ከሰባ በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ
ቅዳሜ፣ መስከረም 28 2015የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በሶማልያ ውስጥ ባለው የአልሸባብ ይዞታ ላይ በውሰደው ጥቃት አስራ አንድ የሽብር ቡድኑ አመራሮች እና ሰባ ያህል ታጣቂዎችን መግደሉን እና ቦታውን ነፃ ማውጣቱን የሶማሌ ክልል አስታውቋል። የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ ባወጣው መረጃ አስራ አንድ የቡድኑ አመራሮች እና ሰባ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኃላፊው የግል ስልክ ባለመስራቱ ማግኘት ባንችልም በጉዳዩ ላይ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር የሆኑትን አቶ ዑስማን መሀመድን በስልክ አስተያየት ጠይቀናል።
እሳቸው እንደሚሉት" በልዩ ኃይል ጥቃት የተወሰደበት የአልሸባብ ይዞታ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት እና እራሱ ልዩ ኃይሉን ለማጥቃት ይዘጋጅበት የነበረ ነው።
"የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ቡድኑ ላይ እየወሰዱት ያለው እርምጃ ሶማሊያን የማገዝ የላቀ ሚና እየተወጣ መሆኑን አመላካች ነው" ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣናት መግለፃቸውን ተናግረዋል አቶ ዑስማን አስረድተዋል።
ሰሞኑን የተካሄደዋ ጦርነት ድል ለሶማሊያ ትልቅ እድል የፈጠረ እና የአልሸባብ መጥፊያ ቀኑ ቅርብ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም አቶ ዑስማን ጠቁመዋል።
የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር ህብረተሰቡን ደጀን በማድረግ በአልሸባብ ላይ እየወሰደበት ባለው ርምጃ የተገኘው ድል ቡድኑን ለማጥፋት እየተንቀሳቀሰች ለምትገኘው ሶማሊያ ጠቃሚ ልምድ እንደሚሆን ተገልፆል ።
አልሸባብ ከወራት በፊት በሶማሌ ክልል ጠረፋማ አካባቢዎች በመዝለቅ ጥቃት መፈፀሙና በአፀፋው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።
መሳይ ተክሉ
ታምራት ዲንሳ