1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችየመካከለኛው ምሥራቅ

የቀይ ባሕር ቀውስ ፦ ሌላ የዓለም ትኩሳት

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ ጥር 4 2016

ሑቲዎች በቀይ ባሕር የሚቀዝፉ ግዙፍ መርከቦች ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ለማስቆም አሜሪካ መራሹ ጥምረት በየመን ድብደባ ጀምሯል። በቀይ ባሕር የበረታው ውጥረት ከእስያ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ መርከቦች በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል እንዲዞሩ አስገድዷል። ቀውሱ ቴስላ በጀርመን የሚገኝ ፋብሪካው ለሁለት ሣምንታት ሥራ እንዲያቆም አስገድዶታል

https://p.dw.com/p/4bCpy
የሜርስክ ግዙፍ መርከብ
ሜርስክ እና ሐፓግ ሎይድን የመሳሰሉ ግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች ስዊዝ ቦይ ሲያሰጋቸው በደቡብ አፍሪካው ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ለመዞር ተገደዋል።ምስል Karim Sahib/AFP

የቀይ ባሕር ቀውስ ፦ ሌላ የዓለም ትኩሳት

የአሜሪካው መኪና አምራች ኩባንያ ቴስላ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን አቅራቢያ በሚገኝ ፋብሪካው ለሁለት ሣምንታት አብዛኛውን ሥራውን እንደሚያቆም አስታውቋል። ፋብሪካው ሥራውን የሚያቆመው መኪና ለማምረት በሚያስፈልጉ አካላት እጦት ምክንያት ነው። በቀይ ባሕር ላይ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት መርከቦች የጉዞ መስመራቸውን በመቀየራቸው ቴስላ የግብዓት እጥረት እንደገጠመው አስታውቋል።

በግሩንሐይደ የሚገኘው የቴስላ ፋብሪካ ሥራ ከጀመረ ገና ሁለት ዓመታት ገደማ ብቻ ይሁነው እንጂ 11 ሺሕ 500 ሠራተኞች አሉት። የኤሌክሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ሥራ ማቋረጡን ይፋ በማድረግ ቀዳሚ ቢሆንም የቻይና እና የስዊድን ኩባንያዎች ለደንበኞቻቸው የሚልኳቸው ምርቶች እንደሚዘገዩ አስጠንቅቀዋል።

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሑቲዎች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ግዙፍ የዓለም የመርከብ ኩባንያዎች በስዊዝ ቦይ በኩል የነበራቸውን ጉዞ እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል። ይኸ መስመር ከእስያ ወደ አውሮፓ ለሚጓዙ መርከቦች ፈጣኑ መንገድ ነው።

ከዓለም የመርከብ ጉዞ 12 በመቶው በዚሁ በኩል የሚደረግ ነው።ከእስያ ወደ አውሮፓ የሚቀዝፉ ግዙፍ መርከቦች በስዊዝ ቦይ በኩል ማቋረጥ ካልሆነላቸው መላ አፍሪካን ሲዞሩ ተጨማሪ 6,482 ኪሎ ሜትሮች መጓዝ አለባቸው።

በጀርመን በርሊን አቅራቢያ የሚገኘው የቴስላ ግዙፍ ፋብሪካ
በቀይ ባሕር ላይ በተፈጠረ ውጥረት ምክንያት ግብዓቶች እንዳሻው ለማግኘት የተቸገረው ቴስላ ከበርሊን አቅራቢያ በሚገኝ ፋብሪካው ለሁለት ሣምንታት በከፊል ሥራ እንደሚያቆም አስታውቋልምስል Patrick Pleul/dpa/picture alliance

ሜርስክ እና ሐፓግ ሎይድን የመሳሰሉ ግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች ስዊዝ ቦይ ሲያሰጋቸው በደቡብ አፍሪካው ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ለመዞር ተገደዋል። ይኸ መስመር ከእስያ ወደ ሰሜን አውሮፓ ለመድረስ አስር ተጨማሪ ቀናት ይወስዳል። መንገዱ ሲራዘም ኩባንያዎቹን እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ወይም (910 000 ዩሮ) ተጨማሪ የነዳጅ ወጪም ይዳርጋል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኮንግደምን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ያቀፈው ጥምረት በሑቲዎች ላይ ተከታታይ ድብደባዎች ጀምሯል። አሜሪካኖች የሑቲዎችን ዒላማዎች በሚሳይሎች እና ቦምቦች ሲደበድቡ የጦር መርከቦች፣ ተዋጊ ጀቶች እና ሰርጓጅ መርከቦች ጭምር መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

የድብደባው ዒላማ የሆኑት አሜሪካኖች እንዳሉት ባለፉት ሣምንታት ሑቲዎች ቦምብ የተጫኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ያስወነጨፉባቸው መንደርደሪያዎች ናቸው። ባለፈው ሐሙስ ከተፈጸመው ድብደባ በኋላ የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፓትሪክ ራይደር “የሑቲዎችን እንዲህ አይነት ግድየለሽ እና ሕገ-ወጥ ጥቃቶች የመፈጸም አቅም ለማዳከም በ16 የተለያዩ ቦታዎች በርካታ ዒላማዎች ላይ ድብደባ ተካሒዷል” ሲሉ ተናግረዋል

ሑቲዎች በድብደባው አምስት ሰዎች መገደላቸውን ሌሎች ስድስት መቁሰላቸውን አስታውቀዋል። በሰንዓ፣ ሑዴይዳ፣ ታዒዝ፣ ሖጃ እና ሳዳ ድብደባ መፈጸሙን የተናገሩት የሑቲዎች ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጄኔራል ያሕያ ሳሬኢ “የየመን ጦር ኃይሎች ለየመን ሉዓላዊነት እና ነጻነት የሥጋት ምንጮችን በምድር እና በባሕር የሚገኙ ጠበኛ ዒላማዎች ከመምታት አያመነቱም” ሲሉ ዝተዋል።

በየመን ዋና ከተማ ለጋዛ ሕዝቦች ድጋፍ በተጠራ ሰልፍ ላይ የተሳተፈ ወታደር
የሑቲ አማጽያን አሜሪካ እና ብሪታኒያ በየመን ከፈጸሟቸው ድብደባዎች በኋላ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋልምስል Mohammed Huwais/AFP

“ይኸ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት የመን ለተበደለው የፍልስጤም ሕዝብ ያላትን የድጋፍ አቋም አይቀለብሰውም” ያሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ያሕያ ሳሬኢ “የየመን ጦር ኃይሎች በኃይል ወደ ተያዘው የፍልስጤም ወደቦች የሚሔዱ፣ በአረቢያን እና በቀይ ባሕር የሚቀዝፉ የእስራኤል መርከቦችን ማስቆማቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከሑቲዎች ማስጠንቀቂያ በኋላ አሜሪካ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት በየመን ቶምሐውክ በተባሉ ሚሳይሎች ተጨማሪ ድብደባዎች ፈጽማለች። ከጦር መርከብ ላይ የተተኮሱት ሚሳይሎች በየመን የራዳር መቆጣጠሪያ ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን አሜሪካ ገልጻለች።

አሜሪካ እና አጋሮቿ በቀይ ባሕር የሚቀዝፉ መርከቦች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ለማስቆም የሑቲዎችን ወታደራዊ አቅም ለማኮላሸት ዕቅድ አላቸው። ሑቲዎች ግን ጥቃታቸውን የማቆም ውጥን ያላቸው አይመስልም። ዋና ዓላማቸው የእስራኤልን የጋዛ ጦርነት ለማቆም ጫና ማሳደር ነው።

የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ በቀይ ባሕር
ሑቲዎች በቀይ ባሕር የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማቆም አሜሪካ መራሹ ጥምር ኃይል ወታደራዊ መርከቦች አሰማርቷልምስል U.S. Navy/abaca/picture alliance

በቻታም ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ክፍል ባልደረባ የሆኑት ፋሬአ አል-ሙስሊሚ የቀይ ባሕር ቀውስ መፍትሔ የሚያገኘው የፍልስጤም ጉዳይ ሲፈታ እንደሆነ ያምናሉ።

“ከእንግዲህ በቀጠናውም ይሁን በየመን ምክንያት ወይም ሚዛናዊነት ያሸንፋል። አለበለዚያ ቅልጥ ወዳለ ሲዖል እንወርዳለን” የሚሉት ፋሬአ አል-ሙስሊሚ “በየመን እየሆነ ያለው የፍልስጤም ጉዳይ ነጸብራቅ እና መዘዝ እንደሆነ አምናለሁ። የየመን መረጋጋት፣ በአጠቃላይ የቀጠናው መረጋጋት ከጋዛ መጀመር አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

በየመን አሜሪካ እና አጋሮቿ የፈጸሙት ድብደባ በሑቲዎች እጅ በምትገኘው ሰንዓ እንዲሁም በሊባኖስ እና በኢራን ኃይለኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። የቀይ ባሕር ውጥረት ወደ ሌላ ግጭት እንዳይቀሰቅስ የሚያሰጋ ነው። ሑቲዎች እንዳሉትም መልሰው ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ። አሜሪካኖች ለበቀል የሚወስዱት ሌላ ዙር እርምጃ የሊባኖሱን ሒዝቦላሕ አሊያም ኢራንን ጎትቶ ወደ ግጭቱ ሊያስገባ ይችላል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ