1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለው የደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ ዞን

ዓርብ፣ ግንቦት 9 2016

ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ለሁለተኛ ጊዜ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ሠልፍ የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች አቤቱታቸውን ለማሰማት ወደ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በማምራት ላይ እንዳሉ በፖሊስ ተበተኑ፡፡ የፀጥታ አባላቱ መንገዱን በፖሊስ ተሽከርካሪዎች በመዝጋት ሠልፈኛው ወደ መጣበት እንዲመለስ ማድረጋቸውን ነው የሠልፉ ተሳታፊዎች የተናገሩት፡

https://p.dw.com/p/4g0Eq
ከሁለት እሰከ ሦስት ወራት ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች
ከሁለት እሰከ ሦስት ወራት ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞችምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የቀጠለው የደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ ዞን

የቀጠለው የደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ ዞን

ከሁለት እሰከ ሦስት ወራት ደሞዝ አልተከፈለንም ያሉ የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ጥያቄያቸውን በሠልፍ እያቀረቡ ይገኛሉ ፡፡ ያምሆኖ እስከአሁን ለጥያቄያቸው ከዞንና ከክልል መስተዳድሮች አጥጋቢ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ሠራተኞቹ ተናግረዋል ፡፡ በዚህም የተነሳ አሁን ላይ ከነቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መውደቃቸውን የተጠቀሱት ሠራተኞቹ ትናንት ለሁለተኛ ጊዜ ጥያቄያቸውን ለማሰማት መሰባሰባቸውን ተናግረዋል ፡፡

የተበተነው ሠልፍ

ሠራተኞቹ ትናንት በድጋሚ በዎላይታ ሶዶ ከተማ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ያደረጉት ሠልፍ በፀጥታ አባላት መበተኑ ነው የተነገረው ፡፡ ሠልፈኞቹ ከሶዶ ዙሪያ ወረዳ የተለያዩ ጽህፈት ቤቶች የተሰባሰቡ ናቸው ፡፡  ሠራተኞች ወደ ዎላይታ ዞንና ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤቶች በመጓዝ ላይ እንደነበሩ የጠቀሱት ሁለት የሠልፉ ተሳታፊዎች “ ይሁንእንጂ ዞን ፍርድ ቤት አካባቢ ሥንደርስ የፀጥታ አባላቱ በፖሊስ ተሽከርካሪዎች መንገድ ዘግተው በማስቆም “ ሠልፉ ህገ ወጥ ሥለሆነ ከዚህ ማለፍ አትችሉም “ አሉን ፡፡ የፀጥታ አባላቱ ተበትናችሁ ወደ ኋለ ተመለሱ ቢሉንም እኛ የጠየቅነው የዳቦ ጉዳይ ነው ሌላ ዓላማ የለንም የሚል ምላሽ ብንሰጣቸውም ሊሰሙን አልቻሉም ፡፡ በዚህም የተነሳ  መስተዳድሩ ጽህፍት ቤት መድረስ ሳንችል ቀርተናል “ ብለዋል ፡፡

የደሞዝ ጉዳይ በትምህርት ላይ ያሳደረው ተፅኖ

በዎላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ የትምህርት አገልግሎት ተቋርጦብናል ያሉ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በወረዳው የአስተዳደር ከተማ በዴሳ ላይ ሠልፍ አድርገዋል ፡፡ ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ መምህራን ወደ ትምህርት ቤት ባለመምጣታቸው የልጆቻቸው ትምህርት መቋረጡን የጠቀሱት ሦስት የተማሪ ወላጆች ተማሪዎቹ የአካባቢው አስተዳደር መፍትሄ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ተናግረዋል ፡፡

ዎላይታ ሶዶ ከተማ
ዎላይታ ሶዶ ከተማ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ተማሪዎቹ በቡድን በመሰባሰብ ወደ ወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት መምጣታቸውን የዳሞት ወይዴ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ናና ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ ወደ ጽህፈት ቤታችን የመጡት ተማሪዎች ከመምህራን ደሞዝ ጋር በተያያዘ ትምህርት እያገኙ እንዳልሆነመናገራቸውን የጠቀሱት አቶ ስንታየሁ “ በእኛ በኩል ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል እንደምናቀርብ ገልጸንላቸዋል ፡፡ ይሁንአንጂ ተማሪዎቹ እንደገና ለተመሳሳይ አቤቱታ  ወደ ወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሄደዋል ፡፡ ከአስተዳደሩ  ምን ምላሽ እንደተሰጣቸው አልሰማሁም “ ብለዋል ፡፡

በዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞችና ተማሪዎች ያቀርቡትን አቤቱታ አስመልክቶ የዞኑንም ሆነ የክልል መስተዳድሮች እስከአሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም  ፡፡  ዶቼ ቬለ የዞንና የክልል የስራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያድርግም ሃላፊዎቹ ከትናንት ጀምሮ የድርጅት ስብሰባ ገብተዋል በመባሉ በጉዳዩ ላይ  ምላሽም ሆነ ማብራሪያ ማግኘት አልተቻለም ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ