1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኛ ተፈናቃይ ቁጥር ማየል

ሐሙስ፣ ሰኔ 9 2014

ኮሚሽነር ግራንዲ እንደሚሉት በ2021 ከተፈናቀለዉ ወይም ከተሰደደዉ ከ89 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ 83 ከመቶ ለሚሆነዉ ከለላ ወይም መጠጊያ የሰጡት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ ሐገራት ናቸዉ። አዉሮጳ ለዩክሬን ስደተኞችና ጉዳቶች የሚሰጠዉን ድጋፍና ያሰየዉን ደግነት ኮሚሽነሩ አድንቀዉ፣የሌሎቹን ሐገራት ችግረኞች መግፋቱን ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/4CpGn
Symbolbild I Flucht und Migration
ምስል Alfredo Zuniga/AFP

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) በበኩሉ እንደገለጸው የምግብ እጥረት፣የመብት ረገጣ፣ የመኖር ዋስትና እጦት፣ ግጭትና አለመረጋጋት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የደሐ ሐገራት ሕዝብን እያሰደደና እያፈናቀለ ነዉ።የኮሚሽነሩ የበላይ ፊሊፖ ግራንዲ ዛሬ እንዳሉት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2021 በየሐገሩ የሚደርስ ጭቆና፣ግጭት፣ ግፍና ሁከት ከ89 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከቀየዉ አፈናቅሏል ወይም አሰድዷል።ዘንድሮ በነባሮቹ ፣ጭቆና፣ግጭት ግፍና ሁከት ላይ የተጨመረዉ ድርቅ፣ የዩክሬን ጦርነት፣የጦርነቱ መዘዝ ያስከተለዉ የምግብ እጥረትና ቀዉስ በተለይ የደሐ ሐገራትን ሕዝብ በብዛት እያሰደደ ወይም እያፈናቀለዉ ነዉ።ግራንዲ እንደሚሉት በግሪጎሪያኑ ዘንድሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሕዝብ ከተፈናቀለና ከተሰደደባቸዉ አካባቢዎች አንዱ የአፍሪቃ ቀንድ ነዉ።«አፍሪቃ ቀንድ ዉስጥ (የተፈናቃዩ ቁጥር ያየለዉ) በብዙ ምክንያቶች ነዉ።አሁን ያልተጠናቀቀዉ የትግራይና የአካባቢዉ ግዛቶች ጦርነት፣ ድርቅ፣ በተለይ በፖለቲካዊ የለዉጥ ሒደት ላይ ያለችዉ ሶማሊያ፣ በጣም መጥፎ እንደማይሆን ተስፋ ብናደርግም ኬንያ ዉስጥ የፖለቲካ ሽግግር ሊደረግ መሆኑ እዉነት ነዉ።ሱዳን ዉስጥ ግልፅ ያልሆነና መፍትሔ ያላገኘ ሁኔታ አለ።»
ኮሚሽነር ግራንዲ እንደሚሉት በ2021 ከተፈናቀለዉ ወይም ከተሰደደዉ ከ89 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ  83 ከመቶ ለሚሆነዉ ከለላ ወይም መጠጊያ የሰጡት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ ሐገራት ናቸዉ።ምዕራቡ ዓለም በተለይም አዉሮጳ ለዩክሬን ስደተኞችና ጉዳቶች የሚሰጠዉን ድጋፍና ያሰየዉን ደግነት ኮሚሽነሩ አድንቀዉ፣የሌሎቹን ሐገራት ችግረኞች መግፋቱን ተችተዋል።
                                           
«አዉሮጳ፣ የዛሬ 6 ዓመት ተኩል ይሕን ኃላፊነት ከያዝኩ ጊዜ ጀምሮ ብዙ መሪዎች ቦታ የለንም፣ሞልተናል ሲሉኝ ነበር።(ባንድ ወቅት) 40 ስደተኞች የያዘች ጀልባ ሲሲሊ-ኢጣሊያ ደረሰች።የየሐገሩ መሪዎች ምንያሕል ሰዉ እንደሚቀበሉ፣ለስንት ጊዜ እንደሚቀበሉ በስልክ ሲወዛገቡ ነበር።አሁን በ6 ሳምንት ግድም  6 እና 7 ሚሊዮን  የዩክሬን ስደተኛ (አዉሮጳ) በቀላሉ ለመቀበል እንዴት ቻለ? አቀባበሉ ደግነት የተሞላበት፣ ዉጤታማም ነበር። ስለዚሕ ይቻላል ማለት ነዉ።»

Symbolbild I Flucht und Migration I Filippo Grandi
ምስል Fabrice Coffrini/AFP

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ