የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ዋንኛ አጀንዳዎች የትኞቹ ናቸው?
ረቡዕ፣ ነሐሴ 3 2015የብሪክስ አባል አገራት 15ኛ የመሪዎች ጉባኤ ከነሐሴ 15 እስከ 18 ቀን 2015 በደቡብ አፍሪካ ይካሔዳል። ጉባኤው በጁሐንስበርግ ከተማ በሚገኘው ቅንጡው ሳንድተን የስብሰባ ማዕከል ይደረጋል። ደቡብ አፍሪካ ጉባኤውን የምታዘጋጀው የብሪክስ የወቅቱ ሊቀ-መንበር በመሆኗ ነው። ደቡብ አፍሪካ ሊቀ-መንበርነቱን የተረከበችው ባለፈው ጥር ወር ነበር።
በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ማን ይሳተፋል?
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፖሳ፣ የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ፣ የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሉዊዝ ሉላ ዳ ሲልቫ እና የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በጉባኤው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ተፈጽመዋል በሚባሉ የጦር ወንጀሎች ምክንያት ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀሎች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ስላወጣባቸው በጉባኤው በአካል አይገኙም። የመሪዎች ጉባኤውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚሳተፉት ፕሬዝደንት ፑቲን በስብሰባው በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ይወከላሉ።
የኢራን ፕሬዝደንትን ጨምሮ ለ67 የአፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ እስያ እና የካሪቢያን አገራት መሪዎች በጉባኤው እንዲሳተፉ ግብዣ መላኩን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ተናግረዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ፕሬዝደንትን ጨምሮ 20 እንግዶችም ተጋብዘዋል።
የጉባኤው ዋንኛ ርዕሰ-ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
የብሪክስ አዳዲስ አባላት በመቀበል የመስፋፋት ዕቅድ በጉባኤው መሪዎች ከሚወያዩባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና በመሥራችነት ያቋቋሙት ብሪክስ በሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፍት ከአስራ ሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ቀድማ የተቀላቀለችው ደቡብ አፍሪካ ነበረች። አሁን ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ23 አገራት መሪዎች በይፋ የአባልነት ጥያቄ ቀርቦለታል። ኢትዮጵያ ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ የተገለጸው ባለፈው ሰኔ 22 ቀን 2015 ነበር።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እንዳሉት ሌሎች በርካታ አገሮችም መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዴት አባል መሆን እንደሚቻል ጠይቀዋል። ብሪክስ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ምን አይነት መስፈርት እንደሚጠቀም እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ጉዳዩ ግን ላለፉት አስርት ዓመታት ውይይት ሲደረግበት የቆየ እንደሆነ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ባለፈው ሰኞ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። የአምስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ሰነዶች አዘጋጅተዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ "ብሪክስ የሚስፋፋበትን መመሪያ፣ መርኅ እና ሒደት የሚወስነውን ሰነድ ስናዘጋጅ ቆይተናል። በ15ኛው ጉባኤ ሰነዱን ለመሪዎቹ እናቀርባለን። በደብዳቤ እና በቀጥታ ግንኙነት አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡ አገራትን ሥም ዝርዝር እናሳውቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ብሪክስ እንዴት ይስፋፋ በሚለው ጉዳይ ረገድ በአባል አገራት መካከል ያለው ልዩነት ግን ከደቡብ አፍሪካው ጉባኤ ትልቅ ውሳኔ እንዳያሳልፍ ሊያግደው ይችላል። ሩሲያ ብሪክስ አዳዲስ አባል አገራትን ሲቀበል ሊፈጠር የሚችለውን ዕድል በዩክሬን በገባችበት ጦርነት ምክንያት በምዕራቡ ዓለም ለበረታባት መገለል እንደ መፍትሔ አድርጋ ትመለከታለች። ከአሜሪካ የምትገዳደረው ቻይና ጂዖፖለቲካዊ ተጽዕኖዋን ለማሳደግ የብሪክስን መስፋፋት አጥብቃ ትሻለች።
የቻይናን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በቅርበት ያጠኑት አንታራ ጎሻል ሲንግ "በቻይና በርካቶች የብሪክስ አባል አገራት ቁጥር በአምስት መገደብ አጠቃላይ በዓለም ዙሪያ ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች የመናገር ዕድል ገድቧል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ ላይ እየጠነከረ በሚሔደው የቻይና እና የአሜሪካ ፉክክር በመላው ዓለም የሚገኙ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች የቻይናን የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲቀላቀሉ እየተሞከረ ነው" ሲሉ ከወደ ቤጂንግ ያለውን ጠንካራ ፍላጎት ያስረዳሉ።
በብሪክስ መስፋፋት ረገድ ሕንድ ተቀራራቢ ፍላጎት አላት። በጉዳዩ ላይ ቸልተኝነት የሚታየው ከወደ ብራዚል ነው። "እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥልቅ ውይይቶች አድርገናል። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሁላችንም ስንስማማ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተለያይተናል" የሚሉት የደቡብ አፍሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን አንድ አገር ተነጥሎ ሊወቀስ አይገባም የሚል አቋም አላቸው።
"ብራዚል ወይም ሕንድ ላይ ብቻ ማተኮር ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። ሁላችንም እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብሪክስ ሊስፋፋ እንደሚገባ ተስማምተናል። ነገር ግን የመጨረሻው ውሳኔ የመሪዎቹ ነው። እርግጥ ነው መሪዎቻችንን እናማክራለን። ነገር ግን ይኸኛው ቸልተኛ ነው፤ ያኛው አይደለም ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። "ከመሪዎቹ የመጨረሻ ውሳኔ ይኖራል ብዬ አጠብቃለሁ። በዚህም ጉዳዩ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ያገኛል የሚል ተስፋ አለኝ" ሲሉ ናሌዲ ፓንዶር ገልጸዋል።
አምስቱ የብሪክስ አባል አገራት ማለትም ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ከዓለም አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) 26 በመቶ ድርሻ አላቸው። ከዓለም ሕዝብ 42 በመቶው በእነዚሁ አምስት አገራት የሚኖር ነው። የብሪክስ አባል አገራት በዓለም አቀፉ የኃይል አሰላለፍ ድምጻቸውን ከፍ አድርጎ ለማሰማት ሁለት አይነት መንገዶች ይጠቀማሉ። በአንድ ወገን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው ብርቱ ግፊት እያደረጉ ነው። ሁለተኛው ስልት እንደ ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ ያሉ ተቋማትን በመመሥረት ላይ ናቸው።
የቀድሞዋ የብራዚል ፕሬዝደንት ዲልማ ሮዜፍ የሚመሩት ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ በ50 ቢሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል የተቋቋመው ከስድስት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር። ባንኩ ከሁለት ዓመታት በፊት ግብጽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ኡሯጓይ እና ባንግላዴሽን በአባልነት ተቀብሏል።
ይኸ ባንክ በብራዚል በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ አውቶቡሶች፣ በሩሲያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በሕንድ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለመገንባት የሚያስፈልገውን ገንዘብ አቅርቧል። በባንኩ መረጃ መሠረት እስካሁን ድረስ በአምስቱ አባል አገራት ለ96 የግንባታ ዕቅዶች 32.8 ቢሊዮን ዶላር አቅርቧል። በደቡብ አፍሪካው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ሉዋንዳ እምፖሴ ባንኩ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ይለያል የሚል እምነት አላቸው።
"የኒው ዴቬሎመንት ባንክ አወቃቀር ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት እጅግ የተለየ ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ወይም የዓለም ባንክ መዋቅራዊ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚባል ቅድመ-ሁኔታ አላቸው። ተቋማቱ ገንዘብ ሲሰጡ ይኸን ይኸን ማሻሻል አለባችሁ የሚል ቅድመ-ሁኔታ ያስቀምጣሉ።በነዚያ አገሮች ላይ ተቋማቱ የራሳቸውን ሥልጣን ይጭናሉ" ሲሉ ሉዋንዳ እምፖሴ ይናገራሉ።
"እንዲህ አይነቱን ቅድመ-ሁኔታ ከተቋማቱ በሚበደሩ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ተመልክተናል" የሚሉት እምፖሴ ጉዳዩ ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት የሚለየው "ቁልፍ" አሰራር እንደሆነ ገልጸዋል። ሉዋንዳ እምፖሴ እንደሚሉት "ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ እንዲህ አይነት ቅድመ-ሁኔታዎች የሉትም።"
የባንኩ ህልም ግን በብሪክስ አባል አገራት ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ፋይናንስ በማቅረብ ብቻ የሚገታ አይመስልም። ባንኩ በብሪክስ አባል አገራት መካከል በሚደረግ የንግድ ልውውጥ ከዶላር ይልቅ የየራሳቸውን የመገበያያ ገንዘብ ጥቅም ላይ እንዲውል ያበረታታል። ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዘዊ ሉ "ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ እና እያንዳንዱ የብሪክስ አባል አገራት በንግድ፣ መዋዕለ-ንዋይ እና የቦንድ ግብይት ከዶላር ይልቅ የራሳቸውን የመገበያያ ገንዘብ በመጠቀም አማራጭ የፋይናንስ ሥርዓት የመገንባት የጋራ ርዕይ አላቸው" በማለት አስረድተዋል።
በተለይ የዶላር ጉዳይ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፖሳ እና የብራዚሉ አቻቸው ሉላ ዳ ሲልቫን ጨምሮ አብዛኞቹ የብሪክስ አባል አገራት መሪዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያነሱት ነው። አባል አገራቱ በሚኖራቸው የርስ በርስ ግብይት ከዶላር ይልቅ የየራሳቸውን የመገበያያ ገንዘብ የመጠቀም ፍላጎት አላቸው። ለዚህ ደግሞ ዲልማ ሮዜፍ የሚመሩት ኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸ ጉዳይ በደቡብ አፍሪካው የመሪዎች ጉባኤ ትኩረት የሚሰጠው ቢሆንም የመጨረሻ ውሳኔ እንደማይጠበቅ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
"በዚህ ወቅት ትልቅ ውሳኔ ይተላለፋል ብዬ አልጠብቅም" ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ "የፋይናንስ ሚኒስትሮች ተገናኝተው ጉዳዩን ሲፈትሹ ቆይተዋል። የኒው ዴቬሎፕመንት ባንክ ፕሬዝደንት በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ያክል ጊዜ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ ከሚሰጡት ማብራሪያ በኋላ ውሳኔ ማስተላለፍ የመሪዎቹ ድርሻ ይሆናል" ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካው የመሪዎች ጉባኤ ዓለም አቀፍ የጂዖፖለቲካ ጉዳዮች፣ ንግድ እና የመሠረተ-ልማት ግንባታን የመሳሰሉ አጀንዳዎች ጭምር ላይ የሚያተኩር ነው። ኢትዮጵያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ አርጀንቲና፣ ኢንዶኔዥያ እና ግብጽን ጨምሮ 23 አገራት ላቀረቡት የአባልነት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ግን ከፍ ያለ ትኩረት ማግኘቱ አይቀርም።
እሸቴ በቀለ