1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተፈጥሮ አደጋዎችና ወረርሽኞች የታጀበው 2016

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017

2016 ዓ.ም. ጥቂት የማይባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተዋል፤ የበርካቶችን ሕይወት ነጥቀዋል፤ ሚሊየኖችንም ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅለዋል። ይህ ብቻም አይደለም በዚሁ ዓመት የወባ በሽታ ባለፉት ዓመታት ከነበረው ይዞታ በተለየ መልኩ ተባብሶ መስፋፋቱም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4kjPF
የመሬት መንሸራተት በሲዳማ
ሲዳማ ውስጥ የደረሰው የመሬት መንሸራተት ፎቶ ከማኅደርምስል Bureau of Government Communications Affairs of Sidama Region

ጤና እና አካባቢ

 

የተፈጥሮ አደጋዎች በ2016

በያዝነው ጎርጎርዮሳዊ 2024 ዓ.ም.  በመላው ዓለም የተከሰተው የመሬት መንሸራተት የተፈጥሮ አደጋ ባለፉት ዓመታት ካጋጠመው እጅግ የበዛ መሆኑን ባለፈው ሐምሌ ወር ይፋ የሆነ መረጃ ያመለክታል። 2024 በኢትዮጵያ 2016 ታኅሣስ ወር ማለቂያ ገደማ የባተ እንደመሆኑ ከዚያ አንስቶ እስከ ጳጉሜን መጨረሻ ቀናት ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቶ ጉዳት አድርሷል። የመሬት መንሸራተትን ከሚጋብዙ መንስኤዎች አንዱ የሆነው የጎርፍ አደጋም በዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎችም አጋጥሟል።

ከባድ ዝናብና የጎርፍ አደጋ

ለረዥም ወራት በዝናብ እጥረት እና ድርቅ የአየር ሁኔታ የሰነበተው የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ከካቻምና የክረምት ወቅት አንስቶ መጠኑ የበረከተ ዝናብ እየወረደበት ከርሟል። በዚህም ምክንያት ይመስላል በተሰናበተው 2016 ከዓመቱ የመጀመሪያ ወራት አንስቶ ነበር ስለተፈጥሮ አደጋዎች መከሰት መሰማት የጀመረው። በኅዳር ወር በድርቅ በተጎዳው ሶማሌ ክልል ውስጥ በተከታታይ ለቀናት የጣለው ዝናብ ጎርፍ አስከትሎ ቢያንስ የ28 ሰዎችን ሕይወት መንጠቁን የክልሉ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጽሕፈት ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ገደቡን በማለፉ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ69 ሺህ በላይ ሕዝብን ማፈናቀሉም የተሰማው በዚያው ሰሞን ነበር። በወቅቱም ጎርፉ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ስድስት ትምህርት ቤቶችን ሲያወድም ስምንት ትምህርት ቤቶችን ከብቦ ከሦስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ማድረጉ አይዘነጋም።

መረጃውን ይፋ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ በእንግሊዘኛ ምህጻሩ OCHA እንዳመለከተው የጎርፍ አደጋው የደረሰው ከጥቅምት ወር መግቢያ አንስቶ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ነው። እንደ ኦቻ ዘገባ ከሆነም በኢትዮጵያ ከፍተኛ አካባቢዎች የጣለው ዝናብ ዝቅተኛና ቆላማ አካባቢዎች በጎርፍ አደጋ እንዲጠቁ ምክንያት መሆኑንም አመልክቷል።

የኦሞ ወንዝ አካባቢ እንደውም ክረምት በመጣ ቁጥር ወንዙ እየሞላ በአቅራቢያው የሚገኙ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ መሆኑ ዓመቱ መገባደጃ ላይም ታይቷል። በነሐሴ ወር አጋማሽ የኦሞ ወንዝ እና በኬንያ ድንበር ላይ የሚገኘው ቱርካና ሐይቅ መሙላታቸው የኦሞራቴ ከተማን ሥጋት ውስጥ መጣሉን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የወንዞቹ ውኃ ከመጠናቸው አልፎ የኦሞራቴ ከተማን መክበባቸው 10,000 ገደማ ነዋሪዎች ያሏት ኦሞራቴ በጎርፍ እንዳትጥለቀለቅ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ እንደነበር በወቅቱ የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ የላከው ዘገባ ያመለክታል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩትም መንደሮች በውኃው ተከበዋል፤ የተጥለቀለቁም አሉ።

 

የኦሞ ወንዝ ሙላት
በኦሞ ወንዝ ሙላት የተጥለቀለቀችው በደቡብ ኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ፎቶ ከማኅደር ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

 

ባለፉት ዓመታት በአካባቢው ጎርፍ መከሰቱ የተደጋገመ ቢሆንም በ2016 ያጋጠማቸው ግን ከበድ ያለ እንደሆነ የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ገልጿል። እንደ አስተዳደሩ መረጃ ከሆነም ከሁለት ዓመታት በፊት በደረሰው ጎርፍ ምክንያት የተፈናቀሉ በጊዜያዊ መጠለያ ከሚገኙት ከ79 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል 15 ሺህ ያህሉ በድጋሚ ባለፈው ዓመት በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት ዳግም ለመፈናቀል ተዳርገዋል። ጎርፉ ይዞታውን በማስፋፋት ወደ ዞኑ አስተዳደር መቀመጫ የሆነችውን ኦሞራቴ ወረዳን በመክበቡም ነዋሪዎችን ስጋት ውስጥ መክተቱንም የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ ተናግረው ነበር።

ምንም እንኳን በተፈጥሮ አደጋው ለተፈናቀሉ ወገኖች ዳግም ለጎርፍ እንዳይጋለጡ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ቢገልጽም፤ በዳሰነች ወረዳ በየዓመቱ ለሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ የአካባቢው ነዋሪ ተረጋግቶ መኖር እንዲችል ማድረግ እንደሚገባ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አሳስበዋል።

በ2016 በተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ በርካቶችን በማፈናቀል በስድስት ወረዳዎች በሰብልም ላይ ጉዳት  ያደረሰው ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ነው። ከዘጠኝ መቶ በላይ ቤቶች በውኃ የተጥለቀለቁ ሲሆን ከ1200 ሄክታር በላይ የበቆሎ፤ የስንዴ፤ የማንጎ፤ የፓፓያ እና የቡና ምርት ከጥቅም ውጪ እንደሆነ ነው የስልጤ ዞን የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው። በስልጤ ወረዳ የጎፍላ ቀበሌ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ጎርፍ ያደረሰውን ጉዳት እንዲህ ነው የገለጹት።

በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የሚከሰተው ጎርፍ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ያደረሰው ጉዳት ሌላው ተጠቃሽ የተፈጥሮ አደጋ ነበር። በተጠቀሰው ስፍራ በዓመቱ ማለቂያ አካባቢ ነሐሴ ወር ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ማሳዎችን ውጧል፤ 19 የቤት እንስሳትንም ገድሏል። ጎርፉ ከ270 በላይ ሄክታር በምርት የተሸፈነ መሬት ከጥቅም ውጪ እንዳደረገም ነው የተገለጸው።

በአማራ ክልል የጎርፍ አደጋ
በአማራ ክልል የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ፎቶ ከማኅደርምስል Aleminew Mekonnen/DW

ጎርፍ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን መክበቡም የተሰማው በዚሁ በተሰናባቹ 2016 የመጨረሻ ወር ነበር። በክልሉ ደቡብ ጎንደር ዞን ሦስት ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ዘጠኝ ቀበሌዎች የክረምቱ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሺህዎች የሚገመቱትን ነዋሪዎች መንቀሳቀሻ ማሳጣቱ ተነግሯል። በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል በደራ፣ በሊቦ ከምከምና በፎገራ ወረዳዎች በሚገኙት ቀበሌዎች ከሐምሌ 20/2016 ዓ ም ጀምሮ በተከታታይ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የአካባቢው ወንዞች ሞልተው ሜዳማ ወደሆኑ ቀበሌዎች ከስድስት ሺህ በላይ ቤቶች በጎርፍ ሲከበቡ በርካታ ሄክታር የሩዝ ሰብልም ወድሟል። እንዲያም ሆኖ አካባቢው ላይ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጎርፍ የተከበቡትን ወገኖች መርዳት እንዳዳገተ ነው የክልሉ ባለሥልጣናት የተነገሩት።  

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ በሰሜን ወሎ፤ በሰሜን  ሸዋ፤ በምዕራብ ጎጃም፤ በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሌሎች አካባቢዎችም ጎርፍ እና ናዳ የሚያስከትል ዝናብ እንደሚኖርም የአየር ትንበያ ባለሙያዎችን ጠቅሶ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፕሮግራም በወቅቱ አሳውቋል።  

የመሬት መንሸራተት

ጎርፍ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ፤ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ነበር። በገዜ ጎፋ ወረዳ የመንግሥት አካላት እንደሚሉት የመሬት መናዱ ከ240 በላይ ሰዎች ድንገት ከመሬት ቀብሮ ሕይወት አሳጥቷል። የመሬት መናዱ በወላይታ፤ ሲዳማ፤ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥም የሰው ሕይወት ከመቅጠፍ አልፎ በርካቶችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።

አማራ ክልል ውስጥም ጎንደር፤ ደሴ ፣ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ የመሬት መናድ አደጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ነበሩ። ዶክተር ተሻለ ወልደአማኑኤል የወንዶ ገነት የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን እና የደን ዘርፍ ተመራማሪ ለመሬት መናድ አደጋ ምክንያያቶች ይሆናሉ ያሏቸውን ገልጸውልን ነበር።

የዶዶላ ጎርፍና መሬት መንሸራተት
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ፎቶ ከማኅደርምስል Dodola communication

የወባ ወረርሽኝ

በዋናነት ባለፈው ዓመት 2016 የወባ ወረርኝ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዳግም ማገርሸቱ ታይቷል። ቀደም ባሉት ዓመታት በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ወባ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየቀነሰ፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም ጠፍቷል እስከመባል መድረሱ አይዘነጋም። ባለፈው ዓመት ግን በተለይ ግጭትና የጸጥታ መረጋጋት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ዳግም በወባ ወረርሽኝ እየተጎዳ መሆኑ ገና በዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ነበር መሰማት የጀመረው። እስከ ዓመቱ ማብቂያም የወባ ወረርሽኝ መባባሱ ሲነገር ከርሟል። ትኩረታችንን ኢትዮጵያ ላይ አደረግን እንጂ ባለፈው ዓመት 2016 የወባ በሽታ አሜሪካን ሀገርም መከሰቱ ተነግሯል። የዓለም የጤና ድርጅትም የወባ በሽታ መስፋፋት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሳይገናኝ እንደማይቀር ጠቁሟል።

ዋትስአፕ መለያ
ዋትስአፕ የማኅበራዊ መገናኛ መለያፎቶ ከማኅደር ምስል photothek/picture alliance

የ2016 ስንብት

2016 በአብዛኛው ደስ የማይሉ ዜናዎች የተሰሙበት መሆኑን ለመጠቆም ለአዲሱ ዓመት 2017 ዋዜማ ብዙዎች የተለዋወጡትን የስንብት መልእክት እኛም እናንሳ፤ «በጣም አዝናለሁ፤ ይህን ያህል ቀን አብረን ስናሳልፍ አንድም ቀን እኔ አልከፋኝም ነበር። ነገር ግን እናንተ እኔን በክፉ አማችሁኝ፤ በእኔም አጉረመረማችሁ፤ ለማንኛውም ላንገናኝ እስከ ወዲያኛው ልለያችሁ ከመጨረሻው ስለደረስኩ አብዝቼ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ከእኔ የተሻለውን ያምጣላችሁ ይላል 2016 ዓም»። እኛም 2017 በጎ ዜና የሚሰማበት የተሻለው ዓመት እንዲሆን በመመኘት እንሰናበት።

 ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ