«የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የሞት ቅጣት እርምጃ ከገባው ቃል ጋር ይጣረሳል»
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 2016ሳዑዲ አረቢያ ባለፉት ስድስት ወራት ሁለት ሴቶችን ጨምሮ 100 ሰዎችን በሞት ከቀጣች በኋላ በሀገሪቱ የሞት ቅጣት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን በአውሮጳ የሳዑዲ አረቢያ የሰብአዊ መብቶች ተመልካች ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ሃገሪቱ በያዝነው የጎርጎርሳውያኑ ዓመት የተፈጸመው የሞት ቅጣት ካለፈው የ2023 ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ42 ከመቶ ብልጫ አሳይቷል።
ሳኡዲ አረቢያ ባለፉት ስድስት ወራት በግድያ ፣ ዕጽ በማዘዋወር እና በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ጥፋተኛ ናቸው ያለቻቸውን 100 ሰዎች በአደባባይ በሞት ቀጥታለች ። ዕርምጃው ሀገሪቱ በ2030 ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማሳካት የሞት ቅጣት መጠንን ለመቀነስ ከወጠነችው ራዕይ ጋር ይጋጫል ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ነው። በሳኡዲ አረቢያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ብርቱ ትችት እና ወቀሳ ካሰሙት መካከል መቀመጫውን በርሊን ያደረገው የአውሮጳውያኑ የሳዑዲ አቢያ የሰብአዊ መብት ተመልካቹ ቡድን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ (ESOHR አንዱ ነው። በድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት ጆይ ሺአ እንደሚሉት ከሰሞኑ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በገፍ የሞት ቅጣት ከጥቂት አመታት በፊት የገባውን የሞት ቅጣት የመቀነስ ቃል ያጠፈ ነው ።
«እንደሚታወቀው ከጥቂት አመታት በፊት የሳውዲ መንግስት የሞት ቅጣትን በተለይ ደግሞ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች እና በህጻናት ላይ የሚደርሰውን የሞት ቅጣት እንደሚቀንስ ቃል ገብቶ ነበር። እንደ አለመታደል ሆኖ የዚህ አዝማሚያ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የተገላቢጦሽ እና የሞት ቅጣትን ለመገደብ የገባውን ቃል እና የሰጠውን ተስፋ በግልፅ ሲጥስ አይተናል።»
የመብት ተቆርቋሪዎቹ እንደሚሉት በአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ላይ የሚሰነዘሩ የትኞቹም አይነት ትችትም ይሁን የመብት ጥያቄዎች በሽብርተኝነት ያስከስሳሉ። ይህንኑ በተመለከተ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት የመብት ጉዳዮች አጥኚዋ ጆይ ሺአ «የቢን ሳልማን መንግስት በዚህ የሰብአዊ መብት አያያዙ ዓለማቀፍ ተጠያቂነት ስላላመጣባቸው ርህራሄ የጎደለው የሞት ቅጣት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗቸዋል» ይላሉ ።
የጀርመን መንግስት ለሳዑዲ አረቢያ ጦር መሳሪያ እንዲሸጥ መወሰኑ
« በልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን የሚመራው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለደረሰው ግፍና በደል ተጠያቂ አለመሆኑ እና ይህም በሰዎች ላይ የሚፈጸመው ያለ ገደብ እንዲቀጥል አስችሎታል የሚል አቋም አለን ።»
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋጅ ድርጅት የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሆና ትሰራ የነበረችው እና በቅርቡ ከእስር የተለቀቀችው የሉጃይ አል ሃትሉን እህት ሊና አል ሃቱል በበኩሏ በሳኡዲ አረቢያ የሰሞንኛ የሞት ቅጣት እርምጃ ለዶቼ ቬለ በሰጠችው አስተያየት የሀገሪቱ መንግስት ሰዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ ለመገደብ ያለመ ነው ።
«እኔ እንደማስበው የመናገር ነፃነት ካለ ሰዎች በስርዓቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን መግለጽ ይጀምራሉ። እናም ህብረተሰቡ ንቁ እንዲሆን የሚያስፈልገው ይህ ነው። ታውቃለህ፣ ዝም ብለህ ሰዎችን አፍነህ እና ረግጠህ ፤ አሰቃይተህ አስረህ ፤ መግደል አትችልም »
ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ሀገራቸው በነዳጅ ዘይት ላይ ያላትን ጥገኝነት ወደ ሌሎች አማራጮች የመመልከት ዕቅዳቸውን ለመተግበር የውጭ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እና በተለይ በአረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ላይ መዋዕለነዋይ ማፍሰስ ቀዳሚ አጀንዳቸው ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሀገሪቱ ሰፊ የቱሪዝም አማራጮችን ለመመልከት ከፊታችን የጎርጎርሳውያኑ 2017 ጀምሮ እስከ 2034 የኦሎምፒክ ጫወታዎችን ጀምሮ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን የማስተናገድ ራዕይ አንግበው መነሳታቸው ነው የሚነገረው ። ከሴቶች መብት አያize አንጻርም በርካታ መሻሻሎችም ታይተዋል። መኪና የማሽከርከር በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው መስራት እና ለብቻቸው መጓዝን ጨምሮ የታዩ መሰረታዊ ለውጥ ያስከተሉ እርምጃዎችም ተወስደዋል ። ነገር ግን አሁንም ድረስ ብዙዎችን እያሳሳበ ያለው እና በጅምላ በሚመስል መልኩ የሚወሰደው የሞት ቅጣት ተባብሶ መቀጠሉ ታይቷል።
ሳዑዲ አረቢያ ውሰጥ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ
ሊና አል ሃትሉን እንደምትለው ለሳዑዲ አረቢያ መንግስት እርምጃ ዝምታ ችግሩን ከማባባስ እንደማይመለስው ነው የምትሰጋው
«አሁን፣ ዓይናችንን ከጨፈንን እነሱ በድርጊታቸው ይቀጥላሉ፣ ታውቃላችሁ፣ እነሱ እጥፍ ይሆናሉ። እነርሱ መንግስትን ሲተች ወይም ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል የተባለን ማንኛውንም ሰው ጋር መጨረስ ይፈልጋሉ።»
ሳዑዲ አረቢያ ባለፈው የጎርጎርሳዊኑ 2023 172 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች ። ይህ በ2022 ከተፈጸመው የ196 ሰዎች የሞት ቅጣት ጋር ሲነጻጸር አንጻራዊ መሻሻል ነበረው ። ነገር ግን በዚህ ዓመት በስድስት ወር ውስጥ ብቻ የተፈጸመው የ100 ሰዎች የሞት ቅጣት ሀገሪቱ አሁንም እርምጃውን አጠናክራ መቀጠሏን ያሳይል ሲሉ የመብት ተሟጋቾቹ አቤቱታቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ነው። ዶቼ ቬለ ብርቱ ትችት እያስተናገደ በሚገኘው የመብት ጉዳይ ላይ የሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምላሽ እንዲሰጥበት ቢጠይቅም ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ መልስ ማግኘት አልቻለም ።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ