1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ፈርጀ ብዙ ቀዉስ

ሰኞ፣ ኅዳር 19 2015

በአብዛኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ያሰለጠነና ያስታጠቀዉ ዳናብ ሰሞኑንም 100 የአሸባብ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታዉቋል።ከአንድ መቶዉ ታጣቂዎች 60ዎቹ የተገደሉት ቡኩራ በተባለችዉ የደቡባዊ ሶማሊያ አነስተኛ ከተማና አካባቢ ነዉ

https://p.dw.com/p/4KCTq
Somalia Mogadishu | Dürre und Hungersnot
ምስል Mariel Müller/DW

ሶማልያ፤ የፕሬዝደንቱ ዛቻ፣ የአሸባብ ጥቃት

የደላዉ ለመዝናኛ የከፋዉ ሐሳብ ለመክፋያ ብቻ ብዙዉ ዓለም ጎል ይቆጥራል።የጠንካራ-ደካማ ቡድናትን ድል-ሽንፈት ያሰላል።ዩክሬን ከተማ-መንደሮችዋን የሚያወድመዉን የሩሲያ ሚሳዬልን እየቆጠረች ድርቅና ረሐብ ለሚያሰቃየዉ አፍሪቃዊ በጣሙን ለኢትዮጵያና ሶማሊያ ዜጎች የትምረዳዉን ስንዴ መጠን ለዓለም ትዘረዝራለች።ኢትዮጵያዉያን ሰሜን ግዛታቸዉን ያነፈረዉ ጦርነት ሰከን-ቀለል ሲል ምዕራብ ግዛታቸዉ ላይ የጎሳ ጥቃት፣ ምስራቅ ደግሞ ረሐብ «አለ እንደገና» እያሉ የዩክሬንን ስንዴ ይጠብቃሉ።የሶማሊያዉ የከፋ ነዉ።ከሰላሳ ዓመት በላይ ከጦርነት፣ግጭት፣ድርቅ ረሐብ ሌላ ብዙም ታሪክ የሌላት ሶማሊያ ዛሬም የጥይት፣ ቦምብ፣የረሐብ-በሽታ ሰለቦችዋን ትቆጥራለች።እስከ መቼ? ያፍታ ጥያቄያችን ነዉ አብራችሁን ቆዩ።
                      
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባለፈዉ ግንቦት አዲስ ለተመረጡት ለሶማሊያ ፕሬዝደንት ለሐሰን ሼኽ ሐሰን የላኩት ስጦታ ሌሎቹ መሪዎች ከላኩት ለየት፣ላቅ ያለም ነበር።ስጦታዉ ለአዲሱ ፕሬዝደንት የግል መገልገያ የሚዉል አልነበረም።ለረሐብ ለተጋለጠዉ የሐገሪቱ ሕዝብ የሚዉል ምግብና መድሐኒትም አይደለም።ጦር ኃይል ነዉ።የቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሶማሊያ ያስወጡት የአሜሪካ ልዩ ኮማንዶ ጦር ተመልሶ ሶማሊያ እንዲሰፍር ባይደን ወሰኑ።ሼኽ ማሕሙድ ለስጦት በትዊተር ባሰራጩት ምስጋና «ሶማሊያ ከአሸባሪዎች ጋር በምታደርገዉ ዉጊያ ዩናይትድ ስቴትስ አስተማማኝ ወዳጅ ናት» በማለት አወደሱ።
የየዩናይትድ ስቴትሱ የስልታዊና ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም (CSIS በእንግሊዝኛ ምህፃሩ» ሶማሊያን ለአካባቢዋ፣ ለዓለምም ጠቃሚ ይላታል።በተቋሚ የአፍሪቃ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ምቬምባ ፊዞ ዲዞልል ብዙዎች-ብዙ ጊዜ በዝርዝር ያሉና የሚሉትን ባለፈዉ መስከረም ባጭሩ አሉት።
                        
«ሶማሊያ በጣም ጠቃሚ ሐገር ናት።በአፍሪቃ ቀንድ ጫፍ ላይ ስለምትገኝ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥዋ በጣም ጠቃሚ ናት።በአካባቢዉ መልከዓምድዊ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ባላት ሚናም በጣም ጠቃሚ ናት።በሌሎች ዓለም ትኩረት ሊሰጣቸዉ በሚገቡ ጉዳዮች በፀጥታ፣በምግብ ዋስትና በዓየር ንብረት ለዉጥና በሌሎችም ጉዳዮች ጠቃሚ ሐገር ናት።»
ለአካባቢዉም ለዓለምም ጠቃሚ የሆነችዉ ሐገር ከ1991ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)ቁል ቁል ስትሰምጥ ዓለም ከጥፋት ሊያድናት ያልፈለገ ወይም ያልቻለበት ምክንያት በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።የቀድሞዉ የትምሕርትና የሰባዊ ርዳታ ባለሙያ ሐሰን ሼክ ማሕሙድ በ2012ለመጀመሪያ ጊዜ የያዙትን የፕሬዝደንትነት ስልጣን በ2016 ሲያገባድዱ ሐገራቸዉን ለጥፋት ከዳረገዉ በርካታ ግጭትና ጦርነት ሁሉ ዋነኘዉ አሸባብ የከፈተዉ የሽብር ጦርነት እንደሆነ አስታዉቀዉ ነበር።ቡድኑ ደግሞ ፕሬዝደንቱ አክለዉ እንዳሉት ዓለም አቀፍ እንጂ ብሔራዊ አጀንዳ ወይም ዓላማ የለዉም። ሶማሊያ፣የሽብር ምድር
                        
«አሸባብ ብሔራዊ አጀንዳ የሌለዉ ድርጅት ነዉ።ዓለም አቀፍ አጀንዳ ነዉ-ያላቸዉ።ብሔራዊ አጀንዳ እንዲኖራቸዉ ለማሳመን በባሕላዊና ኃይማኖታዊ ሽማግሌዎች አማካይነት ሞክረን ነበር።የተወሰኑት ያንን ለመቀበል ዝንባሌ አሳይተዉ ነበር።ብዙዎቹ ግን አልፈለጉም።ይሁንና እንደ ሶማሌ የፈለገዉን ዓይነት ብሔራዊ አጀንዳ ካላቸዉ ለመደራደር ዝግጁ ነን።»
ዉይይት ድርድር ተደርጎ ከነበረ ያመጣዉ ዉጤት የለም።አሸባብን በኃይል ለማንበርከክ ከ20ሺሕ የሚበልጠዉ የአፍሪቃ ሐገራት ጦር፣ ከ20 ሺሕ የሚበልጠዉ የሶማሊያ መንግስት ሠራዊት፣ በድብቅም በግልፅም ሶማሊያ የሰፈረዉ የዩናያትድ ስቴትስ ልዩ ሰራዊት፣ድሮኑም-ዶላሩም ያን አሸባሪ ቡድን ሊያጠፋዉ አልቻለም።ሰዉዬዉ ግን ከፕሬዝደንትነቱ ስልጣን ለ5ዓመታት ያክል አርፈዉ ዘንድሮ ግንቦት እንደገና ተመለሱበት።ሐሰን ሼክ ማሕሙድ። በ2016 የድርድርን ተስፋ ፈንጥቀዉ የነበሩት ሰዉዬ በ2022 ሰኔ ከዩናይትድ ስቴትስ በተደረገላቸዉ የልዩ ኮማንዶ ጦር ድጋፍ ተደፋፍረዉ ሐምሌ ላይ አሸባብን ለማጥፋት ዛቱ።ሕዝቡ ለሁሉን አቀፍ ጦርነት እንዲዘጋጅም አሳሰቡ። 
«የሶማሊያ ሕዝብ ማብቂያ የሌለዉ ሐዘንና የሐዘን ማፅናኛ እንደሰለቸዉ አዉቃለሁ።በነዚሕ፣ ሰላማችንን በሚያደፈርሱ አረመኔዎች ላይ በምንከፍተዉ ሁሉን አቀፍ ጦርነት እንድትሳተፉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።»
ሐምሌ ሁሉን አቀፍ ጦርነት አዉጀዉ መስከረም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ኒዮርክ ሲጓዙ ወደ ዋሽግተን ጎራ ብለዉ ነበር።የሁሉን አቀፍ ፀረ-አሸባብ ዘመቻቸዉን ስልት፣ ዉጤትና ዉድቀት አልጠቀሱም።ጠየቁ እንጂ።
                      
«እራሳችንን መጠየቅ ያለብን መሰረታዊ ጥያቄ ከ 15 ዓመታት ፀረ-ሽብር ዉጊያ በኋላ አሸባብ አሁንም አለ የሚለዉ ነዉ።በፀረ ሽብሩ ዉጊያ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቷል።ለቁጥር የሚያታክት ሕይወት ባሳዛኝ ሁኔታ ጠፍቷል፣ ብዙ ቆስለዋ፣ በድንጋጤ ተሰቃይተዋል። አሸባብ አሁንም አለ።እስኪ ትንሽ ረጋ ብለን እናስብ።ከ15 ዓመታት የዓለም አቀፍ ፀረ ሽብር ዘመቻ በኋላ አሁን አሸባሪዉ ቡድን ያልጠፋዉ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ስልታችን ተሳስቶ ይሆን?የቱጋ ነዉ ስሕተቱ?ይሕን ባለፉት 15 ዓመታት የታየዉን ስሕተት እንዴት ነዉ የምናስተካክለዉ» 
የፕሬዝደንቱ ጥያቄ መመለስ-አለመመለሱንም ሆነ የሚመልሰዉን ወገን ማንነት በርግጥ እናዉቅም።ግንቦት ላይ ዩናይትድ ስቴትስን ለፀረ ሽብር ዘመቻቸዉ «አስተማማኝ ወዳጅ» በማለት ያወደሱ-ያመሰገኑት፣ ሐምሌ ላይ አሸባብን ለማጥፋት ሙሉ ጦርነት ያወጁት፣ መስከረም ወር ዋሽግተን ላይ ጠይቀዉ፣ኒዮርክ ላይ የሚሉትን ብለዉ ሞቃዲሾ በተመለሱ በሁለተኛ ሳምንቱ ርዕሰ ከተማይቱ እንደገና በቦምብ ጥቃት ተሸበረች።በ2017ጥቅምት አሸባብ 500ሰዉ የፈጀበት የሞቃዲሾ መንደር በአምስተኛ ዓመቱ ዘንድሮ ጥቅምት ሌሎች ከአንድ መቶ በላይ ነዋሪዎችዋን ለቦምብ አረር ገበረች።የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት የኤርትራ ጉብኝት
አሸባብ ስፍራ፣ስልቱን እየቀያየረ ከተማ፣ መንደሮችን ሲያጋይ፣ሰላማዊ ሰዎችን ሲፈጅ የሶማሊያ ፣የአፍሪቃ ሕብረት፣ጦር፣ የዩናይትድ ስቴትስ ኮማንዶዎች፣ ድሮኖች ከሁሉም በላይ ዳናብ (መብረቅ ማለት ነዉ) የተባለዉ የሶማሊያ ልዩ ጦር አሸባብና ተባባሪዎቹ የሚላቸዉን የሶማሊያ ዜጎች ያድኑ ይገድሉ ነበር።በአብዛኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ያሰለጠነና ያስታጠቀዉ ዳናብ ሰሞኑንም 100 የአሸባብ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታዉቋል።ከአንድ መቶዉ ታጣቂዎች 60ዎቹ የተገደሉት ቡኩራ በተባለችዉ የደቡባዊ ሶማሊያ አነስተኛ ከተማና አካባቢ ነዉ።የዳናብ ጦር ቃል አቀባይ አስሊ ሐላኔ ባለፈዉ ሮብ እንዳለችዉ የአሸባብ ታጣቂዎች የከተማይቱን የመሰረተ ልማት አዉታሮች አዉድመዉታል።
«60 የአሸባብ ተዋጊዎችን ገድለናል።እዚሕ ከመድረሳችን በፊት ግን ሸሽተዉ ነበር።ከከተማይቱ ከመሸሻቸዉ በፊት ሁሉንም ነገር አቃጥለዉታል።ሱቆችን፣ቤቶችን፣የዉኃ ጉርጓዶችን አዉድመዋቸዋል።ሕዝቡ የሚጠጣዉ ንፁሕ ዉኃ እንኳ የለዉም።»
በአሸባብ፣ በመንግስትና በተባባሪዎቹ ኃይላት መካከል በሚደረገዉ ዉጊያ ላለፉት 15 ዓመታት የሚሰቃይ፣የሚፈናቀለዉ ሰላማዊ ህዝብ ዘንድሮ በድርቅ እየተፈናቀለ፣ በረሐብና ጠኔ የሚሞቱ ተጨማሪ ወገኖቹን መቅበር ግድ ሆኖበታል።ባይዶዎ ረሐብ የጠናባት አንዲት የአምስት ዓመት ታዳጊ በቀደም ተቀበረች።
                    
የለቀስተኛዉ ዱዓ፣ምሕላ፣ተማፅኖ እስካሁን ሰሚ ያገኘ አይመስልም።የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ወደ አፍሪቃ ለመላክ ያቀዱት 60 መርከብ ስንዴም ሶማሊዎችን ለማዳን አልደረሰም።ስሟ ያልተነገረዉ ሕፃን እስካሁን በረሐብና ረሐብ በሚያስከትለዉ በሽታ መሞታቸዉ ከተረጋገጠዉ ከ300 በላይ የሶማሊያ ሕፃናት አንዷ ናት።ባይዶዎ ሆስፒታል ለመድረስ የታደሉትን ልጆች ከሚያክሙት አንዱ ዶክተር አብዱላሒ ዩሱፍ እንደሚሉት ሕሙማኑን ለመርዳት በቂ መድሐኒት፣መሳሪያና የሰዉ ኃይል የላቸዉም።
                         
«በቂ ርዳታ አናገኝም።በቅርቡ ይደርሰናል የሚል ተስፋ አለን።ሁኔታዉ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።»
Save The Chileden የተባለዉ የብሪታንያ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ባልደረባ ዶክተር ቢኒያም ገብሩ እንደሚሉት ደግሞ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚደርሰዉ ድጋፍ ከሚያስፈልገዉ ርዳታ ግማሽ ያሕሉ ነዉ።
«በጣም ከፍተኛ ችግር ነዉ።የሚያስፈልገንን ድጋፍ በሚያስፈልገን መጠንና ጊዜ አናገኝም።የሚደርሰን ድጋፍ ከምንፈልገዉ ግማሽ ያሕሉን ነዉ።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ሶማሊያ፣ኢትዮጵያንና ኬንያን ዘንድሮ የመታዉ ድርቅ በምስራቅ አፍሪቃ የ40 ዓመት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሕዝብ ለረሐብ አጋልጧል።ሶማሊያ ዉስጥ ብቻ 6.7ሚሊዮን ሕዝብ ተርቧል።ከ1.5 ሚሊዮን የሚበልጡት ባብዛኛዉ ሕፃናት ለሕይወት በሚያሰጋ ረሐብና የምግብ እጥረት በሚያስከትለዉ በሽታ እየተሰቃዩ ነዉ። ሶስት መቶዉ ሞተዋል።ከብቶች አልቀዋል።
አሸባብም ያሸብራል።ባለፈዉ ሳምንት ሶስት የኬንያ ወታደሮችን ገደለ።ትናንት የሶማሊያ ባለስልጣናት የሚያዘወትሩትን የሞቃዲሾ ሆቴልን ይዞ 4ሰዉ ገደለ።በየስፍራዉ የሚፈጀዉ ሰላማዊ ሰዉ ቁጥር ግን ፕሬዝደንቱም «ተቆጥሮ የማያልቅ» ከማለት በላይ በትክክል አያዉቁትም።በሞቃዲሾዉ ጥቃት ምክንያት ዛሬ መደረግ የነበረበት የምክር ቤት ስብሰባ ተሰርዟል።ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ ግን ዛሬም አሸባብን ለማጥፋት መዛት-መፎከራቸዉን አላቆሙም።እስከ መቼ አናዉቅም።

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ
ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድምስል Feisal Omar/REUTERS
የአፍሪቃ ሕብረት ሰራዊት
የአፍሪቃ ሕብረት ሰራዊት ምስል Ilyas A. Abubakar/AU UN IST Photo/AFP
የአሸባብ ታጣቂዎች
የአሸባብ ታጣቂዎችምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance
ቱርክ ያሰለጠነቻቸዉ የሶማሊያ ጦር ባልደረቦች
ቱርክ ያሰለጠነቻቸዉ የሶማሊያ ጦር ባልደረቦችምስል Sadak Mohamed/AA/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ