የቀጠለው ችግኝ ተከላና ተስፋው
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 6 2013ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስር ዓመታት በፊት ወደ 3 በመቶ መውረዱ ሲነገርለት የነበረው የደን ሽፋን በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ወደ 15,7 በመቶ ከፍ ማለቱን የዓለም የደን ሀብት ቅኝት መዘርዝር ያሳያል። እርግጥ ነው በሀገሪቱ የችግኝ ተከላ ዘመቻ መካሄዱ እንግዳ አይደለም። ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን ብዙዎችን የሚያሳስበው ግን ምን ያህሉ ይጸድቃል የሚለው ነው። በያዝነው ክረምት ኢትዮጵያ አምስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ማቀዷን፤ ለጎረቤቶቿም እንዲሁ አንድ ቢሊየን ችግኞችን ለማከፋፈል መዘጋጀቷ ተነግሯል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሚሊየኖች የሚቆጠር ችግኝ በክረምቱ መግቢያ በዘመቻ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች መተከሉ ይታወሳል። ዘንድሮ ደግሞ «ኢትዮጵያን እናልብሳት» በሚል መሪ ቃል በቢሊየኖች የተገመተ ችግኝ ሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሃገራትም የማዳረስ ዘመቻው እየተካሄደ ነው። የአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ ንጉሤ ኢትዮጵያን እናልብሳት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ችግን ከመትከል በላይ ነው ይላሉ።
«እኔ ኢትዮጵያን እናልብሳት የሚለውን መሪ ቃል ከችግኝ መትከል በላይ ነው የሚል እምነት አለኝ። ኢትዮጵያን እናልብሳት በምንልበት ጊዜ ኢትዮጵያ በድህነት ምክንያት ተራቁታለች፤ ኢትዮጵያ በሥራ አጥነት ምክንያት ችግር አለባት፣ እነዚህ ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ደግሞ ይሰደዳሉ ስለዚህ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የአየር ንብረት ብዝሃ ሕይወት በምንመለከትበት ጊዜ ኢትዮጵያ በደን ሀብት በልጽጋ የራሷን ፍላጎት አሟልታ በአፍሪቃ ደረጃ በተለይም ደግሞ የአፍሪቃ ቀንድ በሚባለው እና ከዚያም ባለፈ በመካከለኛው ምሥራቅም የደን ምርቶችን አቅራቢ ልትሆን ትችላለች የሚል እምነት አለኝ። ይኽን የምለው ካለው እምቅ ሀብት በመነሳት ነው።»
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ውሎ አድሮ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ንግድም ሊውል የሚችል እምቅ ሀብት ነው የሚሉት የደን ልማት ባለሙያው የዘመቻው የችግን ተከላ እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን የማቀራረብ ሚናም እንዳለው ነው የሚያስረዱት። በዘመቻ ችግኝ በመትከል ጥረት በተለያየ ምክንያት የተጎሳቆለ መሬታቸውን በደን ልማት ማሳደግ የቻሉ በርካታ ሃገራት አሉ። ኢትዮጵያም ይኽንኑ እንቅስቃሴዋን አጠናክራ በመቀጠል የደን ሽፋኗን ከፍ በማድረጉ በኩል እየሠራች መሆኗን እየገለጸች ነው። የአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጥላዬ በመካሄድ ያለው የዘመቻ ችግኝ ተከላው ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ በመሆኑ ድጋፍ ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።
በዘመቻ ችግኞችን የመትከሉ ጥረት ተጠናክሮ ሲቀጥልም አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር ከምንለው ጎን ለጎን ደን አደር ማለትም ደን አልምቶ ገቢውን ከዚያ በሚያገኘው ጥቅም ኑሮውን የሚመራ ማኅበረሰብም መፍጠር እንደሚያስችም ነው የገለጹልን። ለሰጡን ማብራሪያ የአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ ንጉሤ እናመግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ