ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱት ቁጥር ጨምሯል
ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2015የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዩች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN OCHA) እንዳስታወቀው 76,500 የሚደርሱ ዜጎች የሱዳን እርስ በርስ ግጭት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ከሱዳን የሚሻገሩ ዜጎች በመተማ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል በየጊዜው እየገቡ እንደሚገኙ ዘገባው ጠቅሷል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ በኩል ለገቡ 7,600 የሚደርሱ የሱዳን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ መስጠቱን ድርጅቱ አስታውቋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መሐመድ አብዱላዚዝ በኩርሙክ ለሚገኙ 13,625 የሱዳን ስደተኞች እንደሚገኙ ተናግረዋል። በመተከል በኩል ደግሞ ወደ ሱዳን ተፈናቅለው የነበሩ 17,474 የኢትዮጵያ ዜጎች መመለሳቸውን አክለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዩች ማስባበርያ ቢሮ የሱዳን ግጭት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ አስመልክቶ ባወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መንገዶች ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩንም ጠቁመዋል። ከ50 አስከ 60 የሚደርሱ ሰዎች በየጊዜው ወደ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ እንደሚገቡም ተገልጸዋል። ወራትን ያስቆረውን የሱዳን ጦርነትን በመሸሽ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ በኩል ለገቡ 7,200 የሱዳን ዜጎች የምግብ ድጋፍ ማድረጉን ሰብአዊ ጉዳዎች ማስተባበሪያ ቢሮው አስታውቀዋል። 300 የሚሆኑ ስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎችም በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ የሚባል ወረዳ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በኩርሙክ በወባ በሽታ የሕጻናት ሕይወት ማለፉን የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ አብዱላዚዝ በሱዳንውስጥ ግጭት ከተከተሰ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ወደ ኩርሙክ ወረዳ የገቡ ከ13 ሺህ በላይ እንደሆኑ ተናግረዋል። በኩርሙክ የሚገኙ የሱዳን ዜጎች መካከል የተወሰኑት ለምግብ እጥረት ተጋልጠው መቆየታቻቸውን እንዲሁም የወባ በሽታ መስፋፋት ጉዳት ማድረሱን አብራርተዋል። በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙት በተጨማሪም በየጊዜው ከሱዳን የሚሻገሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ተቀላቅሎ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ተቋማቸው ለሁለተኛ ዙር ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ድጋፍ ማድረሱን ተናግረዋል።
በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ በኩል ደግሞ ከ17 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የተፈናቀሉ ዜጎች መመለሳቸውን አመልክተዋል። እነዚህ የተመለሱ ዜጎች ከዚህ ቀደም በዞኑ የነበረው የጸጥታ ችግር ሸሽተው ሱዳን ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል። የሱዳን ግጭት በመሸሽ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቡ ዜጎችን ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ሰብአዊ ድጋፍ ለማደረስ የለጋሽ ድርጅቶች እገዛ እንደሚያሰፈልገም አክለዋል። በሱዳን ውጥ ጦርነት ከተሰከተ ጊዜ አንስቶ ግጭቱን የሸሹ ሰዎች በአማራ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ጋምቤላ በኩል ወደ ኢትየጵያ እየሸገሩ እንደሚገኙ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያስረዳል። ከጠቅላላ ወደ ኢትጵያ ከመጡት መካከል አብዛኞቹ በመተማ በኩል ድምበር አቋርጠው የገቡ መሆናቸወን ዘገባው አመልክቷል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ