የበረሃ አንበጣ መንጋ በምሥራቅ አፍሪቃ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 14 2012ከየመን ወደአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሃገራት የበረሃ አንበጣ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ መግባቱን የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የአዝዕርት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶ ደጋግመው ለዶቼ ቬለ በሰጧቸው ቃለመጠይቆች ጠቁመዋል። በምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ከ25 ዓመት በኋላ በብዛት የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO ባለፈው ሳምንት ባወጣው ተከታታይ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጠቁሟል። በትግራይ እና አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋው በርክቶ ሲከሰት ካዩት ሁለት አስርት ዓመታት እንደሚበልጥ በወቅቱ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ገልጸውልናል። ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ የአንበጣ መንጋ እንዲህ በርክቶ የታየበት የተለየ ምክንያት ይኖር ይሆን ያልናቸው በFAO ከፍተኛ የአንበጣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ ኬትዝ ኬርስማን ጉዳዩ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሳይዛመድ አይቀርም ባይ ናቸው።
«በእኔ አመለካከት ለዚህ ዓመቱ የአንበጣ ክስተት ምክንያት የሚሆነው የአየር ሁኔታው ነው። ለነገሩ የዚህ ዓመት ብቻ ሳይሆን ያለፈው ዓመት የአየር ጠባይም ተፅዕኖ አለው። የአረብ ባሕረ ሰላጤ እና ምሥራቅ አፍሪቃ ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ የባሕር ማዕበሎች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ተከስተዋል። እናም እያንዳንዱ የባሕር ማዕበል በጣም ከባድ ዝናብ አስከትለዋል። የመጨረሻው የባሕር ማዕበል በያዝነው ወር መጀመሪያ ገደማ ሶማሊያ ላይ የደረሰው ነው። ከባዱ ዝናብ ደግሞ ለአንበጣ መራባት አመቺ ሁኔታን ፈጠረ፤ ይህ ነው የአንበጣው መንጋ ቁጥር እንዲጨምር ስለረዳው ነው በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የመንጋው ወረራ እንዲፈጠር አደረገ።»
የዚህ የአንበጣ መንጋ ወረራ በተከሰተባቸው በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እና ሶማሊያ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰ መረጃ እንደደረሳቸውም አክለው ገልፀዋል። ባለሙያው እንደሚሉትም የአንበጣው መንጋ በደረሰ ማሳ ላይ አንዴ ከሰፈረ ከቦታው ሲነሳ ሰብሉን ምንም ሳያስቀር አውድሞ ነው የሚሄደው። የአንበጣ መንጋ ወርሯቸው የነበሩ የአማራ አንዳንድ አካባቢዎች አሁን ከአንበጣው ነፃ መሆናቸውን የክልሉ የሚመለከተው አካል ገልጿል። በFAO ከፍተኛ የአንበጣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ ኬትዝ ኬርስማን እንደሚሉት አንበጣ በባህሪው የሚመቸውን ስፍራ እየመረጠ የሚሰደድ በመሆኑ ይህ እውነት ቢሆንም አይመለስም ማለት ግን አይደለም።
«እውነት ነው እንደምታውቂው አንበጣ ተሰዳጅ ተባይ ነው። የአካባቢው ሁኔታ የማይመቸው ከሆነ ያደጉት አንበጣዎች ይሰደዳሉ። ኢትዮጵያን በተመለከተ እዚያ አካባቢው የተፈለፈለው መንጋ ገሚሱ ወደሰሜን ወደ ኤርትራ ወደቀይባሕር ዳርቻ ሄዷል፤ ገሚሱ ደግሞ በኤርትራ የቀይ ባሕር ዳርቻ በኩል ወደ ሳውድ አረቢያ መሄዱን አውቀናል። ቀሪው ከሰሜን ኢትዮጵያ የተሰደደው መንጋ ወደምሥራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን ወደምንለው አካባቢ እና ወደ ሶማሊያ አቅጣጫ ሄዷል።»
በእርግጥም የአንበጣው መንጋ ወደኦጋዴን አካባቢ ፊቱን አዙሯል። ሁኔታውን ለመከታተል ወደስፍራው የሄዱት የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የአዝዕርት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሰላቶን ከቦታው ስለሁኔታው ጠይቄያቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል።
ኬትዝ ኬርስማን እንደገለፁት አንበጣ የሚራባበት አመቺ የአየር ንብረት እና አካባቢ ይፈልጋል። በዚህ ወቅት ይህን ፍላጎቱን የሚያሟሉለት አካባቢዎች የትኞቹ ይሆኑ? ባለሙያው እንዲህ ነው የሚሉት።
«አዎ እነዚያ በዚህ ወር መጀመሪያ በባሕር ማዕበሉ ምክንያት ከፍተኛ ዝናብ ያገኙ አካባቢዎች ናቸው። ይህም ማለት የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሙሉ፤ እነዚህም የምሥራቅ ሐረር ከፍተኛ አካባቢዎች፤ የኦጋዴን በረሀ፤ ይህ ደግሞ እስከ ሰሜን እና ማዕከላዊ ሶማሊያ እና ደቡብ ሶማሊኢ ይዘልቃል። ይህ ደግሞ በጣም ሰፊ አካባቢ ነው። እነዚህ አካባቢዎች በባሕር ማዕበሉ ምክንያት ከፍተኛ ዝናብ ባያገኙ ኖሮ፤ ችግሩ እጅግ አነስተኛ ይሆን እንደ ነበር ማስታወስ አለብን። ሆኖም ግን ይህን ዝናብ በማግኘታቸው አሁንም ምናልባት እስከ ስድስት ወራት ድረስ ለአንበጣው መራባት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል። ማለትም ከአሁን ጀምሮ እስከመጪው ሰኔ ማለት ነው።»
እሳቸው እንደሚሉትም በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁለት የአንበጣ ትውልድ ይፈጠራል፤ አንዱ ትውልድ እስኪ ደርስ እስከ ሦስት ወራት ይወስዳል። የአንበጣ መንጋን ለማስወገድ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚገባቸውን ዘዴዎች በተመለከተ በFAO ከፍተኛ የአንበጣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ ኬትዝ ኬርስማን ሲናገሩ፤ አካባቢው ላይ የሚደረገው ቅኝት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ያሳስባሉ። በቅኝቱም አካባቢው ለአንበጣ መራባት ተስማሚ የመሆኑን፤ በስፍራውም የተራባ አንበጣ እንደሚገኝ መፈተሽ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም አመልክተዋል። በቅኝቱ ወቅት የመኖሩ ምልክት ከታየ መድኃኒት ተጠቅሞ ከዚያ አካባቢ እንዳይወጣ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ያመለከቱት ባለሙያው መብረር የሚችል ከሆነ የሚያዋጣው በአውሮፕላን የመድኃኒት ርጭት ማድረግ እንደሚሆን ገልጸዋል። እንደ ባለሙያው በአሁኑ ሰዓት በተጠቀሰው አካባቢ ያለው የአንበጣ መንጋ ይዞታ እጅግ አሳሳቢ ነው።
«አሁን ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም ውጤታማ ናቸው ያልኳቸውን የማጥፊያ መንገዶች መጠቀሙ እጅግ ፈታኝ ነው። በተለይ ሶማሊያ አውሮፕላን የላቸውም። በዚያም ላይ መሬት ላይ ያሉትን አውሮፕላኖች ለመደገፍ የሚችል ብሔራዊ አቅምም የለም። በዚያም ላይ ቅኝቱን ለማድረግ፤ ኢላማዎች ላይም ምልክት ለማስቀመጥ፤ እንዲሁም ርጭቱን ከሚያደርጉ አውሮፕላን አብራሪዎች ጋር ከአየር እና ከመሬት ግንኙነቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ ነገሮች የሉም። በዚያም ላይ ሶማሊያ ውስጥ አሁንም ደህንነታቸው የሚያሰጋ አካባቢዎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። በነዚህ ስፍራ መሥራት አይቻልም። ይህ ደግሞ ሶማሊያ ውስጥ የትኛውንም በአጭር ጊዜ ሊከናወን የሚችል መከላከልን በጣም አዳጋች ያደርገዋል።»
ስለዚህ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ለመከላከል የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነው ባለሙያው ያመለከቱት። ሶማሊያ ውስጥ በጣም የሚያስፈልገው መካከለኛ እና የረዥም ጊዜ የአንበጣ ማስወገድ ስልት ነው። ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ብሔራዊ አቅም መገንባት የሚያስችል ጠቀም ያለ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። በኢትዮጵያ ግን ይላሉ፤
«ከድንበሩ ወዲያ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አቅማቸው የተሻለ መሆኑን መጥቀስ አስፈላጊ ነው። በስፍራው ያለውን የመቃኘት፣ የመቆጣጠር እንዲሁም በአየር የሚደረገውን ዘመቻ መደገፍ የሚያስችል አቅም አላቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው አሁን የሚደረገውን ዘመቻ ማጠናከር ነው። ኢላማቸውን በደንብ እንዲመቱ በመጠን ደረጃ አቅማቸውን ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል። »
አንበጣ ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው በሰሜን የሶማሊያ የባሕር ዳርቻ እና በከፊል የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደነበር ነው ባለሙያው የሚናገሩት። ዘንድሮ ግን በኦጋዴን እንዲሁም ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ሶማሊያ አካባቢ ሳይቀር ተስፋፍቶ የታየበት ምክንያት የአየር ጠባዩ እና የባሕር ማዕበሉ ያስከተለው መዘዝ መሆኑን የገለፁት። በተለይ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ የባሕር ማዕበሉ መደጋገም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሳይሆን እንደማይቀርም ያመለክታሉ።
«ይህ ምናልባት ከአየር ንብረት ለውጥ ምልክቶች አንዱ ነው ማለት ይቻላል። ምናልባትም ወዲፊት በተደጋጋሚ የባሕር ማዕበል ይከሰት ይሆናል፤ በርካታ የባሕል ማዕበል ተከሰተ ማለት ደግሞ እንዲሁ የበረሃ አንበጣ እየተፈለፈለ ከፍተኛ ወረራ ሊያደርግ ይችላል ማለት ነው።»
ከዚህም ሌላ ባለፉት ወራት በርካታ አካባቢዎችን ያዳረሰው የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ሆነ በሶማሊያ የምግብ እጥረት ሊያስከትል የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ነው ባለሙያው ያስረዱት። «በትክክል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃ ቀንድም የምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል። ምክንያቱም እንደዚህ ያለ ጥሩ የዝናብ ጊዜ ሲገኝ አርሶ አደሮች ተጨማሪ ዘር በመዝራት ለዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ለመጪ በርካታ ዓመትም የሚሆናቸው አስተማማኝ ምርት ለማግኘት እንደሚያስቡ ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህም ማለት በዚህ ዓመቱ ሰብል ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት የዚህ ዓመት ኑሯቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው እና ለመጪዎቹ በርካታ ዓመታት ተፅዕኖ ይኖረዋል።»
የአንበጣ ተስማሚ ሁኔታ እየተከተለ የሚንቀሳቀስ ፀረ ሰብል ፍጥረት እንደመሆኑ አሁን ተወገደ ከተባለበት አካባቢ መልሶ አይመጣም ማለት አይደለም። አሁንም የFAO ከፍተኛ የአንበጣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያው።
«አሁን አበቃ የተባለው ሳምንታት ቢሆነው ያ ማለት ግን ፈፅሞ ወደኢትዮጵያ አይመጣም ማለት አይደለም። ከአሁን ጀምሮ እስከ የካቲት መጨረሻ፣ መጋቢት መጀመሪያ ባለው ጊዜ በምሥራቅ ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ሶማሊያ የሚገኘው የአንበጣ መንጋ እዚያው እንደሚቆይ ይገመታል። ምክንያቱም በጣም ለምለም ነው፤ አረንጓዴ ሆኖ ቆየ ማለት ደግሞ ለአንበጣው ወደሌላ ቦታ የሚሄድበት ምክንያት የለም ማለት ነው። በዚያ ላይ ነፋሱ ከሰሜን ወደ ደቡብ ስለሆነ የሚመጣው ገሚሱ የአንበጣ መንጋ ወደደቡባዊ ኢትዮጵያ፤ ወደደቡባዊ ሶማሊያ እና ወደሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ሊሄድ ይችላል የሚል ግምት አለ። ከመጋቢት መጨረሻ ጀምሮ እስከ ሰኔ ማለቂያ የነፋሱ አቅጣጫ ከደቡብ ወደሰሜን ይሆናል ።»
ይህ ማለት ደግሞ በስተደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢ የቆየው የአንበጣ መንጋ ዳግም ወደሰሜን የመጓዝ ዕድል ይኖረዋል። ባለሙያው እንደሚሉት በመሠረቱ አንበጣ እንደአየሩ ጠባይ ቦታ በመቀያየር በተለያዩ አካባቢዎች ይሰነብታል። በበጋ መጠኑ ባይበረክትም በሞሪታንያ እና ኤርትራ መካከል ባለው በረሃማ አካባቢ ፤ እንዲሁም በፓኪስታን እና ሕንድ ድንበር አካባቢ ይቆያል። በክረምት ወቅት ደግሞ ተበራክቶ በቀይ ባሕር ዳርቻ፣ በግብፅ፣ ኤርትራ፣ የመን እና ሳውድ አረቢያ አውራቢያ ይከማቻል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ