የተመድ 75 ኛ ዓመት መታሰብያ
ማክሰኞ፣ መስከረም 12 2013ከ75 ዓመት በፊት የተመሰረተዉ የተመድ በጊዜዉ ሌላ የዓለም ጦርነት እንዳይከሰት ከማድረጉም በላይ አስፈላጊ የሆኑ የሰብዓዊ ርዳታዎች እንዲደርሱ አድርጎአል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለፁት የተመድ የተመሰረተበትን 75 ኛ ዓመት በማስመልከት በተጠራ ቪዲዮ ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ነዉ። ይሁንና የተለያዩ ፈተናዎች ያሉበት ድርጅቱ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ግልጋሎት ለመስጠት የመንግሥታቱ ድርጅት ራሱን ማዘመን እንደሚገባዉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች አገር እንደመሆኗና በድርጅቱ ቻርተር የተመለከቱ መርሆች ተግባራዊ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መስራትዋን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ፡ ለድርጅቱም ተልዕኮ ስኬት ላበረከተችው ታላቅ ሚና ከብር እንደሚሰማትም ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በለዉጥ ዉስጥ እንደነበረች የገለፁት ዐቢይ ፤ የኮቪድ ወርርሽኝን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መፍትሄ እንደሚሻ ተናግረዋል።
«ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት የጤና አገልግሎት ሥርዓቶችን ባጨናነቀው እና የዓለም ኤኮኖሚን በተፈታተነው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተጓትቷል። በዚህ ምክንያት በአፍሪቃ ሃገራት ላይ የደረሰዉ ጫና የሚካድ አይደለም። ለዚህም ነዉ አፍሪቃ በካፒታል ድጋፍ፣ በዕዳ ስረዛ፣ የዕዳ አከፋፈል ለውጥ ወይም ማኅበራዊ ዘርፎችን በመደገፍ ለማነቃቂያ ዕገዛ የምትፈልገው።ለዚህም ነዉ የቡድን 20 አባል ሃገራት የማነቃቂያ ድጋፍ እንዲያደርጉ የምንፈልገዉ። በእርግጠኝነት ዓለም አቀፍ መፍትሔ የሚሹ እንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ትልቅም ይሁን ትንሽ አንድ አገር ብቻዉን ሊወጣ አይችልም»
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን የሚታዩትን ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ሁሉ ለመጋፈጥ መሻሻል ይኖርበታል ሲሉ የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አስጠነቀቁ። ሜርክል ይህን ጥሪ ያቀረቡት ዛሬ ታስቦ የዋለዉን የተመድ 75ኛ ዓመት ምስራታ ቀንን በማስመልከት ነዉ። ጀርመን በመንግሥታቱ ድርጅት በርካታ ኃላፊነቶችን እየተወጣች ነዉ ያሉት መራሂተ መንግስቷ ፤ ሃገራቸዉ ጀርመን በፀጥታዉ ምክር ቤትም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ዝግጁነትዋንም ገልፀዋል። ከድርጅቱ ጋር ሁሉም ነገር ስኬታማ ነዉ ብሎ ማሰብ ግን ስህተት መሆኑን የጠቆሙት ሜርክል፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሃገራት በየግላቸዉ እንዳላቸዉ ቅርበት ሁሉ ድርጅቱ ከሃገራቱ ጋር ሁሉ እጅግ በቅርበት መስራት ይኖርበታል ሲሉ ጥሪን አስተላልፈዋል። የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት ይህን ሲናገሩ ግን አንድንም ሃገር በስም አልጠቀሱም።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ