና ትግራይን እየመራ የሚገኘው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለድርድር ያሳዩትን ተነሳሽነት እንደሚያደንቅ የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጠ። ምክር ቤቱ ሁለቱም ወገኖች በድርድር ሂደቱ ላይ በቅን ልቦና እንዲሳተፉ ጠይቋል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለሂደቱ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል። ውሳኔው በተደራዳሪ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ባሉ በሁሉም የሀገር ውስጥ እና የውጪ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ምክር ቤቱ ዐሳውቋል። 

በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን እና ዘርፉን የመወከል እና የማስተባበር ሕጋዊ ሥልጣን የተሰጠውና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሁለቱም ወገኖች ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጧል። 

ምክር ቤቱ አሁን የተጀመረውን ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለውን ጦርነት በሰላም የመፍታት ተነሳሽነት ሙሉ በሙሉ መደገፉን አሳውቆ ሂደቱና ጥረቱ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን ያሳተፈ ሊሆን እንደሚገባ በጥብቅ ያምናል ሲሉ የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በተለይም ለዶቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አሁን ያደረገው በሰላም ድርድሩ ውስጥ ተሳታፊ የመሆን ጥሪ ሂደቱ ቅቡልነት እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ ውጤቱ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንዲችል የሚኖረውን አስተዋጾ ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር የቀረበ ነው ብሏል። ይሁንና የሲቪክ ማሕበራት ድርጅቶች በድርድር ሂደቱ ሚና ኢንዲኖራቸው ሲጠየቅ ምን ተግባር እንዲፈጽሙ ከመፈለግ መነሻ ነው የሚለውን አቶ ሄኖክ ተጠይቀዋል። 

Infografik Karte Äthiopien AM

የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት "የትጥቅ ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ለሚደረገው የሰላም ማስፈን ሥራ ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥ ለዶቼ ቬለ በላከው መግለጫ ጠቅሷል።  የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ከዚህ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ከDW ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በተደራዳሪዎች በኩል ሰፊ የሆነ ቅል ልቦናና ታጋሽነት ይጠይቃል" ብለው ነበር የሲቪክ ማሕበራት ሚናም ቀላል እንደማይሆን በመግለጽ ጭምር።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በሰላም ድርድሩ የሚገኘው ውጤት ገለልተኝነትን መነሻ ያደረገ እንዲሆን እንጠብቃለን ብለዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በኢፌዲሪ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተመዝግበው ዕውቅና ያገኙትን የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን በሙሉ በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ በአዋጁ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በአሁኑ ወቅትም ከ3700 በላይ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባላት መሆናቸው ታውቋል።

በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሰላም ጥረት በሕብረቱ ብቸኛ ጥረት እንዲቀጥል የመንግሥት ፍላጎት መሆኑንና ሌላ ጎን ለጎን የሚሄድ ጥረት ተቀባይነት እንደማይኖረው መንግሥት አሳውቋል። ሕወሓት ደግሞ ከሕብረቱ ይልቅ የኬንያ መንግሥት ድርድሩን እንዲመራው ፍላጎቱን አሳይቷል። ሁለቱ ኃይሎች ለድርድር መዘጋጀታቸውን የገለፁ ቢሆንም ድርድሩ የትና በማን አመቻችነት እንደሚከናወን ግለፅ ሆኖ የተገለጸ ነገር የለም። መንግሥት በትግራይ ክልል የመሠረታዊ አገልግሎቶችን መጀመር ለድርድር በቅድመ ሁኔታነት እንደማያስቀምጥ ከሰሞኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናግሯል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ