1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስተግበሪያ ሕግጋትና ተቋማት

ሐሙስ፣ ሰኔ 6 2016

ሚያዝያ 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሚያስፈጽሙ ተቋማትን ለማቋቋም ይረዳሉ የተባሉ «የሥነ ሥርዓት እና ፍሬ ነገር ሕጎች» እየተዘጋጁ ነው ተባለ። ፍትሕ ሚኒስቴር ዝርዝር ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቆ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ሰሞኑን አሳውቋል።

https://p.dw.com/p/4h08X
የፍትሕ ሚንስቴር
የፍትሕ ሚንስቴርምስል Solomon Muchie/DW

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ያቀፋቸው ዋና ዋና ጭብጦች

ሚያዝያ 9 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሚያስፈጽሙ ተቋማትን ለማቋቋም ይረዳሉ የተባሉ «የሥነ ሥርዓት እና ፍሬ ነገር ሕጎች» እየተዘጋጁ ነው ተባለ። ፍትሕ ሚኒስቴር በፀደቀው ፖሊሲ የትግበራ ምዕራፍ የሚከናወኑ ያላቸውን ተግባራትን በዝርዝር የያዘ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቆ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ሰሞኑን አሳውቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ «በተለያዩ ጊዚያት የተከሰቱ መጠነ-ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እና ውስብስብ ችግሮችን» የወንጀል ተጠያቂነት በማስከተል፣ እውነትን በማፈላለግ፣ ይፋ በማውጣት እና ዕርቅ በማውረድ፣ በምህረት እንዲሁም በማካካሻ ስልቶች መፍትሔ ይሰጣል የተባለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፤ መንግሥት በዚህ ወቅት ትኩረት ሰጥቶት እየሠራበት መሆኑን ደጋግሞ አሳውቋል።

የፖሊሲው ማስፈጸሚያ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ለውይይት መቅረቡ

ፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለመተግበር  የሚቋቋሙ "ነጻ እና ገለልተኛ" ያላቸው ተቋማት፤ ተቋቁመው ሁሉም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማስተግበሪያ ስልቶች ሥራ ላይ እስኪያውሉ ድረስ "በፖሊሲው የትግበራ ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር የያዘ  ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቆ  ለውይይት ዝግጁ መሆኑን" ያስታወቀው በዚሁ ሳምንት ነው።

የተዘጋጀው ረቂቅ ፍኖተ ካርታ "የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአባልነት የሚሳተፉበት፤ ጊዜያዊ እና ዘላቂ ተቋማዊ የቅንጅት አመራር ሥርዓት ስለሚቋቋምበት ሁኔታ፤ ስለ ሽግግር ፍትሕ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል፣ ተቋማቱን ለማቋቋም እና ከተቋቋሙም በኋላ ሥራቸውን ስለሚሰሩበት ሁኔታ" የሚደነግጉ የተባሉ የሕግ ማዕቀፎች የሚዘጋጁበት ዝርዝር ተግባራት መቀረፃቸው ተነግሯል።

ፍኖተ ካርታው በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት "የክልሎችን፣ የባሕላዊ ፍትሕ ሥርዓቶችን፣ የተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሚና፣ ተሳትፎ እና ኃላፊነት" በተመለከተም በዝርዝር ማካተቱ ተጠቅሷል።

ፍትሕ ሚኒስቴር በግልጽ የፖሊሲው ትግበራ መቼ እንደሚጀመር ባይገልጽም "የማስተግበሪያ ሰነዶች ላይ የሚደረጉት ውይይቶች ሲጠናቀቁ" የፖሊሲው ትግበራ ምዕራፍ ዋና ዋና ተግባራት መከናወን ይጀመራሉ ብሏል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ፍኖተ-ካርታ ለውይይት ቀረበ።
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ፍኖተ-ካርታ ለውይይት ቀረበ። ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ እንዲሁም ከሚኒስቴሩ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ድርጊት መርሃ - ግብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማብራሪያ ለመጠየቅ ደጋግመን ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።

ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከካቢኔ አባላት ጋር በተደረገ ውይይት፤ ፖሊሲውን ለመተግበር የሚያስችሉ ተቋማትን ለማቋቋም ይረዳሉ የተባሉ የሥነ ሥርዓት እና የፍሬ ነገር ሕጎች እየተዘጋጁ መሆኑን መንግሥት ለሚያስተዳድራቸው መገናኛ ብዙኃን ገልፀዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ያቀፋቸው ዋና ዋና ጭብጦች

ሥራውን አጠናቆ የተበተነው 13 አባላት የነበሩት  የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አርቃቂ የባለሞያዎች  ቡድን "ጉልህ በሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወይም ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የክስ ሂደት ሊኖር ይገባል"፣ "አዲስ ወይም ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክስ የመስማት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባር ማከናወን ይገባል"፣ "አሁን ካለው የምርመራ እና የዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጭ የምርመራ እና የክስ ሂደቶችን የሚያስተባብር ልዩ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የምርመራ እና የክስ ሥራ የሚሠራ ተቋም በማቋቋም እንዲሁም የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን የምርመራ ባለሙያዎች እና ዐቃቤ ሕግ በመመደብ" ሥራው ሊከናወን ይገባል"፣ ይህም "በአዲስ የእውነት አፈላላጊ ተቋም" አማካኝነት መከናወን አለበት" የሚል ሀሳብ አቅርቦ ነበር።

የመብት ድርጅቶች፣ የፓርቲዎች አስተያየትና ማሳሰቢያ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንም በኢትዮጵያ "ሐቀኛ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት" ተግባራዊ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ባወጣው መግለጫ ጠይቆ ነበር። ኮሚሽኑ "መንግሥት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን በማያሻማ መልኩ እንዲያሳይም "ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኪሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግሮችን ይፈታሉ ብለው እንደ ብቸኛ አማራጭ ከተመለከቷቸው ውስጥ፣ ሀገራዊ ምክክር አንዱ ሲሆን፣ የሽግግር ፍትሕ ሌላኛው መሆኑን በቅርቡ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

የፍትሕ ሚንስቴር
የፍትሕ ሚንስቴርምስል Solomon Muchie/DW

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ "ሂደቱ በአዲስ አበባ  ያለ ትግራይ ተሳትፎ የተጀመረ"  እና ከተጠያቂነት አንፃር "በኤርትራ የተፈፀሙ" ያሏቸውን ጥፋቶች በማንሳት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ አሰራር ሂደት "ክፍተቶች ያሉት"፣ "በርካታ ወንጀሎችን የፈፀሙ አካላትን ጭምር ተጠያቂ ሊያደርግ የማይችል" መሆኑን ከዚህ በፊት ጠቅሰው ነበር።

ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከሽግግር ፍትሕ በፊት አስፈላጊው የሽግግር መንግሥት ነው በሚል ሲሞግቱ ይደመጣሉ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ