የቀጠለዉ የኢትዮጵያ እና ሶማልያ ዉዝግብ
ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2016የሶማሊያዉ ፕሬዝዳንት ለኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ምላሽ ሰጡ
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ችግሮችን "በትብብር ለመፍታት አናግራን አታውቅም" ሲሉ ቅዳሜ ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ገለፁ።
ከሶማሊኛ ወደ እንግሊዝኛ በተተረጎመው የፕሬዝዳንቱ ንግግር "የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት የመልካም ጉርብትና እና ዓለም አቀፍ ሕግ መርህን ጥሷል፣ ዛሬ ደግሞ ሕገ ወጥ በሆነ አቋሙ ፀንቷል" በማለት ኢትዮጵያ ከራስ ገዝ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት በማንሳት ወቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የሶማሊያ መንግሥት በአንድ ሰዓት በረራ እና ውይይት ይሄን ነገር መልክ ማስያዝ ይችላል" በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩ ሲሆን የሶማሊያ መንግሥት ግን "እኛን ከማናገር በየሰፈሩ እየዞረ መክሰስ መርጧል" ብለው ነበር። የሶማሊያው ፕሬዝደንት በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን "እየተዘዋወሩ ሽምግልና ይጠይቃሉ" ሲሉ ተችተዋል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ንግግሮች
ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግባቸው ቀጥሏል። ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቷ አንድ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ራስ ገዝ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመችበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ሞቅዲሾ መካከል የተካረረው ውዝግብ እና አለመግባባት በሁለቱ ሀገራት የፓርላማ ንግግሮች ቀጥሏል።የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ሙሐሙድ ቅዳሜ ዕለት ለሀገራቸው ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያን በግጭት ጠንሳሽም እና አባባሽነት ከሰዋል።
"ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት ሀገር ወቅታዊ ጉዳዮችን በትብብር ለመፍታት አናግራን አታውቅም፤ እየተዘዋወሩ ሽምግልና ይጠይቃሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት የመልካም ጉርብትና እና ዓለም አቀፍ ሕግ መርህን ጥሷል፣ ዛሬ ደግሞ ሕገ ወጥ በሆነው አቋሙ ጸንቷል። ሶማሊያ ይህን ውዝግብ አልፈጠረችም፤ ስምምነት እንዳይደርስም እንቅፋት አልሆነችም"።
ከዚህ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ጎረቤት ሀገራት በሰጡት ማብራሪያ "የሶማሊያ መንግሥት በአንድ ሰዓት በረራ እና በአንድ ሰዓት ውይይት ይሄን ነገር መልክ ማስያዝ ይችላል። በጣም ቀላል ነገር ነው። ምክንያቱም ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ምንም ጠብ የለንም። የሶማሊያ መንግሥት የመረጠው ግን እኛን ከማናገር በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ መርጧል" ብለው ነበር።
የቱርክ አሸማጋይነት ሚናና የቀጣይ ሂደት
ከቀናት በፉት የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ አሸማጋይነት አንካራ ውስጥ በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ንግግር አድርገዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ሀገራት "መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሔዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክከሮችን ለመቀጠልም ተስማምተዋል" ሲል ገልጾ ነበር። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምበሳደር ነቢዩ ተድላ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ በዚህ ድርድር ውስጥ "የየትኛውም ሀገር ጣልቃ ገብነት የለም" ብለዋል።
ሌሎች የውዝግብ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች
በዚሁ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩን የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ የሁለቱ ሀገራት ሁኔታ ከግጭት ጦርነት ይልቅ በንግግር መፈታቱ የማይቀርመሆኑን ገልፀዋል። "የተለያዩ ንግግሮች ይኖራሉ ብየ ነው የምወስደው። ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብም፣ ሀገራትም ያልተገደበ ፍላጎት ስላላቸው ወደ ጦርነት መገባቱን አይፈቅዱትም"።
ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበሬን ጥሰው ወደ ግዛቴ ገብተዋል በሚል ሶማሊያ በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ላይ ክስ ያቀረበች ቢሆንም ኢትዮጵያ ይህ "መሰረተ ቢስ ነው" ስትል አጣጥላዋለች። ሶማሊያ ውስጥ በቅርቡ ተልዕኮው የሚጠናቀቀው "የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ" የተባለውን ኃይል ተክቶ በሚገባው ዓለም አቀፍ ኃይል ውስጥ የኢትዮጵያ ሠራዊት ስለሚኖረው ተሳትፎ ከሶማሊያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ ሕብረትም ሆነ ከተባበሩት መንግሥታት የደረሰ ነገር እንደሌለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን ሶማሊያ በበኩሏ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት ካልተወች በሰላም ማስከበር ተልዕኮው የኢትዮጵያ ወታደሮች ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንደማትፈቅድ መግለጿ ይታወሳል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ